ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ – የአንደኛ ሳምንት ቁጥሮች እና ዕውነታዎች

የ2014 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በተደረጉ ስምንት የአንደኛ ሳምንት ጨዋታዎች ተጀምሯል። በጨዋታዎቹ ላይ የተመዘገቡ ቁጥራዊ መረጃዎች እና እውነታቸዎችም እንዲህ ቀርበዋል።

የመጀመርያዎቹ

በአንደኛ ሳምንት በተደረጉ ጨዋታዎች አመዛኞቹ ዐበይት ክስተቶች ተመዝግበዋል።

– ጎል – የሀዋሳ ከተማው መስፍን ታፈሰ በ15ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው ጎል የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ጎል ሆኖ ተቆጥሯል።

– በአርባምንጭ ላይ ጎል ያስቆጠረው የመከላከያው ኦኩቱ ኢማኑኤል የመጀመርያ የውጪ ዜጋ ጎል አስቆጣሪ ሆኗል።

– ሐት ትሪክ – የፋሲል ከነማው አጥቂ ፍቃዱ ዓለሙ የ2014 የውድድር ዘመን የመጀመርያ ባለ ሐት ትሪክ ሆኗል። ዐምናም በተመሳሳይ የመጀመርያው ሐት ትሪክ የተመዘገበው በፋሲል ከነማ ተጫዋች ነበር (ሙጂብ ቃሲም)

– ፍፁም ቅጣት ምት – የአዳማ ከተማው ዳዋ ሆቴሳ የመጀመርያው ፍፁም ቃጣት ምት መቺ የነበረ ቢሆንም በወልቂጤው ሲልቪያን ግቦሆ ተመልሶበታል። ዐምናም በተመሳሳይ የመጀመርያው የፍፁም ቅጣት ምት (የበረከት ሳሙኤል ምት በፋሲል ገብረሚካኤል ተመልሷል) መምከኑ ይታወሳል።

በጎል ደረጃ የመጀመርያ የፍፁም ቅጣት ምት ጎል ሆኖ የተመዘገበው የፋሲል ከነማው ፍቃዱ ዓለሙ በሀዲያ ሆሳዕና ላይ ያሳረፈው ነው።

– ቢጫ ካርድ – የሀዋሳ ከተማው ኤፍሬም አሻሞ በ43ኛው ደቂቃ የዓመቱ የመጀመርያ የቢጫ ካርድ ሰለባ ሆኗል።

– ቀይ ካርድ – የጅማ አባ ጅፋሩ አማካይ ዳዊት እስጢፋኖስ የመጀመርያው ቀይ ካርድ የተመለከተ ተጫዋች ሆኗል።

– ራስ ላይ የተቆጠረ ጎል – የአዳማ ከተማው ዮሴፍ ዮሐንስ ያስቆጠረው ጎል የውድድር ዓመቱ በራስ ላይ የተቆጠረ የመጀመርያው ጎል ሆኗል።

የጎል መረጃዎች

– በዚህ ሳምንት በተደረጉ ስምንት ጨዋታዎች 12 ጎሎች ተቆጥረዋል። (በአማካይ 1.5 ጎል በጨዋታ)

– ከተቆጠሩት መካከል አንድ (ፍቃዱ ዓለሙ) በፍ/ቅ/ም ሲቆጠር አንድ ደግሞ በራስ ላይ (ዮሴፍ ዮሐንስ) ተቆጥሯል።

– ከ12 ጎሎች መካከል በክፍት እንቅስቃሴ ዘጠኝ ሲቆጠሩ ሦስቱ (ራስ ላይ ጨምሮ) የተቆጠሩት ከቆመ ኳስ ነው።

ዲሲፕሊን

– በዚህ ሳምንት በተደረጉ ስምንት ጨዋታዎች 38 ተጫዋቾች እና አንድ ምክትል አሰልጣኝ (ኢዮብ ማለ) የማስጠንቀቂያ ካርድ ተመዟል።

