የ2014 የውድድር ዘመን የመጀመሪያ ሐት ትሪክ የሰራው የዐፄዎቹ አጥቂ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ተከታዩን አጭር ቆይታ አድርጓል።
የ2014 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ውድድር በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የመጀመሪያውን ሳምንት ጨዋታዎች በትናንትናው ዕለት አገባዷል። ፋሲል ከነማ የ2013 የውድድር ዘመን ያገኘውን አዲሱን ዋንጫ ባነሳበት ጨዋታ ሀድያ ሆሳዕናን 3ለ1 በመርታት አጀማመሩን አሳምሯል፡፡ በጨዋታውም አጥቂው ፍቃዱ ዓለሙ ለቡድኑ ሦስቱን ግቦች ከመረብ በማሳረፍ የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያው ባለ ሐት ትሪክ ሆኗል፡፡
የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ እና መከላከያ አጥቂ በ2012 የውድድር ዓመት ዐፄዎቹን ተቀላቅሎ የነበረ ቢሆንም ከጉዳቶች እና በቂ የመሰለፍ ዕድል አለማግኘት ጋር በተያያዘ ግልጋሎት መስጠት አልቻለም። ይሁን እንጂ ፋሲሎች በድል ዓመቱን ሲጀምሩ በመጀመርያ አሰላለፍ ውስጥ ተካቶ የነበረው ተጫዋቹ ሀድያ ሆሳዕና ላይ ሦስት ግቦችን ከመረብ አዋህዶ የ2014 የጎል አካውንቱን ከፍቷል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያም ስለ እቅዱ እና ተያያዥነት ያላቸውን ጥያቄዎች በአጭሩ ለአጥቂው አቅርባለች፡፡
“ትናንት በመጀመሪያ ጨዋታዬ ሦስት ጎሎችን ማስቆጠር በመቻሌ ጥሩ ስሜትን ፈጥሮልኛል። ከዚህ የተሻለ ማድረግ እንደምችልም መነሳሳትን የፈጠረልኝ ይመስለኛል፡፡ ለሚቀጥሉትም ጨዋታዎች ንቁ ሆኜ እንድጫወት ትልቅ ነገርን በውስጤ አድርጎልኛል ብዬ አስባለሁ።”
በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ከጥቂት ጨዋታዎች ውጪ እምብዛም በበቂ ሁኔታ ለዐፄዎቹ ግልጋሎት መስጠት ያልቻለው አጥቂው እንዲህ ሲል ካለፈው ዓመት ጋር አጀማመሩን ያነፃፅራል፥ “ባለፈው ዓመት ለእኔ ጥሩ ጊዜ ነበረ ማለት አልችልም። አሁን ግን ጥሩ አካሄድን ጀምሪያለሁ። ጎሎችንም እያገባሁ በጥሩ መንገድ እሄዳለሁ ብዬ አቅጃለሁ። ጎሎችን እያገባሁ ክለቤንም አግዛለሁ። የዚህ ዓመት እቅዴ ይሄ ነው፡፡ የሙጂብ መውጣት ትልቅ ክፍተት አለው። እሱን ቦታ ደግሞ ከኦኪኪ ጋር እየተረዳዳን ጥሩ ነገር ለመሥራት አስቤያለሁ።” ሲል ዐምና አንድ ጨዋታ ብቻ በመጀመርያ ተሰላፊነት የተጫወተው አጥቂ ይናገራል።
ሶከር ኢትዮጵያ በቅድመ ውድድር ዝግጅት ዳሰሳዋ የፋሲል ከነማን ዝግጅት በምትሠራበት ወቅት ከአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ጋር በነበራት ቆይታ “በፍቃዱ ዓለሙ ዘንድሮ እምነት አለኝ” ብለው ተናግረው የነበረ ሲሆን ተጫዋቹም የአሰልጣኙን ንግግር ወደ ተግባር እንደሚለውጥ ያምናል። ” እሱ አቅሜን ስለሚያውቅ በተለይ ከዚህ በፊት የነበረኝን ስለሚያውቅ ሌላም ክለብ አሰልጥኖኛል። ያንን አቅም ደግሞ በደንብ ስለሚያውቅ እኔም ውስጥ ያለውን ነገር ስለሚያውቅ ያንን ያመጣዋል ብሎ ስላሰበ ይመስለኛል እምነት አለኝ ያለው። እንደ ቃሉም ሆኗል ብዬ ገምታለሁም”
በመጨረሻም “ዘንድሮ በድጋሚ ክለባችን ዋንጫ እንዲያነሳ ትልቁን ድርሻ ለመውሰድ እጥራለሁ። ይሄን ስል ጎል እያገባው ክለቤን በተቻለ መጠን እየረዳው ማለት ነው። ይሄን ያህል ጎል አገባለው ብዬ ያስቀመጥኩት ነገር የለም። ጎሎችን ባገኘሁት አጋጣሚ እያገባው በደንብ ክለቤን እረዳለሁ ብዬ ነው የማስበው።” ሲል ሀሳቡን አጠቃሏል።