ሪፖርት | ወላይታ ድቻ በሀብታሙ ንጉሤ ጎል ድል ተቀዳጅቷል

ወላይታ ድቻ እና ሀዋሳ ከተማን ያገናኘው የሁለተኛ ሳምንት ሁለተኛ ጨዋታ በወላይታ ድቻ አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል።

በድሬዳዋ ከተማ ተረተው ለዛሬው ጨዋታ የቀረቡት ወላይታ ድቻዎች ከመጀመሪያው ጨዋታ ቃልኪዳን ዘላለምን ብቻ በያሬድ ዳዊት ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በተቃራኒው በድል ዓመቱን የጀመሩት ሀዋሳዎች ደግሞ ከጅማ አባጅፋሩ ጨዋታ ሦስት ለውጦችን አድርገዋል። በዚህም ዳንኤል ደርቤ፣ በቃሉ ገነነ እና ፀጋሰው ድማሙ አርፈው መድሃኔ ብርሃኔ፣ ዳዊት ታደሠ እና ወንድማገኝ ማዕረግ ጨዋታውን ጀምረዋል።

ገና ከጅምሩ ቀጥተኛ አጨዋወት መከተል የያዙት ወላይታ ድቻዎች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ባገኙት የመዓዘን ምት መሪ ለመሆን ሞክረዋል። በአንፃሩ ኳሱን ተቆጣጥረው ለመጫወት ሲጥሩ የታዩት ሀዋሳዎች በ12ኛው ደቂቃ ኳስ እና መረብን ሊያገናኙ ነበር። በዚህም ኤፍሬም አሻሞ ከግራ የተሻገረለትን ኳስ በወረደ አጨራረስ ወደ ግብ መታው እንጂ ቡድኑ መሪ ሊሆን ተቃርቦ ነበር። ጨዋታው ቀጥሎ እስከ 25ኛወው ደቂቃ ድረስ ሙከራ ሳያስተናግድ ቆይቶ በተጠቀሰው ደቂቃ መሪ አግኝቷል።

በዚህም ደቂቃ በደቂቃ እድገት እያሳዩ የመጡት ድቻዎች የሀዋሳ ከተማ ተከላካዮች የተውትን ሰፊ ቦታ በፈጣን ሽግግር በማጥቃት በስንታየሁ መንግስቱ አማካኝነት ሙከራ አድርገዋል። ስንታየሁ የሞከረውን ኳስ የግብ ዘቡ ዳግም ተፈራ ሲመልሰው የዘገየ ሩጫ ወደ ተጋጣሚ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ሲያደርግ የነበረው ሀብታሙ ንጉሴ አግኝቶት መረብ ላይ አሳርፎት ድቻ ወደ መሪነት ተሸጋግሯል።

አቻ ለመሆን መታተር የቀጠሉት ሀዋሳዎች በ34ኛው ደቂቃ ጽዮን መርዕድን የፈተነ ኳስ ልከዋል። በተጠቀሰው ደቂቃ ወንድማገኝ ኃይሉ በግራ የሳጥኑ ጫፍ ቆሞ ለነበረው ብሩክ ያመቻቸለትን ኳስ አጥቂው ወደ ግብ ቢመታውም ለጥቂት መረብ ላይ ሳያርፍ ቀርቷል። ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ይሁ አጥቂ በተቃራኒ ቦታ ሌላ አጋጣሚ አግኝቶ ነበር። ለተከታታዮቹ ጥቃቶች ምላሽ ለመስጠት ያልቦዘኑት ድቻዎች ከደቂቃ በኋላ ምንይሉ በሞከረው ኳስ መሪነታቸውን ለማሳደግ ተንቀሳቅሰው መክኖባቸዋል። በአጋማሹም ተጨማሪ የግብ ሙከራ ሳንመለከት ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሙሉ ለሙሉ መከላከል ላይ ያተኮረ አጨዋወት መከተል የመረጡት ወላይታ ድቻዎች ያገኙትን ሦስት ነጥብ ይዞ ለመውጣት ሲጣጣሩ ነበር። በተቃራኒው ሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ በሙሉ ሀይላቸው ተጭኖ ለመጫወት ሞክረዋል። ይህንን ለማድረግ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾች ላይ ለውጥ ቢያደርጉም እስከ 65ኛው ደቂቃ ድረስ የሰላ ሙከራ አላደረጉም ነበር። በዚህም ከደቂቃ በፊት ወንድማገኝን ለውጦ ወደ ሜዳ የገባው ብሩክ ኤሊያስ መዓዘን ምትን መነሻ ያደረገ ኳስ ሞክሮ ነበር። ከደቂቃ በኋላ ደግሞ መስፍን እና ብሩክ ከሳጥን ውጪ እና ከመዓዘን ምት ሌላ ጥሩ ዕድሎችን ፈጥረው ነበር።

እንደተጠቀሰው ድቻዎች በእጃቸው የገባውን ነጥብ ላለማጣት በመከላከል አጨዋት ቢጫወቱም በረጃጅም ኳሶች ተጨማሪ ጎል ለማግኘት ሲሞክሩ ነበር። ነገርግን እምብዛም ስኬታማ ሳይሆኑ ጨዋታውን ጨርሰዋል። ሀዋሳዎችም በቁጥር በርከት ብለው ወደ ፊት ቢሄዱም ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ጨዋታውን በሽንፈት ደምድመዋል።

ውጤቱን ተከትሎ ወላይታ ድቻ ነጥቡን 3 በማድረስ ከ13ኛ ወደ 7ኛ ደረጃ ከፍ ብሏል። ሀዋሳ ከተማ ደግሞ ወደ ስድስተኛ ደረጃ የተንሸራተተበትን ውጤት አስመዝግቦ ከሜዳ ወጥቷል።