ሪፖርት | የዳዋ የቅጣት ምት ጎል አዳማን አሸናፊ አድርጓል

የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት የመክፈቻ መርሐ-ግብር የሆነው የጅማ እና አዳማ ጨዋታ አንድ ለምንም በሆነ ውጤት አዳማን ባለድል አድርጓል።

ሁለተኛ የሊጉ ጨዋታቸውን ለማድረግ ወደ ሜዳ የገቡት ሁለቱ ቡድኖች ከመጀመሪያ ፍልሚያቸው አራት እና ሦስት ለውጦችን አድርገዋል። ባለሜዳዎቹ ጅማ አባጅፋሮች የግብ ዘቡ ታምራት ዳኜን ጨምሮ ሱራፌል አወል፣ መስዑድ መሐመድ እና ዱላ ሙላቱን በዮሐንስ በዛብህ፣ ዳዊት እስጢፋኖስ፣ አስናቀ ሞገስ እና ሽመልስ ተገኝ ለውጠው ጨዋታውን ሲቀርቡ አዳማ ከተማዎች ደግሞ ምንተስኖት አዳነ፣ ዮናስ ገረመው እና አቡበከር ወንድሙን በዮሴፍ ዮሐንስ፣ ኤሊያስ ማሞ እና አብዲሳ ጀማል ተክተው ሜዳ ደርሰዋል።

ክፍት እንቅስቃሴ ማሳየት የጀመረው ጨዋታው ገና በአራት ደቂቃዎች ውስጥ ሁለት ዕድሎች ተፈጥረውበታል። በቅድሚያም ጅማ በመሐመድኑር ናስር አማካኝነት በግንባር ሲሞክር አዳማ ደግሞ በመቀጠል በአብዲሳ ጀማል አማካኝነት ጥቃት አስመልክተዋል። የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ ያደረገው መሐመድኑር በድጋሜ በ5ኛው ደቂቃም ሌላ ከመዓዘን የተሻገረን ኳስ ራሱን ነፃ አድርጎ በመጠበቅ ወደ ግብ ቢልከውም መረብ ላይ ሳያርፍለት ቀርቷል። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ አሜ ሳጥን ውስጥ ያገኘውን ኳስ ለመጠቀም ጥሮ ቡድኑን መሪ ለማድረግ ቢሞክርም ኳስ ዒላማውን ስቶ ወጥቶበታል።

እንደ አጀማመሩ በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ያልዘለቀው ጨዋታው በ20ኛው ደቂቃ መሪ አግኝቷል። በተጠቀሰው ደቂቃ በላይ አባይነህ አብዲሳ ጀማል ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የቅጣት ምት ዳዋ ሁቴሳ በጥሩ አጨራረስ መረብ ላይ አሳርፎት አዳማ መምራት ጀምሯል። በቶሎ ወደ ጨዋታው ለመመለስ መታተር የያዙት ጅማዎች በ28ኛው ደቂቃ እጅግ ለግብ ቀርበው ነበር። በዚህም በጥሩ የአንድ ሁለት ቅብብል የመጨረሻ ኳስ የደረሰው ዳዊት ፍቃዱ ወደ ግብ የመታውን ያለቀለት ኳስ ቁመታሙ የግብ ዘብ ሴኩምባ ካማራ በጥሩ ቅልጥፍና አድኖታል። ካማራ የመለሰውን ኳስ ያገኘው ዱላ ሙላቱ ደግሞ ዳግም ወደ ግብ ሲመታው ቋሚው መልሶበት ጅማ አቻ ሳይሆን ቀርቷል።

በቀሪ የአጋማሹ ደቂቃዎች አዳማ በሚሊዮን የግንባር ኳስ መሪነቱን ለማሳደግ ሲጥር ጅማ አባጅፋር ደግሞ በዳዊት እና ሱራፌል የረጅም ኳሶች አቻ ለመሆን ሞክረዋል። ነገርግን ከ20ኛው ደቂቃ የዳዋ ጎል ውጪ ተጨማሪ ጎል ሳይስተናገድ የመጀመሪያ አጋማሽ በአዳማ መሪነት ተገባዷል።

የሁለተኛውን አጋማሽ በተሻለ ንቃት የጀመሩት የአሠልጣኝ ፋሲል ተጫዋቾች ገና በ3ኛው ደቂቃ ሁለተኛ ጎል ለማግኘት ከጫፍ ደርሰው ነበር። በዚህም የጅማ ተከላካዮችን መዘናጋት ተከትሎ አሜ ያገኘውን ኳስ ወደ ሳጥን ሲያሻማው የግቡ ባለቤት ዳዋ በቀጥታ ወደ ግብ መትቶት ነበር። ነገርግን ዳዋ በዐየር ላይ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ታምራት ዳኜ በጥሩ ቅልጥፍና አምክኖታል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ለዳዋ አመቻችቶ ያቀበለው አሜ ዳግም ለአብዲሳ ሌላ ኳስ አቀብሎ አብዲሳ ሙከራ አድርጎ ወጥቶበታል።

በጨዋታው ድንቅ ብቃቱን ሲያሳይ የነበረው ዳዋ በ56ኛው ደቂቃ ራሱ ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የቅጣት ምት ዳግም ጅማ መረብ ላይ ሊያሳርፈው ቢቃረብም ለጥቂት ሳይሳካለት ቀርቷል። ከዳዋ የቅጣት ምት በተጨማሪ አዳማዎች የጅማን የላላ የኋላ መስመር አደረጃጀት ክፍተት በመጠቀም በአሜ እና አብዲሳ አማካኝነት ተከታታይ ጥቃቶችን ለመፈፀም ሞክረዋል።

ድንቅ ድንቅ የቆመ ኳስ አጠቃቀም ማስመልከት የቀጠለው ይህ ጨዋታ በ72ኛው ደቂቃ በዚሁ የጨዋታ ሂደት ግብ ሊመዘገብበት ነበር። በዚህም ጅማ ዮሴፍ ዮሐንስ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ ያገኙትን የቅጣት ምት በበላይ አባይነህ አማካኝነት ወደ ግብነት ለመቀየር ጥረው የነበረ ቢሆንም ካማራ አውጥቶባቸዋል። ይሁ የወጣውን ኳስ ከመዓዘን ያሻሙት ጅማዎች በተስፋዬ መላኩ አማካኝነት ግብ ሊያረጉት ቢዳዱም ድንቅ ብቃቱን በግብ ብረቶቹ መሐከል ሆኖ ሲያሳይ የነበረው ካማራ ተቆጣጥሮታል። በቀሪ ደቂቃዎችም ጅማዎች ቢያንስ አንድ ነጥብ ይዞ ለመውጣት የተሻለ ወደ አዳማ የግብ ክልል እያመሩ አጋጣሚ ለመፍጠር ቢያስቡም ሳይሳካላቸው ሦስት ነጥብ አስረክበው ወጥተዋል።

ውጤቱን ተከትሎ አዳማ ከተማ ነጥቡን አራት በማድረስ በጊዜያዊነት የሊጉ መሪ ሆኗል። ተከታታይ ሁለት ጨዋታዎችን የተረቱት ጅማ አባጅፋሮች ደግሞ ያለ ምንም ነጥብ በሁለት የግብ እዳ የመጨረሻዎቹ ደረጃዎች ላይ ተቀምጠዋል።