በዛሬው ቀዳሚ ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ አዲስ አበባ ከተማን 2-1 በማሸነፍ ከመጀመሪያ ሽንፈቱ አገግሟል።
ሁለቱ ተጋጣሚዎች በመጀመሪያው ሳምንት ካደረጉት ጨዋታ አንፃር እያንዳንዳቸው የአምስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። አዲስ አበባ ከተማዎች ግብ ጠባቂው ወንድወሰን ገረመውን በዳንኤል ተሾመ ሲተኩ ሳሙኤል አስፈሪ ፣ ሮቤል ግርማ ፣ ልመንህ ታደሰ እና ብዙአየሁ ሰይፉ በአሰጋኸኝ ጴጥሮስ ፣ ዘሪሁን አንሼቦ እና ሳሙኤል ተስፋዬ እና እንዳለ ከበደ ቦታ ዛሬ ወደ አሰላለፍ መጥተዋል። አርባምንጮች በበኩላቸው አሸናፊ ፊዳ ፣ ተካልኝ ደጀኔ ፣ አንዷለም አስናቀ ፣ በላይ ገዛኸኝ እና ራምኬል ሎክን ሲጠቀሙ አንድነት አዳነ ፣ መላኩ ኤሊያስ ፣ አቡበከር ሸሚል ፣ ሱራፌል ዳንኤል እና አሸናፊ ተገኝን አሳርፈዋል።
ከለውጦቹ ባሻገር ባልተጠበቀ ሁኔታ የአዲስ አበባው አሰልጣኝ እስማኤል አቡበከር በተመልካች መቀመጫ ላይ ሲታዩ ቡድኑ በምክትል አሰልጣኙ ደምሰው ፍቃዱ ተመርቷል። ይህ የሆነውም የአሰልጣኙ ስም በዳኞች መዝገብ ላይ ባለመካተቱ መሆኑ ተሰምቷል። የጉዳዩ መነሻ ደግሞ በዋና አሰልጣኙ እና በቡድን መሪው መካከል የተፈጠረ አለመግባባት ነበር።
የመጀመሪያ አጋማሹ የቡድኖቹ ፉክክር በመሀል ሜዳ ፍልሚያ ላይ ያመዘነ ነበር። ረዘም ባሉ ኳሶች መስመር ተኮር የሆኑ ጥቃቶችን መሰንዘር ምርጫቸው የነበረው አርባምንጮች መጀመሪያ አካባቢ የተሻለ ተጭነው መጫወት ችለው ነበር። አዲስ አበባዎችም በቅብብሎች ለመውጣት የሚያደርጉት ጥረት አልፎ አልፎ ይታይ የነበረ ቢሆንም ሁለቱም የተሳኩ ጥቃቶችን ሰንዝረው የግብ ዕድሎችን እንደልብ ሲፈጥሩ አልታየም።
የጨዋታው ቀዳሚ ጥሩ ዕድል በአርባምንጮች በኩል ሲፈጠር 12ኛው ደቂቃ ላይ ሬምኬል ሎክ ከቀኝ ከበላይ ገዛኸኝ የደረሰውን ኳስ በተከላካዮች መሀል ሆኖ ወደ ግብ ቢሞክርም ኳሱ አቅም አልነበረውም። አዲስ አበባዎች ብዙም ሳይቆይ ምላሽ ለመስጠት ሲሞክሩ ቢኒያም ጌታቸው ከዋለልኝ ገብሬ የተሻገረለትን ኳስ ከግቡ ቅርብ ርቀት ላይ ተንሸራቶ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።
ከእነዚህ ሁለት ጥረቶች ውጪ የቡድኖቹ የማጥቃት ሂደት በተጋጣሚ ሳጥን አቅራቢያ ሲደርስ እየከሸፈ ነበር ጨዋታው የቀጠለው። ቡድኖቹ የቆሙ ኳስ ዕድሎችን ያገኙባቸው አጋጣሚዎች ትንሽ የሚባሉ ባይሆኑም አደገኛ መሆን ግን አልቻሉም። ሁለቱም የመከላከል ትኩረታቸው ከፍ ብሎ ጥቃቶችን አስወግደው ወደ ዕረፍት ሊወጡ ሲቃረቡ ድንቅ ግብ ተቆጥሯል። 45ኛው ደቂቃ ላይ ግራ መስመር ተመላላሹ ያሬድ ሀስን ወደ ፊት ኳስ በመግፋት የጀመረውን ጥቃት ቢኒያም ጌታቸው ተቀብሎ ሲያመቻችለት ሙሉቀን አዲሱ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ በቀጥታ ከመረብ በማረፍ አዲስ አበባን ቀዳሚ አድርጓል።
ከዕረፍት መልስ የአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ቅያሬዎች መሪነቱን ወደ አርባምንጭ ወስደውታል። ከዕረፍት መልስ ራምኬልን ተክቶ የገባው ፍቃዱ መኮንን 56ኛው ደቂቃ ላይ ከወርቅይታደል አበበ የደረሰውን ኳስ ተቀብሎ በመዞር ከሳጥን ውጪ በቀጥታ መትቶ ቡድኑን አቻ አድርጓል። ይህ በሆነ ከሁለት ደቂቃ በኋላ ግብ አስቆጣሪው ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ ከተቀየረ ሦስት ደቂቃዎች ብቻ የሆኑት አሸናፊ ተገኝ በግንባሩ ሲሞክር ሮቤል ግርማ ኳስ በእጅ በመንካቱ አዞዎቹ ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። አምበሉ ወርቅይታደል አበበም ፍፁም ቅጣት ምቱን አስቆጥሯል። ብዙም ሳይቆይ አዲስ አበባዎች በግራ በኩል ጥቃት ከፍተው ያሬድ ካሻማው ካስ ግብ ሊያገኙ ቢቃረቡም የአጥቂው የቢኒያም የግንባር ኳስ በግቡ ቋሚ ተመልሷል።
ከውጤት ለውጡ በኋላ የጨዋታው ፉክክር ጋል ብሏል። አርባምንጮች በፍቃዱ የግንባር ኳስ አዲስ አበባዎች ደግሞ በሮቤል ግርማ የርቀት ቅጣት ምት ተጨማሪ ሙከራዎችን አድርገዋል። ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር ግን የአርባምንጮች ጥቃት የተሻለ አስፈሪ ሆኖ ታይቷል። አማካዩ እንዳልካቸው መስፍን 82ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ ያደረገው ሙከራ ወደ ውጪ ሲወጣ ተጫዋቹ 88ኛው ደቂቃ ላይ ከአዲስ አበባ ተከላካዮች በተነጠቀ ኳስ ከሳጥኑ መግቢያ ላይ ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርጎ ዳንኤል ተሾመ በአስገርሚ ሁኔታ አድኖበታል። አዲስ አበባዎች በጭማሪ ደቂቃ አቻ ሊሆኑ የተቃረቡበት የሮቤል ግርማ ወደ ቀኝ ያደላ ቅጣት ምት በሳምሶን አሰፋ ድኗል። ጨዋታውም በአርባምንጭ ከተማ 2-1 አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል።
ውጤቱን ተከትሎ አርባምንጭ ከተማ ከ13 ወደ 8ኛ ደረጃ ከፍ ሲል አዲስ አበባ በሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ለመቆየት ተገዷል።