የአሰልጣኞች አስተያየት | ሲዳማ ቡና 3-0 ድሬዳዋ ከተማ

ከሱፐር ስፖርት ጋር የነበረው የምሽቱ ጨዋታ ተጋጣሚ አሰልጣኞች ቆይታ ይህንን ይመስላል።

አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ – ሲዳማ ቡና

ጨዋታው እንዳሰቡት ስለመሄዱ

አዎ በትክክል። ማሸነፍ ይጠበቅብን ነበር ዛሬ እንቅስቃስውም ጥሩ ነው። ያለፈው ችግራችንን በተወሰነ መልኩ የቀረፈ ነው ብዬ ነው የማስበው። በቀደም ስንጫወት ብዙ ሙከራ ብናደርግም የአጨራረስ ችግር ነበረብን። ዛሬ ግን አሁንም ሙሉ ለሙሉ ተቀርፏል ባይባልም 3-0 አሸንፎ መውጣት በራሱ ለቡድናችን ትልቅ የሞራል ስንቅ ይሆነናል ብለን እናስባለን።

ስለይገዙ ቦጋለ ቋሚ መሆን

ጥሩ ለውጥ አሳይቷል። ከተጠባባቂነት እየተነሳ ጎል ማግባት በራሱ ብቃት ነው። አሁን ደግሞ ዘጠና ደቂቃ እየጨረሰ ነው። ባለፉት ጊዜያቶች እንደ አጥቂ የጎል ድርቅ ላይ ነበር። ዛሬ ግን በጣም ቀርፏል። ይሄ ብቃት እንዳለው ያሳያል። ስለዚህ ዘጠና ደቂቃ የሚገባው ነው ጥሩ እንቅስቃሴም አድርጓል።

በሁለተኛው አጋማሽ ውጤት ለማስጠበቅ ስለመጫወታቸው

እንደዛ ዓይነት ነገር አልነበረም። ይሄ ተፈጥሯዊ ነው። እየመራህ በሄድክ ቁጥር ብዙ የሚመጡብህ ነገሮች ይኖራሉ። የተለያዩ ተፅዕኖዎች ይፈጠራሉ። እንጂ እኛ 1-0 አስጠብቀን ለመውጣት አላሰብንም። በመጀመሪያው እንደሞከርነው አልነበረም ያስቆጠርነው። በሁለተኛው ግን ብዙ ባንሞክርም ብዙ አግብተናል። ይሄ አጨራረስ ላይ ትንሽ ለውጥ መኖሩን ነው የሚያሳየው።

ደጋፊዎች በአጥቂ ክፍሉ ላይ ስለሚያነሱት ጥያቄ

ጥያቄያቸው ተገቢም ነው ተገቢም ላይሆን ይችላል። በአንድ ጊዜ ወደ አንድ ጫፍ መሄድ አስፈላጊ አይደለም። ለአጥቂ ይህ ሁኔታ የሥነ ልቦና ጫና ይፈጥርበታል። እንደዛ ሆኖም ግን ጎል አግብቷል። አጥቂ ብቻ ሳይሆን አማካይም ያስቆጥራል። ለምሳሌ ፍሬው አስቆጥሯል ከኋላ ተነስቶ። ሌሎችም የሚሞክሩበትን መንገድ ስታይ እንደቡድን ማጥቃት ስትችል ብቻ ነው እንጂ አንድ አጥቂ ላይ ብቻ መንተራስ ተገቢ አይደለም። ግዙፍ የሆነ አጥቂ ለምን አልቆመም ብለህ ማሰብ አይቻልም።

አሰልጣኝ ዘማሪያም ወልደጊዮርጊስ – ድሬዳዋ ከተማ

ውጤት ስላሳጣቸው ምክንያት

መሀል ሜዳ ብልጫ መውሰድ አለብን ብዬ አስብ ነበር። እዛ ቦታ ላይ ነው ክፍተት የነበረው። የሚሻሙ ኳሶች ነበሩ። ያን ከጨዋታ በፊት እንደእቅድ አስገብተን ነበር ግን ተግባራዊ ማድረግ አልቻልንም። ይሄ እንዳለ ነው። ግን በኋላ ላይ ያገኘነው በሥነ ልቦናውም ከኮቪድ ምርመራ ጋር ተያይዞ ችግሮች ስለነበሩ ቡድኑ ውስጥ ተሰምቷል። ተጋጣሚ ቡድን ወረቀት ይዞ አልመጣም። ይሄን በክስ የምንሄድበት ነው የሚሆነው። ከዛ ከዛ ጋር ተያይዞ ልጆቹ ይሄን ስሜት ይዘውታል። አሁን ፕሪንት አድርጉ ብለናል። ፌዴሬሽኑ አንድ ቦታ ተመርመሩ ነው ያለን። በግድ ተመርምረው የመጣ ወረቀት ነው። ያ ልጆቹ ስሜት ውስጥ ገብቶ በሥነ ልቦና እንደጎዳብኝ ነው የተሰማኝ።

ቡድኑ ሙከራዎች ከማድረግ ስለመራቁ

ዕድሎችን መፍጠር አልቻልንም። ባለፈውም ብናሸንፍም ተደጋጋሚ ዕድሎችን የመፍጠር ችግር ይታይብን ነበር። እዛ ቦታ ላይ በደንብ መስራት እንዳለብን ያሳያል። መሀል ላይ ያለን እንቅስቃሴ እና ወደ ፊት ስንሄድ ያለን እንቅስቃሴ ተመሳሳይ አይደለም። ስለዚህ ማጥቃቱ ላይ ይበልጥ መስራት እንዳለብን የሚያሳዩ ነገሮች አሉ። ሦስት ሌሎች የውጪ ዜጎች አሉ እነሱ ተጨማሪ ኃይል ይሆኑናል ብዬ አስባለሁ።

ስለመከላከል ችግራቸው

ከሦስቱ የውጪ ሀገር ተጫዋቾች ውስጥ ተከላካይም አለን። ሁለት አጥቂዎች አንድ ተከላካይ ነው ያለን። በሚቀጥለው ጨዋታ በዚህ መልክ ከጊዮርጊስ ጋር ከቀረብን ተመሳሳይ ስለሚሆን እዛ ላይ የተሻለ ለመንቀሳቀስ እንሞክራለን።

በዳኝነት ውሳኔ ላይ ስላላቸው ቅራኔ

ብዙ ጊዜ እሱን ማንሳት አስቸጋሪ ነው። ሁሉም ያየው ስለሆነ ሰዎች የሚፈርዱት ነው። ግልፅ የሆነ የፔናሊቲ ዕድል ነው ያገኘነው። ያ ቢሆን ኖሮ ጨዋታው ይህንን መልክ አይዝም ነበር። ነገር ግን የዳኞች ውሳኔ ስለሆነ በፀጋ እንቀበላለን።

ያጋሩ