ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፬) – ሌሎች ጉዳዮች

የጨዋታ ሳምንቱ ዐበይት ጉዳዮችን የምንዘጋው በተከታዩ ፅሁፍ ይሆናል።

👉 የእግርኳስን በጎ ተፅዕኖ የመጠቀም ፍላጎቶች

እግርኳስ በሜዳ ላይ በሁለት ቡድኖች በሜዳ ላይ ከሚደረግ ፉክክር ባለፈ ፈርጀ ብዙ ትሩፋቶች እንዳሉት ይታወቃል፤ ከትሩፋቶቹ ተጠቀሚ ለመሆን ተቸግሮ የቆየው እግርኳሳችን በሂደት ከመሰል ጥቅሞች ለመቋደስ ጥረቶች ሲደረጉ እያስተዋልን እንገኛለን።

ዐምና ውድድሩ በቴሌቪዥን ሽፋን የማግኘቱ እና እግርኳሱ በራሱ ማመንጨት ከጀመረው ገንዘብ ክለቦች ተጠቃሚ የሚሆኑበት አግባብ መፈጠሩ እንደ አንድ በጎ እርምጃ የተወሰደ ተግባር ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ ውድድሩ በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ሽፋን ማግኘቱን ተከትሎ የሚገኘውን ተደራሽነቱን (Visibility) ለመጠቀም የተደረጉ በጎ ጅማሮዎችን ተመልክተናል።

ወልቂጤ ከተማዎች በመለያቸው የግራ እጀታውን በኢትዮጵያ የሰንደቅ ዓላማ ቀለሞች እንዲሁም በላዩ ላይ “Visit Ethiopia” የሚል ፅሁፍ በማስፈር በቴሌቪዥን መስኮት እና በተለያዩ መንገዶች የጨዋታውን ሁነት ለሚከታተሉ አካላት ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ መልዕክታቸውን ለማስተላለፍ እያደረጉ የሚገኙት ጥረት (ከሚመለከተው አካል ጋር በጉዳዩ ላይ በቅድሚያ ንግግር ማድረግ ተገቢ ቢሆንም) የሚበረታታ ሲሆን በተመሳሳይ ሌላኛው የሊጉ ተካፋይ የሆኑት ድሬዳዋ ከተማዎች እንዲሁ በተመሳሳይ በመለያቸው የግራ እጀታ ክፍል ላይ ድሬዳዋ ከተማን የሚያስተዋውቅ “City of Love & Peace” የሚል ፅሁፍ የሰፈረበትን መለያ ለብሰው ጨዋታቸውን ሲያደርጉ ተስተውሏል።

እርግጥ በክለቦች መለያ ላይ የሚገኙ ክፍት ቦታዎችን የፕሪምየር ሊጉን ደንብ ባልጣሰ መልኩ ክለቦች ከተለያዩ ተቋማት ጋር የውል ስምምነት በመፈፀም ወደ ገቢ ምንጭነት የመቀየር ቀሪ የቤት ስራ ቢኖርባቸውም ቦታዎቹ ክፍት ከሚሆኑ መሰል በቀጥታ ወይንም በተዘዋዋሪ ከክለቦች ማኅበራዊ ኃላፊነት ለመወጣት የሚያግዙ መልዕክትን ለማስተላለፍ መጠቀማቸው የሚበረታታ ነው።

👉 የደጋፊዎች በተሻለ ቁጥር ወደ ሜዳ መመለስ እና ተያያዥ ጉዳዮች

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በ2012 የውድድር ዘመን የኮሮና ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ ውድድሮች ተቋርጠው ዳግም ዐምና መደረግ ከጀመሩበት ወቅት አንስቶ እጅግ ውስን ቁጥር ያላቸው ደጋፊዎችን ቁጥር በስታዲየሞች ስንመለከት ቆይተናል።

