አዲስ አበባ ከተማ በዛሬው ዕለት በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአርባምንጭ ከተማ 2ለ1 በተረታበት ጨዋታ አሰልጣኙ እና ቡድን መሪው በፈጠሩት አለመግባባት አሰልጣኝ እስማኤል አቡበከር ጨዋታ እንዳይመሩ ተደርጓል፡፡
ዛሬ ቀን 8፡00 ሲል አዲስ አበባ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ ባደረጉት ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማ በመጀመሪያው አጋማሽ ባስቆጠራት ግብ መሪ መሆን ችሎ የነበረ ቢሆንም ከእረፍት መልስ በተቆጠሩበት ሁለት ግቦች ለመሸነፍ ተገዷል፡፡ ክለቡ በዛሬው ዕለት አስቀድሞ በዋና አሰልጣኙ እስማኤል አቡበከር ይመራል ተብሎ ቢጠበቅም አሰልጣኙ ሙሉ የጨዋታውን ክፍለ ጊዜ ከተመልካቾች ጋር በትሪቡን ቁጭ ብለው ሲመለከቱ አስተውለናል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያ አሰልጣኙ ላይመሩ የቻሉበትን ምክንያት ባደረገችው ማጣራት አሰልጣኝ እስማኤል አቡበከር እና ቡድን መሪው አቶ ሲሳይ ተረፈ ክለቡ ባረፈበት ሆቴል በፈጠሩት እሰጣ ገባ አሰልጣኙ በቡድን መሪው ላይ ቡጢ እንደሰነዘሩ እና ክለቡ በጊዜያዊነት እንዳይመሩ አድርጓቸው ትሪቡን ሊቀመጡ እንደተገደዱ ለማወቅ ተችሏል፡፡
አሰልጣኝ እስማኤል ስለተፈጠረው ክስተት ዝርዝር ሀሳብ ባይሰጡንም “ቡድኑን ለመከፋፈል በተደጋጋሚ ሲሰሩ የነበሩ ሥራዎች ስለተበራከቱ እና በአንድ ተጫዋች ወደ አዲስ አበባ መላክ ምክንያት ከቡድን መሪው ጋር ሳንግባባ ስለቀረን ነው ይሄ የተፈጠረው። ከዚህ ውጪ ሌላ የምለው የለም።” ሲሉ አሰልጣኙ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ስታዲየሙን ለቀው ሲወጡ ጠይቀናቸው ይህንን ምላሽ ሰጥተውናል፡፡ የክለቡ ቡድን መሪ አቶ ሲሳይ ተረፈ በበኩላቸው “ምንም ባላደረኩት አሰልጣኙ በቦክስ መትቶኛል። ጉዳዩን ክለቡ ይዞታል። እናም በዚህም መነሻነት አሰልጣኙ የዛሬውን ጨዋታ እንዳይመሩ ተደርጓል።” ሲሉ ለሶከር ኢትዮጵያ ጠቁመዋል፡፡
ገና በሊጉ መጀመሪያ ወቅት በውጤት እጦት ውስጥ የሚገኘው የመዲናይቱ ክለብ ከውጤቱ ባሻገር ተጨማሪ ቡድኑ ሊያውኩ የሚችሉ ጉዳዮች መታየታቸው የክለቡን ቀጣይ እጣ ፈንታ የሚወስኑ መሆናቸው የሚቀር አይመስልም፡፡