ቅድመ ዳሰሳ | ሀዲያ ሆሳዕና ከ ባህር ዳር ከተማ

ጥሩ ፉክክር እንደሚታይበት የሚጠበቀውን የነገ 9 ሰዓት ፍልሚያ እንደሚከተለው ቃኝተነዋል።

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት የሦስተኛ ቀን ጨዋታዎች ነገ ሲቀጥሉ 9 ሰዓት ሀዲያ እና ባህር ዳር በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ይገናኛሉ። በመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታ በወቅቱ የሊጉ ባለ ክብር ፋሲል ከነማ 3-1 የተረቱት ሀዲያዎች በሜዳም ሆነ ከሜዳ ውጪ ያለባቸውን ክፍተት አርመው የመጀመሪያ ድላቸውን የጣና ሞገዶቹ ላይ ለማስመዝገብ እንደሚያልሙ ይገመታል።

የፋሲሉ ጨዋታ ከመጀመሩ በፊት ከክፍያ ጋር በተያያዘ ውዝግብ ውስጥ የነበረው ሀዲያ ባለቀ ሰዓት በአሠልጣኝ ሙሉጌታ ልመና ተጫዋቾቹን ወደ ሜዳ እንዳስገባ ይታወቃል። ይህ ውዝግብ ጨዋታው ሊጀመር ደቂቃዎች እስኪቀሩት መቀጠሉ ደግሞ በቡድኑ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ተፅዕኖ ያመጣ ይመስላል። የሆነው ሆኖ ቀድሞ ማለቅ ያለበት ጉዳይ ነገም ካልተገባደደ ከፍተኛ ክፍተት ቡድኑ ላይ ሊፈጠር እንደሚችል ይታሰባል። ከዚህ ውጪ ግን ተጫዋቾቹ በዚህ ከባድ የሥነ-ልቦና ደረጃ ላይ ተገኝተው ጨዋታውን አድርገው ያሳዩት እንቅስቃሴ ግን ለወቀሳ የሚዳርጋቸው አይደለም።

ፈጣን የኳስ ቅብብሎችን በሜዳው ቀጥተኛ ክፍሎች ለማድረግ ሲሞክሩ የታዩት ሀዲያዎች ነገም ይህ ፍጥነት የታከለበት ቀጥተኛ አጨዋወታቸው ዋጋ ሊከፍላቸው ይችላል። በተለይ ከወገብ በላይ የሚገኙት ተጫዋቾች ከኳስ እና ከኳስ ውጪ ያላቸው ፍጥነት ለባህር ዳር ተከላካዮች ሀሳብ እንደሚሆን ይገመታል። ከምንም በላይ የቀድሞ ክለቡን የሚገጥመው ባዬ ገዛኸኝ እና ሀብታሙ ታደሠ በመስመሮች መሐከል እና ከተከላካይ ጀርባ እየተገኙ የሚፈጥሯቸው ዕድሎች የሚጠበቁ ናቸው። ይህ ቢሆንም ግን ቡድኑ በፈጣን ሽግግሮች ተጋላጭ ሆኖ ነበር። ይህ ተጋላጭነቱ ካልተቀረፈ ደግሞ አስፈሪው የባህር ዳር የፊት መስመር ሊቀጣው ይችላል።

ሄኖክ አርፊጮን በጉዳት ኤፍሬም ዘካሪያስን ደግሞ በቅጣት ከነገው ጨዋታ ውጪ ያደረጉት ሀዲያዎች ተጨማሪ የገንዘብ ጥያቄ ያነሱት 12ቱ ተጫዋቾቻቸው ነገ ጠዋት ከክለቡ የበላይ አመራሮች ጋር ከክፍያ ጋር በተያያዘ ውይይት የሚያደርጉ መሆኑ ተጠቁሟል (የተወሰነ ክፍያ ግን ትላንት ተፈፅሞላቸዋል)። በውይይቱ ተጫዋቾቹ ከተስማሙ ወደ ሜዳ ገብተው ሊጫወቱ እንደሚችሉም ሰምተናል።

በወረቀት ላይም ሆነ በመጀመሪያው የአዲስ አበባ ጨዋታ ኮስታራ የዋንጫ ተፎካካሪ ቡድን መስሎ የታየው የአሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ ባህር ዳር ከተማ ደግሞ ባገኘውን የአሸናፊነት መንገድ ለመዝለቅ እና አሁንም በደረጃ ሠንጠረዡ አናት ለመቆየት ድልን አስቦ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይታሰባል።

ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት የሚጥረው ባህር ዳር ከተማ ኳስን በዓላማ በቶሎ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለማድረስ ፍላጎት እንዳለው ይታያል። በመጀመሪያው ጨዋታ በርከት ያሉ የማጣቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ወደ ሜዳ በማስገባትም አብዛኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በተጋጣሚ ሜዳ ላይ ለማሳለፍ ሞክሯል። ከምንም በላይ ደግሞ የመስመር ተከላካዮቹ መሳይ እና ግርማ (በሁለተኛው አጋማሽ አህመድ) ፈጣን ሩጫዎችን በማድረግ ጥሩ የማጥቃት አማራጭ ሲፈጥሩ ነበር። ከዚህ ውጪ ዜናው፣ ማውሊ እና ተመስገን ፊት ላይ ቦታ እየተቀያየሩ የተጋጣሚ ተከላካዮችን ትኩረት ለመበታተን ሲያደርጉት የነበረው ጥረት በተወሰነ መልኩ ፍሬያማ ሆኖ ታይቷል። ይህ የቡድኑ የፊት መስመር የተደራጀ የተዘበራረቀ አጨዋወትም ነገም እንደሚደገም ይጠበቃል።

ሦስት ነጥብ እና ሦስት ጎል በሸመቱበት የአዲስ አበባ ከተማው ጨዋታ ብዙም ያልተፈተኑት ባህር ዳሮች ነገ ግን ሜዳ ላይ ጠንካራ ፍልሚያ እንደሚጠብቃቸው እሙን ነው። በተለይ በአዲስ አበባው ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የቡድኑ አማካዮች ማርክ ተደርገው ከራሳቸው ሜዳ መውጣት ሲቸገሩ ታይቷል። ቀስ በቀስ ግን ከገጠማቸው የሰው በሰው አያያዝ አጨዋወት ራሳቸውን ነፃ በማድረግ በመጫወት የግብ ዕድሎችን መፍጠር ጀምረዋል።

በቡድኑ ውስጥ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ውድድር ላይ ጉዳት ያጋጠመው ኤርትራዊው ዓሊ ሱሌይማ ብቻ በእርግጠኝነት ከነገው ጨዋታ ውጪ መሆኑ የተረጋገጠ ተጫዋች ነው። እስካሁን የሥራ ፍቃዱ ያላለቀለት አብዱልከሪም ንኪማ ደግሞ ጠዋት ላይ ጉዳዩ ከተገባደደ ብቻ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ተጠቁሟል።

9 ሰዓት የሚጀመረውን ጨዋታ ፌዴራል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ በመሐል ዳኝነት ሲመሩት ሙስጠፋ መኪ እና ሻረው ጌታቸው ደግሞ ረዳት ዳኞች ናቸው። ማኑየ ው/ጻድቅ ደግሞ የመርሐ-ግብሩ አራተኛ ዳኛ ነው።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች ነገ በሊጉ ለሦስተኛ ጊዜ የሚገናኙ ይሆናል። ቡድኖቹ ዓምና በተገናኙባቸው ሁለት ጨዋታዎችም በተመሳሳይ አንድ ለምንም በሆነ ውጤት ተሸናንፈዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዲያ ሆሳዕና (4-3-3)

መሳይ አያኖ

ብርሃኑ በቀለ – ፍሬዘር ካሳ – ኤሊያስ አታሮ – ኤሊያስ ታምሩ

ሳምሶን ጥላሁን – ተስፋዬ አለባቸው – ፍቅረእየሱስ ተክለብርሃን

ሀብታሙ ታደሠ – ባዬ ገዛኸኝ – ፀጋዬ ብርሃኑ

ባህር ዳር ከተማ (4-3-3)

ፋሲል ገብረሚካኤል

መሳይ አገኘሁ – ሠለሞን ወዴሳ – ፈቱዲን ጀማል – አህመድ ረሺድ

ፍፁም ዓለሙ – አለልኝ አዘነ – ፎዐድ ፈረጃ

ግርማ ዲሳሳ – ኦሲ ማውሊ – ተመስገን ደረሰ

ያጋሩ