ታድያ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ግን የሊግ አክሲዮን ማኅበሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ መክሮ ጨዋታዎች በሚደረግባቸው ስታዲየሞች ውስጥ ስታዲየሞቹ ማስተናገድ ከሚችሉት የደጋፊዎች ቁጥር ውስጥ 1/4 (ዘጠኝ ሺህ ደጋፊዎች) የሚሆኑት ወደ ሜዳ እንዲገቡ መፈቀዱን ተከትሎ ከቀደሙት አንፃር በርካታ ቁጥር ያላቸው ደጋፊዎች በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም እየተመለከትን እንገኛለን።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ሌላኛው ጉዳይ በደጋፊዎች መካከል ያለው የትኬት ኮታ ጉዳይ ነው። በአወዳዳሪው አካል በተገለፀው መሠረት 70% የሚሆነው ትኬት ለባለሜዳው እንዲሁም የተቀረው 30% ለተጋባዥ ቡድን ደጋፊዎች ስለመሆኑ በግልፅ ቢያትትም በአንዳይድ ጨዋታዎች ግን ይህ ሲሆን አልተመለከትንም። በተለይም በኢትዮጵያ ቡና እና ሲዳማ ቡና ባገናኘው ጨዋታ ባለ ሜዳ የነበረው ቡድን ኢትዮጵያ ቡና ቢሆንም እንግዳው ቡድን ሲዳማ ቡና ከኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በላቀ ቁጥር ደጋፊዎችን ወደ ሜዳ ማስገባቱን ተመልክተናል።

አወዳዳሪው አካል ሆነ ሌሎች ላወጧቸው ደንቦች ተገዢ መሆን የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ግዴታ መሆኑን ተገንዝበው መሰል ለቅሬታ በር የሚከፍቱ አሰራሮችን ከወዲሁ ማስወገድ ይኖርባቸዋል።

👉 የመጫወቻ ሜዳ ጉዳይ

ለእግርኳስ ጨዋታ መሰረታዊ ከሚባሉት ነገሮች አንዱ እና ዋነኛው የመጫወቻ ሜዳ እንደሆነ ይታወቃል። ነገር በሀገር የእግርኳስ አስተዳደር አካላት ጋር ያለው ግንዛቤ ግን ከዚህ በተቃራኒ የቆመ ይመስላል።

በሀገራችን አውድ እርግጥ የጥራት ጉዳይ ጥያቄ ቢነሳባቸውም የአርማታ ሙሌት ውጤት ለሆኑት መቀመጫዎች (Civil Work) ሥራዎች በሚሰጠው ትኩረት ሩቡን ያክል ለመጫወቻ ሜዳ ሳሮቹ አይሰጥም ቢባል ማጋነን አይሆንም። የመጫወቻ ሜዳዎቹን አረንጓዴያማ ገፅታ ከማልበስ ባለፈ ለጨዋታ ምቹ ከማድረግ ጋር በተያያዘ ሰፊ ክፍተቶች ይስተዋላል።

የውድድሩ የመጀመሪያ ምዕራፍ ዘጠኝ የጨዋታ ሳምንትን የማስተናገድ እድሉን ያገኘው የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ገና ከወዲሁ የሳሩ ሁኔታ ጥያቄዎች እየተነሱበት ይገኛል። ዐምና በተወሰኑ የሜዳ ክፍሎች የተወሰኑ የአሸዋ ልጥፎችን ስንመለከትበት የነበረው የመጫወቻ ሜዳው ዘንድሮ ደግሞ የሳሮቹ የቁመት መጠን በተወሰነ መልኩ ከፍ ከፍ ማለቱን ተከትሎ ለቡድኖች የኳስ ቅብብል ፈተና ሲሆን እየተመለከትነው እንገኛለን።

ሌላኛው ከሜዳው ጋር የሚነሳው ጉዳይ በሀዋሳ እና በአካባቢ በአሁኑ ወቅት ካለው እጅግ የከረረ ፀሀይ ጋር በተያያዘ የመጫወቻ ሜዳው እና ሳሩ በጣም ደረቅ በመሆናቸው የተነሳ ተጫዋቾች በጨዋታ እንቅስቃሴ ወቅት በንክኪዎች ለመውደቅ በሚዳረጉበት ወቅት የተለያዩ የሰውነት ክፍሎቻቸው ሲጋጋጡ በተደጋጋሚ እያስተዋልን እንገኛለን በተለይ የጅማ አባጅፋሩ ወጣቱ አጥቂ መሐመድኑር ናስር በፀጋሰው ድማሙ ተገፍቶ ወደቀበት ቅፅበት ያጋጠመው የእጅ መገሽለጥ ተጠቃሽ ጉዳት ነበር።

