ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

በዚህ ፅሁፋችን ደግሞ በጨዋታ ሳምንቱ ትኩረት የሳቡ አሰልጣኝ ነክ ጉዳዮች የዳሰስንበት ነው።

👉 የአሰልጣኞች መሸጋሸግ

በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ በተለይ አዳዲስ ፊቶችን በስልጠናው ዘርፍ መመልከት አስቸጋሪ ሲሆን ይታያል። እርግጥ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተወሰነ መልኩ በሊጉ ለማሰልጠን አዲስ የሆኑ አሰልጣኞችን እዚህም እዚያም መመልከት የጀማመርን ቢሆንም አሁንም ግን ክለቦች አሰልጣኞችን የሚቀጥሩበት መንገድ መጤን ይኖርበታል።

በሳምንቱ መጨረሻ ጅማሮውን ባደረገው በአዲሱ የውድድር ዘመን ተካፋይ ከሆኑ 16 የሊጉ ክለቦች ውስጥ ዐምና ካሰለጥኗቸው አሰልጣኞች ጋር የቀጠሉ ክለቦች ከታች ያደጉት ሦስት ክለቦችን ጨምሮ በድምሩ 5 (31%) የሚሆኑት ናቸው። ዐምና በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ቡድኖችን ተረክበው የነበሩና ዘንድሮም ከቡድኖቹ ጋር የቀጠሉትን እዚሁ ዝርዝር ውስጥ ብንጨምራቸው በቁጥር ወደ 7 (44%) የሚሆኑት አሰልጣኞች ከቡድኖቻቸው ጋር ሲቀጥሉ የተቀሩት ከግማሽ የሚበልጡት ቡድኖች ግን አሰልጣኞችን ቀይረዋል።

እዚህ ጋር አሰልጣኞችን ቀይረዋል ከሚለው አገላለፅ ይልቅ “አሰልጣኞችን አሸጋሽገዋል” የሚለው ቃል የተሻለ የሚገልፅ እንደሆነ ለመረዳት አሰልጣኝ ከቀየሩት ቡድኖች ውስጥ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ውጭ የተቀሩት ክለቦች ባሰናበቷቸው አሰልጣኞች ምትክ ዐምና በሊጉ በሌሎች ክለቦች ሲያሰለጥኑ የነበሩ አሰልጣኞችን በምትካቸው ቀጥረዋል።

የማሸጋሸጋቸው ነገር ብዙ ላያስብል ይችላል። ነገርግን በርከት ያሉ የቅጥር ሒደቶች በእግር ኳሳዊ እሳቤ (Footballing Merit) የተደረጉ ስለመሆናቸው ግን አጠራጣሪ ናቸው። ከስንብቶች እስከ ተተኪ ቅጥር ያለው ሒደት በግልፅ የማይታወቅ እና ገዢ በሆነ የእግር ኳሳዊ አስተሳሰብ የሚመሩ አይደሉም።

እርግጥ በሌሎችም ሀገራት በላይኛው ሊግ የሚገኙ ክለቦች ተተኪ አሰልጣኞችን ሲያፈላልጉ ለምርጫ የሚቀርቡት አማራጫቸው በአመዛኙ በቅርብ ጊዜያት ወቅት በሊጉ የሰሩ አሰልጣኞች ቢሆንም ይህ ያልተፃፈ ህግ እንዳለሆነና በሊጉ ያልሰሩ ነገርግን ለቡድናቸው አጠቃላይ የወደፊት እቅድ የሚስማማ አሰልጣኝን አወዳድረው ሲቀጥሩ ይስተዋላል።

ነገሩን የባሰ የሚያደርገው ደግሞ አሰልጣኞቹ በአጭር ጊዜ የውል ስምምነት እንደመቀጠራቸው በዓመቱ መጨረሻ በክለቡ አውድ ውጤታማ የውድድር ዘመን ለማሳለፍ ያግዙናል የሚሏቸውን “የበቁ” ተጫዋቾች በከፍተኛ ቁጥር እና ዋጋ ማስፈረማቸው፤ ነገር ቡድኖቹን በብዙ ሲለዋወጡና ከዓመት ዓመት በሽግግር ውስጥ እንዲያሳለፉ ሲገደዱ ይስተዋላል በመሆኑም ክለቦች ሰከን ብለው አካሄዳቸውን ሊመረምሩ ይገባል።

