ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ – የሶከር ኢትዮጵያ የአንደኛ ሳምንት ምርጥ 11

የሀገራችን ትልቁ የሊግ እርከን ባሳለፍነው ሳምንት መጀመሪያ ጅማሮውን ሲያደርግ በጨዋታዎቹ የታዩ ምርጥ ተጫዋቾችንም በዚህ መልክ ድረ-ገፃችን መርጣለች።

ግብ ጠባቂ

ዳግም ተፈራ (ሀዋሳ ከተማ)

በመጀመሪያ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች በአንፃራዊነት የተሻሉ የግብ ዘቦች ከነበሩት መካከል ወጣቱ የሀዋሳ ከተማ ግብ ጠባቂ ዳግም ተፈራ አንዱ ነው። ተጫዋቹ በቦታው ቀዳሚ ተመራጭ እንደሚሆን የሚታሰበው መሐመድ ሙንታሪ በስራ ፍቃድ ምክንያት አለመኖሩን ተከትሎ ያገኘውን የመሰለፍ ዕድል በጥሩ ብቃት በመጠቀም ቡድኑ ግብ እንዳያስተናግድ ሲጥር ታይቷል። እርግጥ ተጫዋቹ ብዙ ባይፈተንም ሁለት ያለቀላቸው አጋጣሚዎችን በጥሩ ቅልጥፍና ማዳኑ ለቡድኑ ድል የነበረው ዋጋ ከፍተኛ ነበር።


ተከላካዮች

ሰዒድ ሀሰን (ፋሲል ከነማ)

ባሳለፍነው የውድድር ዓመት እምብዛም የጨዋታ ዕድል ያላገኘው ሰዒድ በመጀመሪያው የጨዋታ ሳምንት ዕድል ካገኘ ምን አይነት ብቃት እንዳለው በሚገባ አሳይቷል። የቀኝ መስመር ተከላካዩ በአይደክሜ ብቃቱ መስመሩን ከላይ ታች ከመሸፈኑ በተጨማሪ ለግብ የሚሆኑ ተሻጋሪ ኳሶችን በመላክ ጥሩ የማጥቃት አማራጭ ለቡድኑ ሲሰጥ ታይቷል። ባለ ሀት ትሪኩ ፍቃዱ ዓለሙ ያስቆጠራት የመጀመሪያ ጎልም ከዚሁ የመስመር ተከላካይ መነሻን ያደረገች ነበረች።

ጊት ጋትኩት (ሲዳማ ቡና)

ቁመተ ረጅሙ ጊት ከአዲሱ የቡድኑ ፈራሚ ያኩቡ መሀመስ ጋር ጥሩ የመሀል ተከላካዮች ጥምረትን አሳይቷል። ሲዳማ እንደቡድን የኢትዮጵያ ቡናን የማጥቃት መስመሮች መዝጋት በቻለበት በዚህ ጨዋታ የጊት ብቃት ይበልጥ የተገለፀው ኳሶችን በማቋረጡ በኩል አልነበረም። ይልቁኑም ብዙ ጫና ያልነበረበት ተጫዋቹ የቡድኑን ቀጥተኛ የማጥቃት ምርጫ በተደጋጋሚ ያልተዛነፉ ረጃጅም ኳሶችን በቀጥታ ወደ ፊት በማድረስ ድንቅ ተሳትፎ ሲያደርግ አምሽቷል።

ሰለሞን ወዴሳ (ባህር ዳር ከተማ)

በተደጋጋሚ ጫና ተፈትኖ ያለፈ የመሀል ተከላካይ በብዛት ባልነበረበት የመጀመሪያው ሳምንት ሌላኛው ምርጫችን ሰለሞን ሆኗል። እንደጊት ሁሉ በአዲስ መልክ ከፈቱዲን ጀማል ጋር የተጣመረው ሰለሞን እንደነባር ተጫዋችነቱ ጥሩ እርጋታን ያሳየበትን ዘጠና ደቂቃ አሳልፏል። ይህ በመሆኑም ፍጥነት ላይ መሰረት ያደረገውን የተጋጣሚውን የማጥቃት ሂደት ያለብዙ ችግር ሲያቋርጥ ተመልክተነዋል። አዲስ አበባዎች በአመዛኙ በግራ አድልተው ሲያጠቁ ሰለሞን ለመሳይ አገኘሁ ጥሩ ሽፋን በመስጠት የባህር ዳር የቀኝ ወገን እንዳይሰበር በማድረግ ኃላፊነቱን ተወጥቷል።

ሚሊዮን ሰለሞን (አዳማ ከተማ)

ሁለገቡ ተጫዋች ሚሊዮን ኳስ በሚያገኝባቸው ቦታዎች ላይ የነበረው ለትክክለኝነት የቀረቡ ውሳኔዎች እና እንቅስቃሴዎች ምርጥ ቡድናችን ውስጥ እንድናካትተው አስችሎናል። ተጫዋቹ ክለቡ ከወልቂጤ ከተማ ጋር ነጥብ ሲጋራ የፍፁም ቅጣት ምት ማስገኘቱ (ምንም እንኳን ቢሳትም)፣ ጥሩ ጥሩ የግብ ዕድሎችን መፍጠሩ እና ግብ ማስቆጠሩ ያለ ጥርጥር የተሳካ የጨዋታ ቀን አሳልፎ ከሜዳ እንደወጣ የሚያመላክቱ ናቸው።


አማካዮች

ቴዎድሮስ ታፈሠ (ሲዳማ ቡና)

በሊጉ ያለ ግብ ከተጠናቀቁ ሁለት የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች መካከል አንዱ የሁለቱ ቡና ጨዋታዎች ነው። በዚህ ጨዋታ የአማካይ መስመሩ ላይ ታታሪነት የተሞላበት ብቃት ሲያሳይ የነበረው ተጫዋች ደግሞ የሲዳማ ቡናው አማካይ ቴዎድሮስ ታፈሰ ነው። ዳግም ከአሠልጣኝ ገብረመድህን ጋር የተጣመረው ተጫዋቹ ከሳጥን ሳጥን የመሮጥ ተነሳሽነቱ፣ ተከላካዮች እንዳይጋለጡ መታተሩ እና ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶችን ከእግሩ እንዲነሱ ማድረጉ የሚደነቅ ነበር።

ሱራፌል ዳኛቸው (ፋሲል ከነማ)

ለፍፁምነት የተጠጋ ብቃት ያሳየው እና በምርጥ ቡድናችን ያካተትነው ሌላኛው ተጫዋች ደግሞ ሱራፌል ዳኛቸው ነው። ሻምፒዮኖቹ ዓምና ከቆሙበት ሲቀጥሉ በምርጥ ብቃቱ አብሮ የቀጠለው አማካዩ ሱራፌል ነው። ቡድኑ ሀዲያ ሆሳዕናን 3-1 ሲረታ የብዙ ነገሮች መነሻ የሆነው ተጫዋቹ አንድ ግብ የሆነ ኳስ ሲያቀብል ሌላ ግብ ለሆነ ኳስም መነሻ ሆኗል። በአጠቃላይ የቡድኑ የማጥቃት የልብ ምት ሆኖ ያመሸው ተጫዋቹ የሳምንቱ ምርጥ ቡድናችን ውስጥ ቦታ አግኝቷል።

ፍፁም ዓለሙ (ባህር ዳር ከተማ)

እንደ ሱራፌል ሁሉ ከዓምና ብቃቱ ሳይቀንስ የመጣው ፍፁምም ቡድኑ ሦስት ነጥብ እና ጎል ከአዲስ አበባ ሲሸምት ምርጥ ነበር። ቡድኑን በአምበልነት እየመራ ወደ ሜዳ የገባው ተጫዋቹ ሌሎች ለተከላካዮች የራስ ምታት የሚሆኑ ተጫዋቾች አብረውት መሰለፋቸው እንደ ዓምና የትኩረቶች መሐከል ሆኖ ሜዳ ላይ እንዲቀርብ አላደረገውም። ይህንን ተከትሎ ተጫዋቹ በከፍተኛ ነፃነት ወደ ኋላ እየተሳበ ኳሶችን ሲቀበል፣ ወደ መስመር እየወጣ የተጫዋቾች ክምችት ሲፈጥር (Over load) እና በመስመሮች መካከል እየተገኘ አፈትላኪ ሩጫዎች ሲያደርግ ነበር። ጥሩ ጥሩ የግብ እድሎችንም በዚህ ነፃነቱ ሲፈጥር ታይቷል።


