ሪፖርት | ዐፄዎቹ ሁለተኛ ድል አሳክተዋል

ምሽት ላይ የተደረገው የወልቂጤ ከተማ እና የፋሲል ከነማ ጨዋታ በበዛብህ መለዮ ብቸኛ ግብ ፋሲልን ባለድል አድርጎ ተጠናቋል።

ነጥብ ከተጋሩበት የአዳማ ጨዋታ አንፃር አራት ለውጦችን ያደረጉት ወልቂጤዎች ጉዳት እና ቅጣት የገጠማቸው ዮናስ በርታ እና ረመዳን የሱፍን በውሀብ አዳምስ እና አበባው ቡታቆ ሲተኩ ጫላ ተሺታ እና ያሬድ ታደሰም አህመድ ሀሰን እና እስራኤል እሸቱን ቦታ ወስደዋል። በፋሲል ከነማ በኩል በዛብህ መለዮ በሳሙኤል ዮሀንስ ምትክ ወደ ሜዳ የገባበት ለውጥ ከሀዲያ ሆሳዕናው ድል የተደረገ ብቸኛ ለውጥ ሆኗል።


ከኳስ ጋር መቆየት ምርጫቸው የሆነው ሁለቱ ተጋጣሚዎች በፈጣን እና በፉክክር በተሞላ እንቅስቃሴ ጨዋታውን ጀምረዋል። ፋሲል ከነማ በቀኝ መስመር በሽመክት ጉግሳ እና ሰዒድ ሁሴን የሜዳ ቁመት ጥምረት አድሎቶ ኳሶችን ወደ አጥቂው ፍቃዱ ዓለሙ በቶሎ የማድረስ ሀሳብ ተንፀባርቆበታል። በተመሳሳይ ወልቂጤዎች በቀኝ የጀመረው አጥቂያቸው ጫለ ተሺታን ማዕከል ያደረጉ ጥቃቶች ለመሰንዘር ሞክረዋል። ሆኖም የፋሲል ተጫዋቾች ወደ ኋላ እየተመለሱ ክፍተቶችን መዝጋት የወልቂጤን ጥቃት በሙከራ እንዳይቋጭ አድርጓል።


ጨዋታው በዚህ ሁኔታ ሲቀጥል በሌላኛው ጎል የፋሲል የቀኝ መስመር ጥቃት የአደጋ ምልክት ሲያሳይ ቆይቶ 20ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶለታል። ከግቡ በፊት የሽመክት ተሻጋሪ ኳስ ሳጥን ውስጥ ደርሶ በዳግም ንጋቱ ሲጨረፍ በረከት ደስታ ለማስቆጠር ያደረገውን ጥረት ዳግም ተደርቦበታል። ከዚህ እንቅስቃሴ ቀጥሎ በዛው የቀኝ መስመር ከእጅ ውርወራ የተነሳ ኳስ ሀብታሙ ተከስተ አማካይነት ሲሻማ በዛብህ መለዮ ሮጦ ወደ ውስጥ በመግባት ከዳግም ንጋቱ ቀድሞ ኳስ በመንካት ከመረብ አገናኝቶታል።

ከግቡ በኋላ እስከ ዕረፍት ድረስ ጨዋታው ከባባድ ሙከራዎችን አላሳየንም። ነገር ግን በሁለቱም በኩል የነበረው ፉክክር በመሀል ሜዳ ፍልሚያዎች ታጅቦ ቀጥሏል። ፋሲል ከነማዎች የቀኝ መስመር ጥቃታቸው ቀዝቀዝ ቢልም በቀጥታ ኳሶችን ወደ ፍቃዱ ለማድረስ የሚያደርጓቸው ጥረቶች መታየታቸው አልቀረም። በመልሶ ማጥቃት የፋሲልን የኋላ መስመር ሰብረው ለመግባት ጥረት ሲያደርጉ ቢታይም ጥረቶቻቸው በተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጪ እየሆኑባቸው ነበር። አሁንም ወደ ግራ በዞረው ጫላ በኩል አድልተው በፈጣን ሽግግር ወደ ግብ ለመድረስ ቢጥሩም ያለቀለት የግብ ዕድል ሳያገኙ ጨዋታው ተጋምሷል።


ከዕረፍት መልስ ፋሲል በድጋሚ ከሽመክት ወደ ውስጥ በተላከ እና በበረከት በተመቻቸ ኳስ ግብ ለማግኘት ተቃርቦ ነበር። ሆኖም የህንን የፍቃዱ ዓለሙን ሙከራ ሲልቪያን ግቦሆ በመጭረፍ አድኖታል። ወልቂጤዎችም 50ኛው ደቂቃ ላይ ሲጠብቁት የነበረውን ቅፅበት አግኝተው ነበር። ከጌታነህ የተላከውን ኳስ ይዞ በግራ በኩል የመግባት ዕድል ያገኘው ጫላ ሙከራ ግን በርