ዋልያዎቹ ከጥቋቁር ከዋክብቶቹ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ በየትኛው ገለልተኛ ስታዲየም እንደሚከናወን ተረጋግጧል።
ኳታር ለምታስተናግደው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምድብ 7 ተደልድሎ የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎችን እያደረገ እንደሆነ ይታወቃል። ምንም እንኳን የማጣሪያ ጨዋታዎቹ ባይጠናቀቁም ቡድኑ ከወዲሁ ከዓለም ዋንጫው ውድድር ውጪ መሆኑ ተረጋግጧል። ይህ ቢሆንም ብሔራዊ ቡድን ከጋና እና ከዚምባቡዌ ጋር የምድብ 5 እና 6ኛ ጨዋታዎችን ከሳምንታት በኋላ ማድረግ ይቀጥላል።
ከጋና ጋር የሚደረገው መርሐ-ግብር የሜዳ ላይ ጨዋታ ቢሆንም ካፍ በኢትዮጵያ የሚገኙ ስታዲየሞች ብቁ አይደሉም በሚል በማገዱ ጨዋታው በሀገራችን የመካሄዱ ነገር አክትሞለታል። ከዚህ መነሻነት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከጋና ጋር የሚደረገው ጨዋታ ደቡብ አፍሪካ፣ ዚምባቡዌ እና ኬንያ ላይ እንዲደረጉ ፍላጎት በማሳየት እንቅስቃሴ ላይ የነበረ ሲሆን አሁን የመጫወቻ ሜዳው መታወቁን አረጋግጠናል። በዚህም ደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የኦርላንዶ ስታዲየም የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን ከጋና አቻው ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ እንደሚያስተናግድ ታውቋል።
የኬንያ እና የዚምባቡዌ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ለቀረበላቸው ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ቢሰጡም ዚምባቡዌ ያላት ስታዲየም የመጨረሻ ጨዋታውን ብቻ እንዲያስተናግድ በመወሰኑ ከመጨረሻ እጩነት ውጪ መሆኑ ተረጋግጧል።
ብሔራዊ ፌዴሬሽናችንም ጨዋታው ደቡብ አፍሪካ ላይ እንዲከናወን የወሰነው የመጨረሻ ጨዋታው ዚምባቡዌ ሀራሪ ላይ ስለሆነ የጉዞ እና ተያያዥ ወጩዎችን ለመቀነስ እንደሆነ አመላክቷል።