አጥቂዎች

ግሩም ሀጎስ (መከላከያ)

አዲሱ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተጫዋች ግሩም ሀጎስ በሊጉ ቤተኛ እስኪመስል በመከላከያ እና አርባምንጭ ጨዋታ ደምቆ አምሽቷል። ከምንም በላይ ታታሪነቱ ጎልቶ የወጣው ግሩም በማጥቃት እና በመከላከል አጨዋወት ቡድኑን በሚገባ ሲጠቅም ተስተውሏል። አልፎም በሁለቱም ሽግግሮች ላይ ፈጣን ሩጫዎችን በማድረግ በአስፈላጊው ቦታ ሲገኝ ታይቷል። በዋናነት ግን የመሐል አጥቂው ኦኩቱ ኢማኑኤል ወደ ጎልነት ሊቀይራቸው የሚችሉ የዐየር እና የመሬት ላይ ኳሶችን ከመስመር ሲያሻማ እና ለአርባምንጮች ፈተና ሲሆን ነበር።

ፍቃዱ ዓለሙ (ፋሲል ከነማ)

የ2014 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያው ባለ ሀት ትሪክ የዐፄዎቹ አጥቂ ፍቃዱ ዓለሙ ነው። ዓምና በሚያገኘው ዕድል ራሱን አሳይቶ የሚወጣው ይህ አጥቂ አሁንም የኦኪኪን መጎዳት ተከትሎ ባገኘው ዕድል ቀዳሚ ተመራጭ መሆን የሚያስችል አቅም እንዳለው በሚገባ አሳይቷል። ተጫዋቹ በዐየርም ሆነ በመሬት ላይ ፍልሚያዎች ጠንካራ ከመሆኑ በተጨማሪ የአጨራረስ ችሎታው ከፍታ በግልፅ በሀዲያው ጨዋታ ታይቷል። በተለይ ሁለተኛ ጎሉን ካልታሰበ ቦታ ያስቆጠረበት መንገድ በሳምንቱ ነጥሮ እንዲወጣ አድርጎታል።

ኦሴ ማውሊ (ባህር ዳር ከተማ)

አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱን ተከትሎ ባህር ዳር የደረሰው ማውሊ በመጀመሪያ ጨዋታው አስፈሪነቱን ማሳየት ጀምሯል። ማውሊ ድንቅ የቦታ አያያዝ ችሎታው፣ የአንድ ለአንድ ፍልሚያዎችን የማሸነፍ አቅሙ እና የአጨራረስ ብቃቱ የተሟላ አጥቂ ያስብለዋል። ከምንም በላይ የሚያገኛቸውን ኳሶች ሳያባክን ውጤታማ ለማድረግ የሚጥርበት መንገድ ድንቅ ነበር። ተጫዋቹም ጀርባውን ለጎል ሰጥቶ ከአጋሮቹ ጋር አንድ ሁለት የሚጫወትበት ሂደት የሚደነቅ ነው።


አሠልጣኝ

አብርሃም መብራቱ (ባህር ዳር ከተማ)

በመጀመሪያው ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብሮች ቡድናቸውን ለድል ካበቁ አምስት አሠልጣኞች መካከል የባህር ዳሩ አለቃ አብርሃም መብራቱ ይገኙበታል። እርግጥ ቡድናቸው በአዲስ አበባ እምብዛም ባይፈተንም ለጨዋታው በበቂ ሁኔታ በመዘጋጀት የቀረቡበት መንገድ እና ተጫዋቾቻቸው በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ረገድ ሚዛኑን የጠበቀ ውህደት ኖሮት እንዲጫወት የዘየዱት ስልት በሚገባ የተዋጣለት ስለነበረ አሠልጣኙን የሳምንቱ ምርጥ ብለናቸዋል።


ተጠባባቂዎች

ሚኬል ሳማኬ (ፋሲል ከነማ)
ሚኪያስ ካሣሁን (ድሬዳዋ ከተማ)
ግርማ ዲሳሳ (ባህር ዳር ከተማ)
ብርሀኑ አሻሞ (ሲዳማ ቡና)
ቢኒያም በላይ (መከላከያ)
ምንይሉ ወንድሙ (ወላይታ ድቻ)
ኦኩቱ ኢማኑኤል (መከላከያ)
ተመስገን ደረሰ (ባህር ዳር ከተማ)