👉 ተጋጣሚን ማጥናት

ዘመናዊ አሰልጣኞች ለጨዋታዎች ቡድናቸውን በማዘጋጀት ሒደት ውስጥ በቡድናቸው ላይ ከሚያደርጉት ትኩረት ባልተናነሰ ተጋጣሚዎቻቸውን ለማጥናት ከፍ ያለ ትኩረትን ይሰጣሉ። በሀገራችን ግን በተወሰነ መልኩ በአንዳንድ ክለቦች ይህን የሚያደርጉ ባለሙያዎችን ጭምር በመቅጠር ይህንን ወሳኝ የጨዋታ ዝግጅት ሒደትን ለማካተት ጥረት ሲደረግ ይስተዋላል።

የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር እና በአሁኑ ወቅት ባህር ዳር ከተማን በማሰልጠን ላይ የሚገኙት አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ወልቂጤ ከተማ ከአዳማ ከተማ ጋር ያደረጉትን ጨዋታ ለመታደም ወደ ሜዳ በተገኙበት አጋጣሚ በተለያዩ ቅፅበቶች የቡድኖቹን የጨዋታ እንቅስቃሴ የሚያሳዩ የተለያዩ ምስሎችን ለማስቀረት ጥረት ሲያደርጉ ታዝበናል። ይህም አሰልጣኞች በአይናቸው ብቻ ባስተዋሉበት ልክ ለቀጣይ ጨዋታዎች ቡድኖቹን ሲገጥሙ ሊረዷቸው የሚችሉ ግብዓቶን በመሰብሰብ ሂደት በምስል የተደገፉ ማስረጃዎች ይበልጥ ከጨዋታው በኋላ እንቅስቃሴዎቹን በምልሰት እና በትኩረት ለማጤን ከመርዳቱ ጋር በተያያዘ የእሳቸው ተሞክሮ ይበል የሚያሰኝ ሆኖ አግኝተነዋል።

👉 ዮሐንስ ሳህሌ የተለየ ሙከራ

ከባለፉት ቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሆነ የተለያዩ ክለቦች በማሰልጠን የማንውቃቸው እና አሁን ላይ ደግሞ ወደ ሊጉ አዲስ ያደገው መከላከያን በማሰልጠን ላይ የሚገኙት አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ከሌሎች የሊጉ አሰልጣኞች በተለየ መንገድ ተጫዋቾችን በተለያየ የመጫወቻ ቦታ ላይ የሞከር (Expermient) የማድረግ ልምድ እንዳለቸው በተለይ በወልዋሎ በነበራቸው ቆይታ የታዘብነው እውነታ ነበር።

በወልዋሎ ቆይታቸው በርከት ያሉ የቡድኑ ተጫዋቾችን (ምስጋናው ወ/ዮሐንስ ፣ ገናናው ረጋሳ ፣ ካርሎስ ዳምጠው ፣ ብሩክ ሰሙ ፣ ራምኬል ሎክ ፣ አቼምፖንግ አሞስ ፣ ሳሙኤል ዮሐንስ) ከተፈጥሮአዊ ቦታቸው ውጪ በተለያዩ አዳዲስ ሚናዎች በማጫወት የሚታወቁት አሰልጣኝ ዮሐንስ ዘንድሮም ይሄን ነገር ዳግም ያስመለክቱን ይሆን የሚለው ነገር ይጠበቅ ነበር።

አሁን በያዙት የመከላከያ ስብስብም ውስጥ አርባምንጭ ከተማን ሲገጥሙ ሁለቱ የመስመር ተከላካይ በመሆን ጨዋታውን የጀመሩት ገናናው ረጋሳ እና ዳዊት ማሞ ከተለያዩ ሚናዎች ወደ መስመር ተከላካይ ተስበው የሚጫወቱ ሲሆን በጨዋታውም የመሐል አማካዩ ግሩም ሀጎስን በመስመር አማካይነት እንዲሁም ተቀይሮ የገባው የመስመር አጥቂውን አዲሱ አቱላን በአማካይነት ሲጠቀሙት አስተውለናል።

