ዳዊት እስጢፋኖስ ጠንከር ያለ ቅጣት ሲተላለፍበት ሦሰት ተጫዋቾች ላይም የቅጣት ውሳኔ ተሰጥቷል

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ በታዩ የዲሲፕሊን ግድፈቶች ዙሪያ የውድድር አመራር እና ሥነ ስርዓት ኮሚቴው ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

የ2014 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ከሰሞኑ በተደረጉ ስምንት ጨዋታዎች ተጀምረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር አመራር እና ሥነ ስርዓት ኮሚቴም በተደረጉ ስምንት ጨዋታዎች ላይ የታዩ የዲሲፕሊን ጥሰቶች ዙሪያ ጠንከር ያለ ውሳኔን አስተላልፏል፡፡

ጅማ አባጅፋር በመክፈቻ የመጀመሪያ ቀን በሀዋሳ ከተማ 1ለ0 በተሸነፈበት ጨዋታ 70ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የወጣው አማካዩ ዳዊት እስጢፋኖስ ከአስራ ስድስት ደቂቃዎች በኋላ ከነበረበት የተጠባባቂ ወንበር በመነሳት ኳስ አቀባይን በፕላስቲክ ውሀ መጠጫ በመማታቱ የዕለቱ አራተኛ ዳኛ አሸብር ሰቦቃ ለዋና ዳኛው ኃይለየሱስ ባዘዘው ጠቁመው የዕለቱ ዋና ዳኛም በቀይ ካርድ እንዲወገድ አድርገውት ነበር። በወቅቱ ተጫዋቹ ከቀይ ካርዱ በኋላ አፀያፊ ስድብን የዕለቱ ዳኞችን መሳደቡ ሪፖርት የተደረገ ሲሆን የ7 ጨዋታዎች እና የሰባት ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ተላልፎበታል፡፡ ተጫዋቹ ላይ ቅጣት መጣሉን ያወቀው ክለቡ ተጫዋቹን ወደ አዲስ አበባ እንደሸኘውም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ሌላው ቅጣት የተጣለበት ተጫዋች ኤፍሬም ዘካርያስ ሆኗል። ቡድኑ ሀዲያ ሆሳዕና በፋሲል ከነማ በተሸነፈበት ጨዋታ በ83ኛው ደቂቃ በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣው ተጫዋቹ ዳኛውን አፀያፊ ስድብ ስለመሳደቡ ሪፖርት የቀረበበት ሲሆን በዚህም በድምሩ 4 ጨዋታ እና ሦስት ሺህ ብር ቅጣት ተላልፎበታል።

በመጀመሪያው ሳምንት የማሳረጊያ ጨዋታ ሰበታ ከተማ ቅዱስ ጊዮርጊስን በገጠመበት እና ያለ ጎል በተጠናቀቀው ጨዋታ ላይ 89ኛው ደቂቃ ላይ የሰበታው ተከላካይ አንተነህ ተስፋዬ በቅዱስ ጊዮርጊሱ አማካይ ሀይደር ሸረፋ ላይ በሰራው አደገኛ አጨዋወት በቀይ ካርድ የተወገደ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ ኮሚቴው የ3 ጨዋታ የሦስት ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ተጫዋቹ ላይ አስተላልፏል፡፡

በሌሎች ቅጣቶች ወልቂጤ ከአዳማ በነበረው ጨዋታ በሁለት ቢጫ ከሜዳ የወጣው ረመዳን የሱፍ አንድ ጨዋታ ቅጣት ሲተላለፍበት በቡድን ደረጃ ወልቂጤ ከተማ ሰባት ቢጫ ካርድ የተመዘገበ በመሆኑ ክለቡ አምስት ሺህ ብር እንዲከፍል፤ ሰበታ ከተማ በአንፃሩ ከቅዱስ ጊዮርጊስ በነበረው ጨዋታ አምስት ቢጫ ካርድ በመመዝገቡ ክለቡ ላይ የአምስት ሺህ ብር ቅጣት በተመሳሳይ ተጥሎበታል፡፡