በጥቅሉ በከፍተኛ ጉጉት በተጠበቀው የመክፈቻ የጨዋታ ሳምንት የተመለከትን አጠቃላይ የመጫወቻ ሜዳ ሁኔታ አመርቂ የሚባል አይደለም በመሆኑም የሚመለከተው አካል የሳሮቹን ቁመት ሆነ ሜዳው ከጨዋታ መጀመር አስቀድሞ በተወሰነ መልኩ የሚያገኝበትን አግባብ በመፍጠር የመጫወቻ ሜዳውን በተወሰነ መልኩ እርጥበታማ በማድረግ ለጨዋታ ምቹ የማድረግ ሀላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።

👉 የትኬት ሽያጭ ጉዳይ

በአዲሱ የውድድር ዘመን አንደኛው አዲሱ ነገር የደጋፊዎች ወደ ሜዳ መመለስ ሆኗል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የመጀመሪያው የጨዋታ ሳምንት ግን የተወሰኑ ያልተጠናቀቁ ነገሮች መኖራቸውን ተከትሎ ከትኬት ሽያጭ ጋር በተያያዘ የተወሰኑ እንግልቶች እንደነበሩ ለማስተዋል ችለናል።

በ2012 14ኛው የአዲስአበባ ከተማ ዋንጫ የቀደመውን የእጅ በእጅ የትኬት ሽያጭን በማስቀረት በዘመናዊ መንገድ ባንክን እንዲሁም የበይነ መረብ መተግበሪያዎችን በመጠቀም ተደረገው አመርቂ ሙከራ በተሰረዘው የ2012 የውድድር ዘመን በሊጉ ተግባራዊ ለማድረግ ጥረቶች ተደርገዋል። የሊግ አክሲዮን ማህበሩም ይህን አዲስ ልምምድ ዘንድሮ የደጋፊዎችን ወደ ሜዳ መመለስን ተከትሎ ለማስቀጠል ጥረት እያደረገ ይገኛል።

በበይነ መረብ ይሸጣል ተብሎ ተገልፆ የነበረው የጨዋታ ትኬቶች ነገር ባጋጠመ የቴክኒክ እክል ምክንያት ወደ ቀደመው የእጅ በእጅ ሽያጭ የተመለሰበትን ሒደት አስተውለናል። ይህም ቴክኒካዊ እክል በቅርቡ በተናጠቀቀው የዘንድሮ የአዲስአበባ ከተማ ዋንጫ ላይም የበይነ መረብ ግብይቱ እንዳይሳለጥ ማነቆ እንደነበር አይዘነጋም። በመሆኑም ይህንን ልምምድ ይበልጥ በፈጠነ እና በተሻለ መንገድ መጠቀም ከታለመ አገልግሎቱን ለማቅረብ ስምምነት ከፈፀሙ አካላት ጋር ትኩረት ተሰጥቶ ለመቅረፍ የተጠናከሩ ጥረቶች መደረግ እንዳለበት እናስገነዝባለን።

ችግሩንም በጊዜያዊነት ለመቅረፍ የጨዋታዎች ትኬት በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ መግቢያ እና በቅርበት በሚገኙ አካባቢዎች ማድረግ እየተቻለ ትኬቶቹ በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት እስከ አመሻሽ አስራ አንድ ሰአት ድረስ እንዲሸጥ እየተደረገ ይገኛል። ይህም ሒደት ተመልካቾችን ለእንግልት ብሎም ለሀሰተኛ ትኬቶች ምርት እና የትኬቶች የጥቁር ገበያ ሽያጭ በር የሚከፍት ከመሆኑ ጋር በተያያዘ በአፋጣኝ መስተካከል ይኖርበታል።

👉 የተሻሻለው የሊጉ መለያ እና መግቢያ ሙዚቃ

ባሳለፍነው የውድድር ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ የቴሌቪዥን ሽፋን በግዙፉ የክፍያ ቴሌቪዥን ኔትወርክ ያገኘው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ የውድድር ዘመን ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የተወሰነ ውስንነቶች እንደነበሩበት አይዘነጋም። ከእነዛም መካከል የሊጉ መለያን እና የሊጉ የመግቢያ ሙዚቃ በተወሰነ መልኩ ጥያቄዎች ያስነሱ ነበሩ።

