የከፍተኛ ሊግ የምድብ ሐ ተካፋዩ ነገሌ አርሲ የቀድሞው አሰልጣኙን በድጋሚ ሾሟል፡፡
በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በምድብ ሐ ስር ካሉ አስራ ሁለት ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ነገሌ አርሲ በአሰልጣኝ ታዬ ናኒቻ መሪነት የ2013 የውድድር ዘመንን በምድቡ በሰበሰባቸው 27 ነጥቦች 6ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቆ የነበረ ሲሆን ለ2014 የውድድር ዘመን በአዲስ አሰልጣኝ ለመመራት በማሰብ የቀድሞው አሰልጣኙን ወደ ኃላፊነት አምጥቷል፡፡ አሰልጣኝ ራህመቶ መሐመድም ከሁለት ዓመት በኋላ ዳግም አዲሱ የክለቡ አሰልጣኝ ሆኗል፡፡
የተጫዋቸነት ዘመኑን በአዳማ ከተማ እና ሙገር ሲሚንቶ አሳልፎ ወደ አሰልጣኝነት ሙያው ከመጣ በኋላ በባቱ (ዝዋይ) ከተማ ረዳት አሰልጣኝ እንዲሁም ደግሞ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ በመሆን በተለያዩ ጊዜያት ያገለገለ ሲሆን ቀጥሎ በመቂ ከተማ እንዲሁም ደግሞ በሞጆ ከተማ ዋና አሰልጣኝ በመሆን ሰርቷል፡፡ በ2011 ነገሌ አርሲን አሰልጥኖ የነበረ ሲሆን በድጋሚ ዋና አሰልጣኝ ተደርጎ ተሹሟል፡፡