የአሰልጣኞች አስተያየት | ወላይታ ድቻ 1-0 ሀዋሳ ከተማ

ከምሽቱ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ሁለቱ አሰልጣኞች ከሱፐር ስፖርት ጋር ይህንን ቆይታ አድርገዋል።

አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማሪያም – ወላይታ ድቻ

ስለጨዋታው

በመጀመሪያ ከፍተኛ መስዕዋትነት የከፈሉ ተጫዋቾቼን ማመስገን እፈልጋለሁ። በከፍተኛ ተነሳሽነት ነው ወደ ሜዳ የገቡት። ዛሬ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ቻምፒዮን ለመሆን የተደረገ ጨዋታ ነበር ማለት ይቻላል። ሀዋሳ ከተማ ሦስት ነጥብ ይዞ ነው የመጣው። ከእኛ ነጥብ አገኘ ማለት በሁለታችን መሀል የስድስት ነጥብ ልዩነት ኖረ ማለት ነው። በጣም ውጥረት የነገሰበት ሜዳ ላይ የነበረውም ፉክክር በጣም ጠንካራ የሆነ በሁለታችንም በኩል በማጥቃት ላይ የተመሰረተ እና ተነሳሽነቱ ከፍተኛ የሆነ ጨዋታ አይተናል። በሁለታችንም በኩል የነበረው እንቅስቃሴ በጣም ጥሩ ነው። በአጠቃላይ ግን ዛሬ ወሳኝ ሦስት ነጥብ ነው ማግኘት የቻልነው። ከዚህ ጀምሮ ቡድናችን ወደ ኋላ መሄድ የለበትም። ለቡድኑ ሞራል ለደጋፊዎቻችንም ሞራል አስፈላጊ ሦስት ነጥብ አግኝተናል። በድጋሚ መስዕዋትነት የከፈሉ ተጫዋቾቼን ማመስገን እፈልጋለሁ።

ከግቡ በኋላ ነጥብ ለማስጠበቅ ስለመጫወታቸው

አንዳንዴ ከፍተህ የምትጫወትበት አጋጣሚ አለ ፤ ውጤት ለማስጠብቅ የምትጫወትበትም አለ። በአሁኑ ሰዓት ምንም አያስፈልግም። የቡድን ስታይል የምታይበት ጊዜም አይደለም። ውጤት ባመጣህ ቁጥር በቡድንህ ውስጥ ያለው በራስ መተማመን እያደገ ይሄዳል። ይህንን ነው ታሳቢ ያደረግነው። እንቅስቃሴውም መጥፎ አልነበርም ፤ የኛ ጨዋታ። ቢሆንም ግን እነሱም የጠራ የግብ ሙከራ አላደረጉም። ተጭነው ለመጫወት ሞክረዋል ወደ መጨረሻ አካባቢ። እና ወሳኝ ሰዓት ላይ ሦስት ነጥብ አስጠብቆ ለመውጣት በሚደረግ ሽግሽግ ላይ እንዲህ ዓይነት ክፍተት ይኖራል። ዞሮ ዞሮ የቡድኑን ሥነልቦና መመለስ ነበር የፈለኩት። በዛሬው ጨዋታ የጥሎ ማለፍ ባህሪ ተላብሰን ነው ወደ ሜዳ የገባነው። ስለዚህ አሸንፈን በመውጣታችን ወሳኝ ሦስት ነጥብ ነው ማለት እችላለሁ።

ካርዶች ስለመብዛታቸው

ዲሲፒሊን በየትኛውም መልኩ ወሳኝነት አለው። ከራሳችን ነው የሚጀምረው። እኔ ራሴ ቢጫ ካርድ አይቻለሁ ፤ ምንም ማለት አይደለም። ሁል ጊዜ ትዕግስት የሚኖርህ ቦታ አለ ፤ ትዕግስት የማይኖርህ ቦታ አለ። ዞሮ ዞሮ የዳኛ ውሳኔ ሁል ጊዜ መከበር አለበት። የዳኛ ውሳኔ ሁሌም የመጨረሻ ውሳኔ ነው። እንግዲህ ስሜታዊነት ሊኖር ይችላል እና ዞሮ ዞሮ ይህንን ማረም እና ተጫዋቾቻችንም ራሳችንም ተገዢ መሆን ያስፈልጋል። ጥሩ አርዓያ መሆን አለብን ብዬ አስባለሁ። ዳኞቻችንም በአንፃሩ ትዕግስተኛ መሆን አለባቸው። በእርግጥ የዛሬው ዳኝነት እኔ በጣም ተመችቶኛል። ልምዱን በመጠቀሙ እንጂ ከዚህ በላይ ብዙ ጥፋቶች ሊኖሩ ይችሉ ነበር። ልምዱን በመጠቀም በሚዛናዊነት ዳኝቶናል በዚህ አጋጣሚ ላመሰግነው እፈልጋለሁ።

ዘርዓይ ሙሉ – ሀዋሳ ከተማ

ስለጨዋታው

በዚህ አጋጣሚ ድቻዎችን እንኳን ደስ ያላችሁ እላለሁ። ብዙ ኳሶችን መሳታችን ዋጋ አስከፍሎናል ማለት ይቻላል። ኳሱን ተቆጣጥረን ዘጠናውንም ደቂቃ ማለት ይቻላል ብልጫ ወስደን ተጫውተናል። ጎል ጋር ብዙ ደርሰናል የአጠቃቀም ችግሮች በተደጋጋሚ ይታዩ ነበር እንጂ በጣም በቀላሉ አሸንፈን መውጣት የምንችለው ጨዋታ ነበር። ዞሮ ዞሮ በሰራነው ስህተት ጎል አለማግባታችንም ተጨማሪ ሆኖ ተሸንፈን ወጥተናል።

ካርዶች ስለመብዛታቸው

እነሱም ውጤቱ ያስፈልጋቸው ነበር። እኛም አሸናፊነቱን ይዞ ለመቀጠል ከፍተኛ ጥረት ነበር ያደረግነው። በዚህ አጋጣሚ የተጫዋቾች ፍላጎት የሚፈጥረው ነገር ነው ፋዎሎች እንዲበዙ የሚያደርገው። በዚህ አጋጣሚ ተፈጠረ እንጂ ሌላ ችግር አልነበረውም። ዞሮ ዞሮ ግን ማራኪ ጨዋታ ነው ብዬ ነው የማስበው። ምክንያቱም ዘጠና ደቂቃ ኳስ ጎል ጋር ቶሎ ቶሎ ይደርስ ስለነበር ደጋፊም ያንን ስለሚፈልግ። በውጤት ባንታጀብም ጥሩ እንቅስቃሴ ነበር ያሰረግነው።