ሊጉ በመጀመሪያ የውድድር ዘመኑ ይጠቀምበት የነበረው ይፋዊ መለያው (Logo) በተመሳሳይ የስያሜ መብት ባለቤት ከተያዘው የኬንያ ፕሪምየር ሊግ በይዘት መመሳሎች መኖራቸውን ተከትሎ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ይቀርቡቀበት እንደነበር አይዘነጋም። ይህን ጉዳይ ምላሽ ለመስጠት ያሰበው የሊጉ አክሲዮን ማህበርም ራሱ ይጠቀምበት የነበረውን መለያ ከተወሰኑ ማሻሻያዎች ጋር የሊጉ ይፋዊ መለያ እንዲሆን ተደርጓል።

በተመሳሳይ ዐምና የሊጉ የመግቢያ ሙዚቃ ሆኖ ሲያገለግል የነበረውን ሙዚቃም ዘንድሮ ተቀይሯል። ከኢትዮጵያዊ የሙዚቃ ስሜት ወጣ ያለ የነበረው ሙዚቃ ከሊጉ ጋር ዝምድና በሌለው አንድ በቀጥታ ሽፋን በሚሰጠው ተቋም በሚተዳደሩ ቻናሎች ውስጥ የአንድ ድርጅት ማስታወቂያ የማጀቢያ ሙዚቃ የሆነው ይህ ዜማም ዘንድሮ ይበልጥ ለኢትዮጵያዊያን ጆሮ ቀረብ ባለ አዲስ ዜማ ተተክቷል።

ኢትዮጵያ ዜማ እና ኢትዮጵያ የሙዚቃ መሳሪያዎች ጥቅም ላይ በዋሉበት በአዲሱ የሊጉ ይፋዊ ሙዚቃ በተወሰነ መልኩ በእግርኳሳዊ ሜዳዎች ላይ ጥቅም ላይ ከሚውሉ ሙዚቃዎች አንፃር ቀዝቀዝ ያለ ሙዚቃዊ ይዘት ያለው ሲሆን ሌላው የሙዚቃ ዜማዎች የመወራረስ ባህሪ እንዳላቸው ቢታመንንም አዲሱ የሊጉ ይፋዊ ሙዚቃ ግን አብዛኛው የዜማ ክፍሎች በሊጉ ባለመብት ኩባንያ ስር በሚሰራው የሀገር ውስጥ መዝናኛ ቻናል ላይ ለጊዜውም ቢሆን አሁን ላይ እይታ ላይ ከማይገኝ አንድ ተከታታይ ድራማ የማጀቢያ ሙዚቃ ጋር ግን በጣም እንደሚመሳሰል መናገር ይቻላል።

ሁሉም ነገር በአንድ ጀንበር አይስተካከልምና አክሲዮን ማህበሩ ከዘመን ጋር የተጣጣመ የማይመስለውን መለያውን እንዲሁም በመዚቃ ይዘትም ሆነ በሌሎች መመዘኛዎች ከፍ ያለ ሙዚቃን በሂደት ያስደምጡናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።

👉 በመረጃ እጥረት ስታዲየም ቀድመው የደረሱት ወልቂጤዎች

የዘንድሮ የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የጨዋታ ሰዓቶች በወጥነት እንዳልተቀመጡ ይታወቃል። በተለይ የጨዋታ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታዎች 8 አልያም 9 ሰዓት እንዲደረጉ የተዘበራረቀ መርሐ-ግብር ወጥቷል። የመጀመሪያ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታው 8 ሰዓት ሲደረግ ከሁለተኛ ቀን ጀምሮ ያሉት የመጀመሪያ ጨዋታዎች ደግሞ 9 ሰዓት ተደርገዋል። ይህንን ወጥ ያልሆነ መነሻ ያደረገ በሚመስል ስህተትም ወልቂጤ ከተማዎች በመጀመሪያ ሳምንት የሁለተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ከአዳማ ከተማ ጋር ለማድረግ 9 ሰዓት ቀጠሮ ቢያዝላቸውም ጨዋታው 8 ሰዓት የሚደረግ መስሏቸው በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም እጅግ ቀድመው (ከ7 ሰዓት በፊት) ደርሰዋል።

