ቅድመ ዳሰሳ | ወልቂጤ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ

የጨዋታ ሳምንቱ ሦስተኛ ቀን መዝጊያ የሆነውን ጨዋታ የተመለከቱ ነጥቦችን እንድትካፈሉ ጋብዘናል።

ነገ ምሽት የሚደረገው ይህ ጨዋታ አጥቅቶ መጫወትን የሚያዘወትሩ ቡድኖችን የሚያገናኝ በመሆኑ ጥሩ ፉክክር እንደሚደረግበት ይጠበቃል። ፋሲል ከነማ የማሸነፍ አጀማመሩን የሚያስቀጥልበት ወልቂጤ ከተማ ደግሞ የመጀመሪያ ድሉን የሚፈልግበት መሆኑም ፉክክሩን ከፍ የሚያደርገው ነው።

ፋሲል ከነማ ሀዲያ ሆሳዕናን ባሸነፈበት ጨዋታ ኳስ መስርቶ ከመውጣት ባለፈ ቀጥተኛነትንም እየቀላቀለ መምጣቱን ያሳየ ነበር። ቡድኑ መሀል ሜዳ ላይ እንደልብ ቅብብሎችን ከውኖ ማለፍ ሲቸግረው መሰል መንገዶችን መጠቀም መቻሉ ከተገማችነት የሚያርቀው ነው። የነገው ተጋጣሚውም የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን የሚፈልግ መሆኑ ሲታሰብ ደግሞ አፄዎቹ ነገም ይህንን ባህሪ ሊያሳዩ እንደሚችል የሚያስገምት ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ ሳይጠቀስ የማይታለፈው አማካይ ሱራፌል ዳኛቸው ነው።

ቡድኑ በቅብብል ከራሱ ሜዳ ከወጣ በኋላ በሱራፌል መካከለኛ እና ረጃጅም ኳሶች ደጋግሞ አደጋ መፍጠር እንደሚችል ግብ በማስቆጠር ጭምር አሳይቷል። ይህ መሆኑ አማካዩ የሚወስዳቸው ተመሳሳይ እርምጃዎች በወልቂጤ የኋላ ክፍል በምን መልኩ ምላሽ ይሰጠዋል የሚለው ጉዳይ ነገም ተጠባቂ ነው። ፋሲሎች ለወትሮው የሚታወቁበት ከመስመር ወደ ውስጥ ሰብረው የሚገቡ አጥቂዎቹ ብቃት ለዘብ ማለቱ በተቃራኒው ለወልቂጤ የመስመር ተከላካዮች የማጥቃት ነፃነት ሊሰጥ የሚችልበት ዕድል ይኖራል።

ወልቂጤ ከተማ በጉዳት እና ቅጣት በተከላካይ ክፍሉ ላይ በአንዴ ቢያንስ ሁለት ቅያሪዎችን ለማድረግ የሚገደድ መሆኑ የነገ ትልቁ ፈተናው ነው። ቡድኑ የፋሲል ከነማን የማጥቃት ጥንካሬ በአዳዲስ ጥምረቶች ለመቋቋም የመገደዱ ሁኔታ አማካይ ክፍሉ ይበልጥ ጥንቃቄ ላይ እንዲያተኩር በማድረግ መፍትሄ እንዲሰጥ ሊያደርገው ይችላል። ይህ ደግሞ ገና የሚፈለገው ደረጃ ላይ ያልደረሰውን የቡድኑ የፊት መስመር ውህደት ይበልጥ ሊያላላው ይችላል።

ሠራተኞቹ ሦስት የዘጠኝ ቁጥር ባህሪ ያላቸው እስራኤል ፣ ጌታነህ እና አህመድን በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ መጠቀማቸው ትኩረትን የሚስብ ነበር። ነገር ግን ይህ ነጥብ ከተፈጥራዊ የመስመር አጥቂዎች ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም ያሳጣቸው ይመስላል። በሦስት የኋላ ተከላካይ ከሚጠቀመው ፋሲል ጋር ሲገናኙም በእነዚሁ ተከላካዮች እና በመስመር ተመላላሾች መሀል የሚኖረውን ክፍተት መጠቀም የሚያስችል ባህሪ ያለው የመስመር አጥቂ ሳያስፈልጋቸው አይቀርም። ያ ካልሆነም መከላከሉን ያልዘነጋ ጥሩ የመስመር ተከላካዮች የማጥቃት ተስትፎን ማግኘት የግድ ይላቸዋል።

ወልቂጤ ከተማ ኋላ ክፍሉ ላይ ዮናስ በርታን በጉዳት ረመዳን የሱፍን በቅጣት ያጣል። በሌላው ከባድ እጦት ቡድኑን አማካይ ክፍል ላይ ብልጫ ሊያስወስድበት በሚችል መልኩ አብዱልከሪም ወርቁ በጉዳት ምክንያት ጨዋታው ያመልጠዋል። በፋሲል ከነማ በኩል አሁንም እንደመጀመሪያው ሳምንት ኦኪኪ አፎላቢ እና ይሁን እንዳሻው ለጨዋታው እንደማይደርሱ ተሰምቷል።

ጨዋታውን ፌደራል ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ በመሀል ዳኝነት ይመሩታል።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– አምና በሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙባቸው ሁለት ጨዋታዎች በተመሳሳይ ሁኔታ በፋሲል ከነማ 1-0 አሸናፊነት የተቋጩ ነበሩ።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወልቂጤ ከተማ (4-3-3)

ስልቪያን ግቦሆ

ተስፋዬ ነጋሽ – ዳግም ንጉሴ – ዋሀብ አዳምስ – አበባው ቡታቆ

በኃይሉ ተሻገር – ሀብታሙ ሸዋለም – ያሬድ ታደሰ

እስራኤል እሸቱ – ጌታነህ ከበደ – ጫላ ተሺታ

ፋሲል ከነማ (3-4-3)

ሚኬል ሳማኬ

አስቻለው ታመነ – ያሬድ ባየህ – ከድር ኩሊባሊ

ሰዒድ ሁሴን – ሀብታሙ ተከስተ – ሱራፌል ዳኛቸው – ሳሙኤል ዮሃንስ

ሽመክት ጉግሳ – ፍቃዱ ዓለሙ – በረከት ደስታ