– አራት ተጫዋቾች (ዳዊት እስጢፋኖስ፣ ረመዳን የሱፍ፣ ኤፍሬም ዘካርያስ እና አንተነህ ተስፋዬ) የቀይ ካርድ ተመልክተዋል።

– በስድስት የቡድኑ አባላት ላይ የማስጠንቀቂያ ካርድ (እና አንድ ቀይ ካርድ )የተመዘዘበት ወልቂጤ ከተማ ከፍተኛው ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ፋሲል ከነማ፣ ባህር ዳር ከተማ፣ አዲስ አበባ ከተማ እና መከላከያ ዝቅተኛ ቁጥር (1) ያስመዘገቡ ናቸው።

የሊጉ አዲስ አዳጊ ቡድኖች እውነታዎች

– ሊጉ በአዲስ መልክ ከተጀመረ ወዲህ ሁሉም ነባር ቡድኖች ከረጅም ጊዜ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ አድርገዋል። (የ2012 የተሰረዘው ዓመት ሳይጨምር) በሊጉ ላለፉት ተከታታይ ስድስት ዓመታት ቢያንስ አንድ አዲስ ቡድን ሊጉን ሲተዋወቅ ቆይቶ በዘንድሮ የውድድር ዓመት ሦስቱም በሊጉ ከዚህ ቀደም የተሳተፉ ቡድኖች አድገዋል። ለመጨረሻ ጊዜ ይህ የሆነውም በ2005 የውድድር ዓመት (መድን እና ውሀ ስፖርት) ነበር።

– መከላከያ ከ27 ወራት በኋላ የመጀመርያ የሊግ ጨዋታውን አከናውኗል። ጦሩ ለመጨረሻ ጊዜ በፕሪምየር ሊጉ ጨዋታ ያደረገው ሰኔ 30 ቀን 2011 ከኢትዮጵያ ቡና ሲሆን 4-3 አሸንፎ ነበር።

– ኦኩቱ ኢማኑኤል በተመሳሳይ ከ27 ወራት በኋላ ጎል ያስቆጠረ የመከላከያ ተጫዋች ሆኗል። ለመጨረሻ ጊዜ ጎል ያስቆጠረው ተጫዋች የአሁኑ የፋሲል አጥቂ ፍቃዱ ዓለሙ ሰኔ 30 በተደረገው ጨዋታ በ72ኛው ደቂቃ ኢትዮጵያ ቡና ላይ ነበር።

– አርባምንጭ ከተማ ከ39 ወራት በኋለ ወደ ሀገሪቱ ትልቅ ሊግ ተመልሶ ጨዋታ አድርጓል። ሐምሌ 7 ቀን 2010 ፋሲል ከነማን በፍቃዱ መኮንን ጎል 1-0 ያሸነፈበት ጨዋታ በሊጉ ለመጨረሻ ጊዜ ያደረገው ጨዋታ ነበር።

– አዲስ አበባ ከተማ ወደ ሊጉ ተመልሶ ጨዋታ ሲያደርግ ከ52 ወራት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ነው። ለመጨረሻ ጊዜ ጨዋታ ያደረገው ሰኔ 17 ቀን 2009 በወላይታ ድቻ 1-0 በተሸነፈበት ጨዋታ ነበር።

የሳምንቱ ስታቶች
(መረጃዎቹ የተገኙት ከሱፐር ስፖርት ነው)

ኢላማ የጠበቀ ሙከራ

ከፍተኛ – ሲዳማ ቡና (7)
ዝቅተኛ – ሰበታ ከተማ (0)

ጥፋት

ከፍተኛ – ሲዳማ ቡና (26)
ዝቅተኛ – አዲስ አበባ ከተማ (11)

ከጨዋታ ውጪ

ከፍተኛ – ወላይታ ድቻ (9)
ዝቅተኛ – ሰበታ እና ሆሳዕና (0)

የማዕዘን ምት

ከፍተኛ – አዲስ አበባ ከተማ (11)
ዝቅተኛ – ቅዱስ ጊዮርጊስ (0)

የኳስ ቁጥጥር

ከፍተኛ – ኢትዮጵያ ቡና (61%)
ዝቅተኛ – ሲዳማ ቡና (39%)