የሁለተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ሁለተኛ መርሐ-ግብር ፍልሚያን የተመለከተ ዳሰሳ እንዲህ ተሰናድቷል።
ነገ ከሚደረጉት ጨዋታዎች መካከል ተጣባቂው የሲዳማ እና ድሬዳዋ ጨዋታ ነው። በአሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የሚመራው ሲዳማ ቡና በመጀመሪያ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያለ ግብ አቻ መለያየቱ ይታወሳል። እርግጥ ቡድኑ በጨዋታው በአንፃራዊነት የተሻሉ ዕድሎችን ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም ሦስት ነጥብ በእጁ ማስገባት ሳይችል ከሜዳ ወጥቷል። ነገ ግን የመጀመሪያ ድሉን ድሬ ላይ ለማስመዝገብ ያልማል።
በኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ እጅግ ፈጣን እንቅስቃሴ ሲያስመለክቱ የነበሩት የሲዳማ ተጫዋቾች በተለይ ከወገብ ላይ ተጋጣሚን ተጭኖ በመጫወት ኳሶችን በቶሎ ወደ ግብ ለመቀየር ሲታትሩ ነበር። ከምንም በላይ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ከራሳቸው ሜዳ ኳስ እንዳይመሰርቱ በማድረግ ራሳቸው ላይ ሊፈጠር የሚችለውን ጫና እየቀነሱ በዛው የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን እምብዛም ከተጋጣሚ ሳጥን ሳይርቁ ለመፍጠር ሲያስቡ ነበር። ይህ እንቅስቃሴ ደግሞ ነገም በድሬዳዋው ጨዋታ እንደሚቀጥል ይታመናል።
በመጀመሪያ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች በርካታ ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች በማድረግ ቀዳሚ የሆነው ሲዳማ ቡና (7) የአጨራረስ ብቃቱን አሻሽሎ ሜዳ ከገባ የማሸነፍ ዕድሉን ያሰፋል። ከምንም በላይ ከፍሬው ሰለሞን እና ቴዎድሮስ ታፈሠ የሚነሱ የመሐል ለመሐል ኳሶች ለድሬዎች ፈተና እንደሚሆን ይገመታል። ምናልባት ግን የድሬዳዋ ፈጣን የመስመር ላይ ሽግግሮችን ቡድኑ በሚገባ መመከት እንደሚገባው ግልፅ ነው። ከዚህ ውጪ ለኳስ ቁጥጥር ብዙም ፍላጎት የማያሳየው ቡድኑ ነገ የሚኖረው ፍላጎት ግን የሚጠበቅ ነው።
በቡድኑ ውስጥ ምንም የጉዳት እና የቅጣት ዜና የሌለ ሲሆን በስራ ፍቃድ ምክንያት ግን ዩጋንዳዊው አጥቂ ዴሪክ ንሲምባቢ እንደማይኖር ታውቋል።
በድል ዓመቱን ከጀመሩ አምስት ክለቦች መካከል የምስራቁ ተወካይ ድሬዳዋ ከተማ አንዱ ነው። በሄኖክ አየለ የመጨረሻ ደቂቃ ግብ ወላይታ ድቻን ያሸነፈው ክለቡም በዚህ በያዘው የአሸናፊነት መንገድ ለመቀጠል እና በወረቀት ላይ የዋንጫ ተፎካካሪ እንደሆነ የሚገመተውን ሲዳማ ቡናን በማሸነፍ የደረጃ ሠንጠረዡን አናት ለመቆናጠጥ ጠንክሮ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይታሰባል።
ኳስ ተቆጣጥሮ ለመጫወት እና የተጋጣሚን ክፍተት በትዕግስት ለመፈለግ የሚሞክር የሚመስለው የአሠልጣኝ ዘማርያም ቡድን ነገም በዚህ ስክነት የተሞላበት የመሐል ሜዳ ላይ እንቅስቃሴ እንደሚጫወት ይገመታል። ከመሐል ሜዳ ሲያልፍ ግን ወደ መስመሮች በማመዘን የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚሞክር ቡድን ነው። በተለይ ደግሞ ጋዲሳ መብራቴ በሚሰለፍበት ቦታ ላይ አተኩሮ ተጋጣሚን ማስጨነቅ እንደሚቀናውም በዲቻው ጨዋታ በጉልህ ታይቷል። ይህ ቢሆንም ግን የቡድኑ የውህደት ደረጃ በሚፈለገው መጠን አለመሆኑ በርከት ያሉ የግብ ዕድሎችን እንዳይፈጥር ያደረገው ይመስላል።
በቡድኑ ላይ የታየው እና መጠቀስ ያለበት ችግር ደግሞ በተከላካይ ጀርባ የሚተወው አደጋ አምጪ ክፍተት ነው። በተለይ በድቻው ጨዋታ ቡድኑ ማጥቃት ላይ ያለው ትኩረት እየጨመረ ሲሄድ ከተከላካይ ጀርባ የሚተወው ክፍተት ለጥቃት እንደሚዳርገው ስለታየ ነገ መሻሻል ይኖርበታል። አለበለዚያ ግን ፈጣን እና ስል ተጫዋቾች ያሉት ሲዳማ ይህንን ክፍተት እንደ በጎ ጎን ወስዶ የግብ ምንጭ ሊያደርግበት ይችላል።
በድሬዳዋም በኩል ምንም ጉዳት እና ቅጣት የለም። ጋናዊው ተከላካይ አውዱ ናፊዩ እና አማካዩ መሐመድ አብዱለጢፍ እንዲሁም ማሊያዊው አጥቂው ማማዱ ሲዲቤ የሥራ ፍቃዳቸው ስላላለቀ ለነገው ፍልሚያ እንደማይደርሱ ተመላክቷል።
ይህንን ጨዋታ ፌዴራል ዋና ዳኛ ዮናስ ካሣሁን በአርቢትርነት የሚመሩት ይሆናል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ 16 ጊዜ የመገናኘት ታሪክ አላቸው። ከእነዚህ ጨዋታዎች ውስጥ ግማሹን በድል የተወጣው ሲዳማ ቡና 17 ግቦችን አስቆጥሯል። ድሬዳዋ ከተማ ስምንት ግቦች ያሉት ሲሆን ሁለት ጊዜ ድል አድርጓል። ቀሪዎቹ ስድስት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ነበሩ።
ግምታዊ አሠላለፍ
ሲዳማ ቡና (4-3-3)
ተክለማርያም ሻንቆ
አማኑኤል እንዳለ – ጊት ጋትኩት – ያኩቡ መሐመድ – ሰለሞን ሀብቴ
ቴዎድሮስ ታፈሰ – ብርሀኑ አሻሞ – ፍሬው ሰለሞን
ሀብታሙ ገዛኸኝ – ይገዙ ቦጋለ – ፍራንሲስ ካሃታ
ድሬዳዋ ከተማ (4-3-3)
ፍሬው ጌታሁን
እንየው ካሣሁን – መሳይ ጻውሎስ – ሚኪያስ ካሣሁን – ሄኖክ ኢሳይያስ
ዳንኤል ኃይሉ – ብሩክ ቃልቦሬ – ሱራፌል ጌታቸው
ሙኸዲን ሙሣ – አብዱራህማን ሙባረክ – ጋዲሳ መብራቴ