ድረ-ገፃችን ባደረገችው ማጣራት የቡድኑ አባላት የሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ 8 ሰዓት በመደረጉ የሁለተኛ ቀን ጨዋታውም በተመሳሳይ ሰዓት የሚደረግ መስሏቸው እንደሆነ ሰምተናል። ምንም ቢሆን ግን ይህንን ጉዳይ በሚገባ ማጣራት እንደነበረባቸው የሚታመነው የክለቡ የቡድን መሪ በቅድመ ጨዋታ ላይ ሰዓቱን በሚገባ አለማጣራታቸው ትኩረትን ስቧል። የቡድኑ አባላትም የጨዋታ ሰዓቱ 8 ሰዓት መስሏቸው ሜዳ ቀድመው ከደረሱ በኋላ አገልግሎት የሚሰጣቸው አካል አጥተው ዳግም ወደ መኪናቸው በማምራት ሰዓቱን መጠባበቅ ይዘው እንደነበር አስተውለናል።

👉 የአዳማ ከተማ በውሰት ወጌሻ ማምጣት

በአሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመሩት አዳማ ከተማዎች በሳምንቱ መጀመሪያ ከወልቂጤ ከተማ ጋር የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ጨዋታ አድርገው ነጥብ ተጋርተዋል። በጨዋታው ደግሞ የቡድኑ የህክምና ባለሙያ (ወጌሻ) ሆነው የታዩት በባህር ዳር ከተማ ሥር የሚታወቁት አቶ ኢሳይያስ ናቸው።

በእግርኳሱ ዓለም ተጫዋቾች በውሰት ከአንድ ክለብ ወደ ሌላ ክለብ ሲዘዋወር ማየት የተለመደ ነው። ይህ የውሰት እንቅስቃሴ ደግሞ ደግሞ በተለየ ሁኔታ በባህር ዳር እና አዳማ ከተማ ቡድኖች ውስጥ ታይቷል። እንደገለፅነው የባህር ዳር ከተማው ወጌሻ አቶ ኢሳይያስ ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ለዋና ክለባቸው እና ለአዳማ ከተማ በሜዳ ላይ ግልጋሎት ሲሰጡ አስተውለናል። ይህ እንዴት ሆነ ብለን ስንጠይቅም የአዳማ ከተማው ወጌሻ የሆኑት አቶ ዮሐንስ በህመም ምክንያት ለክለባቸው ግልጋሎት መስጠት ባለመቻላቸው ከክለቡ አሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ጋር ለሁለት ዓመትታ በጣና ሞገዶቹ ቤት የሰሩት አቶ ኢሳይያስ በውሰት ለአዳማ ከተማ ግልጋሎታቸውን ለግሰዋል።

👉 የሊጉ አሸናፊ ሚካኤል ወልደሩፋኤል በተንታኝነት ብቅ ማለት

የኢትዮጵያን ትልቁን የሊግ እርከን ከፍተኛ ወጪ በማውጣት የምስል መብት የገዛው ዲ ኤስ ቲቪ ዓምና እምብዛም በሀገራችን ባልተለመደ የጥራት ደረጃ እያንዳንዱን የሊጉን ጨዋታዎች በቀጥታ ስርጭት ለስፖርት ቤተሰቡ ሲያደርስ ነበር። ጨዋታዎቹ ህይወት ኖሯቸው እንዲተላለፉ ደግሞ የሀገር ውስጥ እና የውጪ ኮሜንታተሮችን እና ተንታኞችን ሲጠቀም ነበር። በተለይ በአማርኛ አማራጩ ከተወሰኑ ጨዋታዎች ውጪ በሙያው ልምድ ያላቸው የሀገራችንን ጋዜጠኞች ሲጠቀም እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።

በልዩ ይዘት ዘንድሮ በተጀመረው የሊጉ ውድድር ደግሞ ሙሉ በሙሉ የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ሽፋን እንደሚያገኝ ሲገለፅ የተንታኞች ለውጥም መደረጉ ታውቋል። በዚህም ከጨዋታ ኮሜንታተሮች እና የሜዳ ላይ መሪዎች ጎን የቀድሞ ተጫዋቾችን እንደሚጠቀም ሰምተናል። በመጀመሪያ ሳምንት የሊጉ 8 ጨዋታዎችም የቀድሞ የሀዋሳ ከተማ ወሳኝ የመስመር ተጫዋች የነበረው ሚካኤል ወልደሩፋደኤል በተንታኝነት ከሚዲያ ከጠፋበት ብቅ እንዲል ተደርጓል። ይህ ሂደትም በቀጣዮቹ ጊዜያትም በወጥነት እንደሚቀጥል ተጠቁሟል።

