የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት የመክፈቻ ጨዋታን እንዲህ ዳሰነዋል።
በዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በርካታ ተጫዋቾችን ለውጠው ከቀረቡ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ጅማ አባጅፋር የዓመቱን የመጀመሪያ ድል ለማግኘት የነገውን ጨዋታ ይጠባበቃል። በመጀመሪያ ሳምንት በሀዋሳ ከተማ አንድ ለምንም የተረታው ክለቡም አዳዲስ ተጫዋቾችን በማዋቀር እየገነባው ያለው ቡድኑን ከድል ጋር ለማስታረቅ ነገ ኮስተር ያለ አጨዋወት እንደሚከተል ይገመታል። እርግጥ በሀዋሳውም ጨዋታ ቀጥተኝነትን ሲከተል የነበረ ቢሆንም ፊት ላይ ስል አለመሆኑ ነጥብ እንዳያገኝ አድርጎታል።
አንጋፋ እና ወጣት ተጫዋቾችን የሰበሰበው የአሠልጣኝ አሸናፊ ክለብ በነገው ጨዋታ ፈጣኖቹን የፊት መስመር አጥቂዎች የተከላካይ ጀርባ ሩጫ እጅግ የሚሻ ይመስላል። በተለይ ዳዊት ፍቃዱ እና መሐመድኑር ናስር ረጃጅም ኳሶችን እና ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶችን ለመጠቀሚ የሚሄዱበት ርቀት ለአዳማ ከተማዎች ፈተና ሊሆን ይችላል። በተቃራኒው ግን አዲሱ የቡድኑ የኋላ መስመር የውህደት ደረጃ በሀዋሳው ጨዋታ ክፍተቶችን ሲያሳይ ስለነበር ነገ ካልተሻሻለ ቡድኑ አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል ይገመታል።
በቡድኑ ውስጥ ምንም የጉዳት ዜና የሌለ ሲሆን በመጀመሪያው ጨዋታ የአሠልጣኙ ተቀዳሚ ተመራጭ ሆኖ ሲጫወት የነበረው ዳዊት እስጢፋኖስ ከሜዳ ተቀይሮ ከወጣ በኋላ ባሳየው የዲሲፕሊን ጥሰት የ7 ጨዋታዎች ቅጣት ስለተላለፈበት በነገው ጨዋታ ለቡድኑ ግልጋሎት አይሰጥም። ከዳዊት በተጨማሪ ካሜሩናዊው አማካይ ሮጀር ማላ ይህንን ዘገባ እስካጠናከንበት ጊዜ ድረስ የስራ ፍቃዱን ባለማግኘቱ ለነገው ፍልሚያ ብቁ አለመሆኑን አውቀናል።
በአሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመራው አዳማ ከተማ ደግሞ በመጀመሪያው ሳምንት ከወልቂጤ ከተማ ጋር ተጫውቶ በአስቆጪ ሁኔታ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል። በተለይ ቡድኑ በጨዋታው የፍፁም ቅጣት ምት ማምከኑ እና በመጨረሻው ደቂቃ እጅግ ለግብ የቀረበ ዕድል አግኝቶ በአብዲሳ ጀማል አማካኝነት ሳይጠቀም መቅረቱ ዋጋ ያስከፈለው ይመስላል። ይህ ቢሆንም ቡድኑ እንደ ተጋጣሚው ጅማ በርካታ ለውጦችን በስብስቡ በማድረግ የዓመቱን ድል ቶሎ ለማስመዝገብ እና ዓምና የነበረበት ቦታ ዳግም ላለመገኘት ጠንክሮ ጨዋታውን ሊቀርብ ይችላል።
እንደ ጅማ ሁሉ ፈጣን አጥቂዎችን እንደሚያሰለፉ የሚጠበቁት አዳማዎች ከጅማ ሊጠብቃቸው ከሚችለው የዐየር ላይ ፍልሚያዎች በተቃራኒ ፈጣን ሽግግሮችን በማድረግ ጎል ጋር ለመድረስ እንደሚጥሩ ይታመናል። በተለይ ደግሞ የአሜ፣ ዳዋ እና አቡበከርን ፍጥነት ያማከሉ ኳሶችን ቶሎ ቶሎ ከአማካይ በማስነሳት ጅማ ላይ ጥቃት ለመፍጠር እንደሚሞክሩ ይገመታል። በተጨማሪም በወልቂጤው ጨዋታ የታየው የመስመር ተከላካዮቹ የማጣቃት ተሳትፎ ነገም ከተደገመ የጅማ ተከላካዮች ብርቱ ትግል ሊገጥማቸው ይችላል። እንደ ክፍተት ግን የአጨራረስ ችግር እና የቆሙ ኳሶችን በተደጋጋሚ ለተጋጣሚ የመፍቀድን ጉዳይ ክለቡ አሻሽሎ ሜዳ ካልገባ ለጅማ መልካም አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል።
በአዳማ በኩል ደግሞ በግል ምክንያት ፍቃድ ጠይቆ በአሁኑ ሰዓት ከስብስቡ ጋር የማይገኘው የግብ ዘቡ ጀማል ጣሰው ከነገው ጨዋታ ውጪ መሆኑን አረጋግጠናል።
8 ሰዓት የሚጀምረውን ጨዋታ ዳንኤል ግርማይ በመሐል ዳኝነት የሚመሩት ይሆናል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ጅማ አባጅፋ (4-2-3-1)
ዮሐንስ በዛብህ
ሽመልስ ተገኝ – በላይ ዓባይነህ – ያብስራ ሙሉጌታ – አስናቀ ሞገስ
ተስፋዬ መላኩ – አሳህሪ አልማዲ
መሐመድ ኑርናስር – መስዑድ መሐመድ – ኢዮብ ዓለማየሁ
ዳዊት ፍቃዱ
አዳማ ከተማ (4-3-3)
ሴኩምባ ካማራ
ሚሊዮን ሰለሞን – አሚን ነስሩ – ቶማስ ስምረቱ – ደስታ ዮሐንስ
ዮናስ ገረመው – ምንተስኖት አዳነ – አማኑኤል ጎበና
አቡበከር ወንድሙ – ዳዋ ሁቴሳ – አሜ መሐመድ