የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዲያ ሆሳዕና 0-1 ባህር ዳር ከተማ

የዕለቱ የመጀመሪያ በነበረው እና በባህርዳር ከተማ አሸናፊነት ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ አሰልጣኞች ተከታዩን ቆይታ ከሱፐር ስፖርት ጋር አድርገዋል።

አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ – ባህር ዳር ከተማ

ስለጨዋታው

“ከውጤት አንፃር የምፈልገውን አግኝቻለሁ ፤ ጨዋታው ግን እጅግ ፈታኝ ነበር በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ሀዲያዎች ወደ እኛ ሜዳ በተደጋጋሚ መግባታቸው እኛን ጫና ውስጥ ከቶን ነበር ግን በውጤቱ ደስተኛ ነበርን።”

በሶስት የመሀል ተከላካይ ስለመጀመራቸው

“ከኃላ ሶስት ተከላካዮችን የተጠቀምኩት የመስመር ተመላላሾቻችን ይበልጥ ወደ መሀል እየገቡ በመሀል ሜዳ ላይ የቁጥር ብልጫ ወስደን በተሻለ መንገድ ኳስ ለመቆጣጠር እና በመስመሮች ለማጥቃት ነበር። በተደጋጋሚ እድሎችን ፈጥረን መጠቀም ሳንችል ቀርተናል።”

በ92ኛው ደቂቃ ስለተገኘችው የማሸነፍያ ግብ

“እጅግ በጣም የሚያስደስት ነው በዚህ አይነት ደቂቃ የማሸነፍያ ግብ ስታስቆጥር የተለየ ስሜት አለው ፤ በውጤቱ እጅግ ተደስቻለሁ ነገር ሀዲያ ሆሳዕና ግን እጅግ ጠንካራ ተጋጣሚ ነበር።”


አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት – ሀዲያ ሆሳዕና

ስለጨዋታው እና ውጤቱ

“ጨዋታው ወደ መጠናቀቁ እንደመቃረቡ እና እንደ ጨዋታው ጥንካሬ እንዲሁም በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ እንደፈጠርናቸው እድሎች ተጠቃሚነት ይኖረን ነበር ፤ ነገርግን በጥቃቅን ስህተቶች ውጤቱን አጥተናል። አቻ ውጤት ቢሆን ኖሮ ግን ለሁለታችንም ፍትሃዊ ይሆን ነበር አሁንም የሚቀሩን ነገሮች አሉ እነሱን አስተካክለው ለቀጣይ ጨዋታዎች እንቀርባለን።”

እድሎችን መፍጠር ቢችሉም ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ስላመቻላቸው

“ዋናው ነገር ግቡ አካባቢ መድረስ መቻላችን ነው ፤ ግን መጨረስ መቻል ደግሞ ሌላኛው ዋነኛ ጉዳይ ነው ስለዚህ አጨራረሳችን ላይ መስራት ይኖርብናል። በተቀረ ተጫዋቾቹ በ90 ደቂቃ የተቻላቸውን በማድረጋቸው ደስተኛ ነኝ።”

ያጋሩ