ሪፖርት | የማዉሊ የመጨረሻ ደቂቃ አስደናቂ ግብ ባህር ዳርን ባለድል አድርጋለች

ሦስተኛ ቀኑን በያዘው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ በጭማሪ ደቂቃ ጎል ሀዲያ ሆሳዕናን መርታት ችሏል።

ሀዲያ ሆሳዕና ዑመድ ዑኩሪን በፀጋዬ ብርሀኑ በመተካት ከፋሲሉ ሽንፈት ብቸኛውን የአሰላለፍ ለውጥ አድርገዋል። በባህር ዳር ከተማ በኩል ከአዲስ አበባው ድል መናፍ ዐወል ፣ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ እና አህመድ ረሺድ በመሳይ አገኘሁ ፣ ዜናው ፈረደ እና ተመስገን ደረሰ ቦታ የመሰለፍ ዕድል አግኝተዋል።


የጨዋታው ጅማሮ ተጋጣሚዎች እርስ በእርስ ይፈታተሹ የነበረበት ሆኗል። ባህር ዳሮች ኳስ መስርተው ለመውጣት ሲሞክሩ ሀዲያ ሆሳዕናዎች እዛው አፍኖ ለማስቀረት ሲጥሩ ታይተዋል። 6ኛው ደቂቃ ላይም ሀዲያዎች የባህር ዳርን ቅብብል ከጅምሩ በማቋረጥ ያገኙትን ዕድል ሳምሶን ጥላሁን ከሳጥን ውስጥ መትቶ ለጥቂት ስቷል። ጨዋታው አስር ደቂቃዎችን ከተሻገረ በኋላ የሜዳ ላይ ጥፋቶች በርከት ብለው ማታየት ጀምረው የነበረ ሲሆን የቡድኖቹ የቆመ ኳስ ሙከራዎች ግን አደጋ የሚፈጥሩ አልነበሩም።

በሂደት በቅብብሎቻቸው ገፍተው መሄድ የጀመሩት ባህር ዳሮች ወደ ፍፁም ዓለሙ የግራ ክፍል በማድላት ፈጠን ያሉ ጥቃቶችን መሰንዘር ጀምረዋል። ያም ሆኖ የመጨረሻ ቅብብሎቻቸው ስኬት ሳጥን ውስጥ አደጋ እንዳይፈጥሩ አድርጓቸዋል። ይልቁኑም ሀዲያ ሆሳዕናዎች የማጥቃት የበላይነቱን በመውሰድ በተጋጣሚያቸው አጋማሽ መቆየት ችለዋል። በሙከራ ደተጃም 23ኛው ደቂቃ ላይ የብርሀኑ በቀለን የቀኝ መስመር ተሻጋሪ ኳስ ባዬ ገዛኸኝ በግንባር ገጭቶ ወደ ውጪ ወጥቶበታል።


ሀዲያዎች የተሻለ አስፈሪነት ተላብሰው በታዩባቸው በቀጣይ ደቂቃዎች ባህር ዳሮችም በመልሶ ማጥቃት ወደ ግብ መድረሳቸው አልቀረም። 28ኛው ደቂቃ ላይ ለግብ በቀረበ መልሶ ማጥቃት ከሆሳዕና ሳጥን ደርሰው ፍፁም ዓለሙ ኦሴ ማውሊን ከግብ ጠባቂ ጋር አገናኝቶች የአጥቂው ሙከራ በመሳይ አያኖ ድኗል። የተሻለ ጫና በመፍጠር የቀጠሉት ሀዲያዎችም የአጋማሹን ከባድ ሙከራ 35ኛው ደቂቃ ላይ አድርገዋል። መሀል ለመሀል በከፈቱት ጥቃት ዑመድ ዑኩሪ ከሳምሶን ጥላሁን የተቀበለውን ኳስ ከግቡ ቅርብ ርቀት ሞክሮ ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል።

የዕረፍት ሰዓት በቀረበበት ደቂቃ ባህር ዳሮች አምበሉ ፍቅረሚካኤል ዓለሙን በጉዳት አጥተው በአብዱልከሪም ኒኪማ ልመተካት ተገደዋል። በ42ኛው ደቂቃ ባዬ ገዛኸኝ በሳጥኑ መግቢያ ከቅጣት ምት ያደረገው እና ለጥቂት የወጣው ሙከራም የአጋማሹ የመጨረሻ ሙከራ ሆኗል።

ሁለተኛው አጋማሽ እንደመጀመሪያው በከባድ ሙከራዎች አልታጀበም። ሆሳዕናዎች ኳስ ይዘው ከሜዳ ለመውጣት የሚጥሩበት ሂደት ኳስ በመነጣጠቅ የመሀል ሜዳ ፍትጊያ ቀጥሏል። የመልሶ ማጥቃት ባህሪ የሚነበብባቸው ባህር ዳሮችም የማጥቃት ሽግግራቸው ወደ አስፈሪ ሙከራ ሳይቀየር ቆይቷል። ይልቁኑም የጨዋታ ውጪ እንቅስቃሴዎችን ጨምሮ ቡድኖቹ ጥቃትን በማርገብ በኩል ተመጣጥነው ቀጥለዋል።

ከሁለተኛው የውሀ ዕረፍት በኋላ ጨዋታው በፉክክር ጨምሮ ቢትይም ሙከራዎች ሊታዩ አልቻሉም። ፍትጊያውን ተከትሎ በሚፈፀሙ ጥፋቶች የሚገኙ የርቀት ቅጣት ምቶችም እንደመጀመሪያው ሁሉ ውጤታማ ሲሆኑ አልታየም። በመጨረሻ ደቂቃዎች የተሻለ በተነቃቃው ጨዋታ 85ኛው ደቂቃ ላይ ከፍፁም የግል ጥረት በተገኘ ኳስ ማዉሊ በግራ ከጠባብ አንግል ያደረገው ሙከራ ለመሳይ ከባድ አልነበረም። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ባዬ ገዣኸኝ ከሳጥን ውጪ ለሆሳዕና ለማስቆጠር መሬት ለመሬት የመታው ኳስ ለጥቂት ወጥቶበታል።

በጨዋታው ግብ ለማየት የአንዳቸው ስህተት ይጠበቅ በነበረበት የመጨረሻ ቅፅበት ባህር ዳሮች ወሳኝ ጎል አግኝተውል። በቀኝ የሰነዘሩ ጥቃት በሀዲያዎች በአግባቡ ሳይርቅ ቀርቶ ሰለሞን ወዴሳ ያመቻቸለትን ኦሴይ ማዉሊ ከሳጥኑ መግቢያ ላይ በአስደናቂ ሁኔታ በመግልበጥ የመታው ኳስ ከመረብ አርፏል። ይህች ግብም ባህር ዳርን በስድስት ነጥቦች በሰንጠረዡ አናት አስቀምጣለች። ከግቡ በኋላ የዳኛው ፊሽካ ሰከንዶች ሲቀሩት ፍፁም ዓለሙ ከሆሳዕና ግብ አፋፍ ደርሶ ከብርሀኑ እና መሳይ ጋር በመታገል ለማስቆጠር በጣረበት ቅፅበት ጥፋት ተሰርቶብኛል ቢልም የዕለቱ አርቢትር በዝምታ አልፈውት ጨዋታውም በዛው ተቋጭቷል።