👉 የፓውዛ መብራት መሻሻል እና አቅም የከዳውን የመዓዘን ባንዲራ የመተካት እንቅስቃሴ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር እና የውድድሩ የስያሜ እና የምስል መብት ባለቤት ዲ ኤስ ቲቪ የሊጉ ጨዋታዎች ከዓምናው በተለየ ከሰዓት እና ምሽት እንዲከናወኑ ማድረጋቸው ይታወቃል። ይህንን ተከትሎ ጨዋታዎች ምሽት ላይ ለቀረፃ ምቹ እንዲሆኑ የመብራት ፓውዛዎችን ብቁ የማድረግ ስራ ሊጉ ከመጀመሩ በፊት ሲከወን ሰንብቷል። ይህ ቢሆንም ግን ሊጉ የተጀመረበት የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ጥንቅቅ ብሎ ለእይታ አልበቃም ነበር። በተለይ በግራ ከማን አንሼ መቀመጫ በኩል የሚገኘው ፓውዛ በመጀመሪያው ጨዋታ እምብዛም ሀይል እንዳልነበረው አስተውለናል። ይህንን ክፍተት የታዘቡት የዩኒቨርስቲው የሊግ ካምፓኒው አመራሮች ጉዳዩን በቶሎ በማረም በማግስቱ ለተከናወነው ጨዋታ ዝግጁ አድርገውታል።

ይህ ብቻ ሳይሆን በሁለተኛው የጨዋታ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ ከመጀመሩ በፊት በተመሳሳይ በግራ ከማን አንሼ በኩል የሚገኘው የመዓዘን ባንዲራ መያዧ ቋሚ የመሰበር አደጋ አጋጥሚት የጨዋታ ጊዜ በሰከንዶች እንዲዘገይ አድርጓል። እንደ ምንም ተተክሎ የጀመረው ጨዋታው ላይም በተመሳሳይ የዩኒቨርስቲው እና የሊግ ካምፓኒው የውድድር አመራሮች ፈጣን ምላሽ በመስጠት በደቂቃዎች ውስጥ አዲስ መቆሚያ እና ባንዲራ መጥቶ እንዲተካ በማድረግ ክፍተቱን አርመዋል። ይህ ለክፍተቶች ፈጣን ምላሽ የመስጠት እንቅስቃሴም ይበል የሚያሰኝ መሆኑን መጠቆም እንፈልጋለን።

👉 አሳዳጊ አባት እና ልጅ በአንድ ጨዋታ

አዳማ ከተማ እና ወልቂጤ ከተማ በተጫወቱበት መርሐ-ግብር ሌላ ትኩረት የሳበ አጋጣሚ ተፈጥሯል። ይህም የአሳዳጊ አባት እና ልጅ ጥምረት ነው። ይህንን ጨዋታ በኮሚሽነርነት ለመምራት የቀድሞው ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ፍቃዱ ጥላሁን ተመድበው ሜዳ ደርሰዋል። በአዳማ በኩል ደግሞ በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ የገባው አቡበከር ወንድሙ በተጫዋችነት ለመሳተፍ ሜዳ ቀርቧል። የሚገርመው የጨዋታው ኮሚሽነር ፍቃዱ ጥላሁን ያሳደጉት አዲሱ የአዳማ ከተማ የመስመር አጥቂ አቡበከር ወንድሙን ጨዋታ ለመምራት መመደባቸው አስገራሚ ግጥምጥሞሽን ፈጥሯል።

(በቅድሚያ በነበረው ፅሁፍ ላይ ኮሚሽነር ፍቃዱ የአቡበከር ወላጅ አባት የሚለው በስህተት በመሆኑ አሳዳጊ በሚለው እንደስተካከል እንዲሁም ወንድሙ የአጎቱ ሳይሆን የወላጅ አባቱ ስም መሆኑን እየገለፅን ለተፈጠረው የመረጃ መፋለስ ተጫዋቹን እና ኮሚሽነሩን ይቅርታ እንጠይቃለን)

ያጋሩ