የአሠልጣኞች አስተያየት | ጅማ አባጅፋር 0-1 አዳማ ከተማ

በአዳማ አንድ ለምንም አሸናፊነት ከተጠናቀቀው የዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሠልጣኞች ተከታዩን የድህረ-ጨዋታ አስተያየት ሰጥተዋል።

ፋሲል ተካልኝ – አዳማ ከተማ

ጨዋታው እንዴት ነበር?

በጨዋታው የምንፈልገውን ሦስት ነጥብ አግኝተናል። ጎል አግብተናል። ጎል ካገባን በኋላ ጨዋታውን በምንፈልገው መንገድ ተቆጣጥረን ወጥተናል ብዬ ግን አላስብም። አንዱ ግን የምናገኛቸውን ዕድሎች በአግባቡ አለመጠቀማችን ጫናዎች እንዲበረታብን አድርጓል። ዋናው ነገርግን ሦስት ነጥብ ማግኘታችን ነው።

ሌሎች የግብ ዕድሎችን ስላለመጠቀማቸው?

የመጨረሻውን አስር እና አስራ አምስት ደቂቃዎች ጫና ውስጥ የገባነው ከእረፍት በኋላ በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች በሳትናቸው ግልፅ የግብ ዕድሎች ነው። እነሱን አለመጠቀማችን ብዙ ነገር አበላሽቶብናል። እንደ ቡድን ግን ማሸነፋችን ተገቢ ነው።

በቀጣይ ጨዋታዎች…?

ውድድሩ ረጅም ነው። ሩቅ ነው። እያንዳንዱን ጨዋታ ማሸነፍ እንፈልጋለን። ስለዚህ ከእያንዳንዱ ጨዋታ ነጥብ ለማግኘት እና የአሠልጣኝ ቡድኑም ሆነ የተጫዋቾችን ስነ-ልቦና ከፍ ለማድረግ ማሸነፍ እንፈልግ ነበር። በአጠቃላይ የዛሬው ሦስት ነጥብ ለእኛ ብዙ ነገር ነው።

አሸናፊ በቀለ – ጅማ አባጅፋር

ጨዋታው እንዴት ነበር?

በጨዋታው ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች በአግባቡ አልተጠቀምንም። ጎል አካባቢ የምንሰራቸው ስህተቶችም ዋጋ አስከፍሎናል። ከዚህ ውጪ ግን የነበረን እንቅስቃሴ በጣም ጥሩ ነገር አለው። መቻኮሎች አሉ። ይህ ከልጅነት የሚመጣ ነገር ነው። እነዚህን ነገሮች አስተካክለን ለሚቀጥለው ጨዋታ ዝግጅታችንን እንቀጥላለን።

ተጫዋቾችን በተለየ ሚና ስለማጫወታቸው?

ክፍተቶች አሉብን። ክፍተቶቹን ለመድፈን ደግሞ እንደዚህ አይነት ነገሮች ይቀጥላሉ ብዬ እገምታለሁ።

እንዲሸነፉ ያስቻለችውን ጎል ስላስቆጠረው ዳዋ…?

ዳዋ የፍፁም ቅጣት ምት አካባቢ ጥሩ ነው። እዛ አካባቢ ስህተት እንዳንፈፅም አስበን ነበር ወደ ሜዳም የገባነው። ግን አልሆነም። በዚህ አጋጣሚ አዳማዎችን እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ። ውጤቱ ግን እንቅስቃሴውን አይገልፀውም።

ያጋሩ