የአሰልጣኞች አስተያየት | አዲስ አበባ ከተማ 1-2 አርባምንጭ ከተማ

የ8:00 ሰዓቱ ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ አሰልጣኞች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቀጣዩን ቆይታ አድርገዋል።

አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ – አርባምንጭ ከተማ

ስለጨዋታው

ጨዋታው ጥሩ ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ በምንፈልገው ደረጃ አልተንቀሳቀስንም። በሁለተኛው አጋማሽ ግን አንዳንድ ቅያሪዎችን አድርገን እግዚያብሔርም ረድቶን ውጤት ይዘናል። ትንሽ የሥነ ልቦና ጥንካሬን ይፈልግ ነበር። ባለፈው ከረጅም ጊዜ በኋላ ነው የተሸነፍነው። ወደ ማሸነፍ መመለስ ነበረብን። ሁለተኛው አጋማሽ ላይ አግብተናል ግን ተመልካች ጥሩ እና አዝናኝ ነገር ማየት አለበት። ሆኖም ከኋላ ተነስተን ሁለት ጎሎች አግብተን አሸንፈን መውጣት ችለናል። ሌሎች አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ጥረናል። ከዚህ በላይ መሻሻል ግን ያስፈልጋል።

ስለደጋፊው ጥያቄ

አሁን ላይ ምንም ጫና ውስጥ የሚያስገባን ነገር የለም። ማራቶን ሲጀመር ግር ብሎ ነው። ስላሸነፍክም ቻምፒዮን ሆነሀል ማለት አይደለም። ሁለት እና ሦስት ጨዋታ ስለተሸነፈም እሱ ቡድን ቻምፒዮን አይደለም የሚባልበት ጊዜ ላይ አይደለንም። ስለዚህ ትዕግስት ይፈልጋል። ከዛ ውጪ የተለያዩ ፍላጎቶች ያላቸው አካላት ይኖራሉ ያ እኛን ምንም አያደርገንም። ይህ ቡድን እዚህ ሲደርስ በተለያዩ ጫናውች ውስጥ አልፎ ነው። ስለዚህ ነገ ከነገ ውዲያም የሚደግፍም ደስ የማይለውም ይኖራል እኛ ግን የራሳችን ሥራ ላይ ነው የምናተኩረው። ብናሸንፍ አንኩራራም ብንሸነፍም አንደናገጥም። ማድረግ የሚገባንን እየሰራን መሄድ ነው። ከዛ ውጪ ደግሞ እግዜያብሔር እና አለቆቻችን የሚሉትን ነው የምንሰማው።

ምክትል አሰልጣኝ ደምሰው ፍቃዱ – አዲስ አበባ ከተማ

ስለጨዋታው

ጨዋታው ጥሩ ነበር። የመጀመሪያውን ሳምንት ጨዋታ ተሸንፈን ስለነበር ምን ማድረግ አለብን ? ቡድናችን የነበረው ክፍተ ምን ላይ ነው ? የሚለውን ነገር አይተን ትንሽ የተጫዋቾች እና የአጨዋወት ዘዴ ቀየር አድርገን ለመግባት ሞክረናል። በዛም የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠቃሚ ነበርን ፤ የተሻልን ነበርን።

ስለአሰልጣኝ እስማኤል ቡድኑን አለመምራት

ምክንያቱ ገና ይፋ አልሆነም። ከቡድን መሪው ጋር አንዳንድ አለመግባባቶች ስለነበሩ ነው። ያ ነገር ይፋ ሲሆን እናንተም ታውቁታላችሁ።

ስለተደጋጋሚ ሽንፈቱ

እውነት ነው ማሸነፍ እና መሸነፍ ልዩነት አለው። ባሸነፍክ ቁጥር የሥነ ልቦና የበላይነትን ልትጎናፀፍ ትችላለህ። ነገር ግን ውድድሩ ገና መጀመሩ ነው እኛም ረዘም ያለ ጊዜ ወስደን በሥነልቦናው እየተሻሻልን ክፍቶቻችንን በማረም እንቀርባለን።