እርግጥ ቡድኑ ሽግሽግ በሚደረግባቸው የሜዳ ክፍሎች ተፈጥሯዊ ተጫዋቾች በሙሉ ጤንነት በስብስቡ እየተገኙ ከእነዚህ የሚና መሸጋጎች በስተጀርባ ያሉ ታክቲካዊ ለውጦች ለመረዳት አስቸጋሪ ሆነው ብንመለከትም አሰልጣኙ በቅድመ ውድድር ዳሰሳችን ላይ አፅዕኖት ሰጥተው ወናግረውት እንደነበረው ሁሉ እነዚህ ተገማች ያልሆኑ ሽግሽጎችን እያደረጉ ይቀጥላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

👉 ቁንጥንጡ መሳይ ተፈሪ

አርባምንጭ ከተማን ይዞ ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊግ የተመለሰው የቀድሞው የወላይታ ድቻ እንዲሁም ለአጭር ጊዜያት ቢሆንም የፋሲል ከነማ አሰልጣኝ የነበሩት መሳይ ተፈሪ በመጀመሪያ የሊጉ ጨዋታ ቡድናቸውን ሲመሩበት የነበረው መንገድ እጅግ አስገራሚ ነበር።

ወጣቱ አሰልጣኝ በሜዳው ጠርዝ ቡድኑን ሲመሩ ከፍ ባለ ስሜት እየተቁነጠነጡ እና የቡድኑን ተጫዋቾች በአንዳንድ የጨዋታ ቅፅበት አብሯቸው በመሮጥ በሚመስል እንቅስቃሴ ጨዋታውን ከዳር ሆነው ይመሩበት የነበረበት መንገድ አስገራሚ አለፍ ሲልም አዝናኝ የነበረ የመጀመሪያ ሳምንት አጋጣሚ ነበር።

አሰልጣኝ መሳይ በስሜት ቡድናቸውን ሜዳ ጠርዝ ላይ ሆነው ከመምራት ባለፈ ከጨዋታዎች በኋላ በሚሰጣቸው ግልፅነት በተሞላባቸው አስተያየቶች እና የራሳቸው የሆነ የተለየ መገለጫ ያላቸውን ቡድን በመገንባት የሚታወቁ አሰልጣኝ ናቸው። በሊጉም በዘንድሮ የውድድር ዘመን የተለየ ነገር ያስመለክቱናል ብለን ከምንገምታቸው አሰልጣኞች በቀዳሚው ተርታ ይመደባሉ።

👉 የዝላትኮ ክራምፖቲች አስተያየት

የሳምንቱ የመጨረሻ የነበረው የሰበታ ከተማ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ደካማ እንቅስቃሴ ከታየባቸው ጨዋታዎች አንዱ ነበር። በእርግጥ በተለያዩ ምክንያቶች ተጫዋቾችን መጠቀም ሳይችል ለቀረው ሰበታ ከተማ ውጤቱ የሚያስከፋ አልነበረም። የአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራውም አስተያየት ይህንኑ የሚጠቁም ነበር። የአዲሱ የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ዝላትኮ ክራምፖቲች አስተያየት ግን ግራ የሚያጋባ ነው።

አሰልጣኙ በአስተያየቶቻቸው የተጫዋቾቻቸውንም ሆነ የእስካሁኑ የቡድን ሥራቸውን በይፋ መተቸት ከማይመሩጡ አሰልጣኞች መሀል መሆናቸውን የሚጠቁም አስተያየትን መስጠትን መርጠዋል። በውድድር ዓመቱ ተጠባቂ ከሆኑ ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ የጨዋታ ብልጫ ከመውሰድም ሆነ ሙከራዎችን ከማድረግ አንፃር ይህ ነው የሚባል ጠንካራ አቋም አላሳየም። ቡድኑ ተጠናክሮ እንደሚመጣ ከመጠበቁ አንፃር ከዚህ የተሻለ ጥንካሬ እንደሚኖረው ይገመት ነበር። ያም ቢሆን አሰልጣኙ ከውጤቱ ባሻገር ቡድናቸው የተጫወተበት መንገድ እና ያደረገው ጥረት እንዳስደሰታቸው መናገራቸው ትኩረት ሳቢ ነበር።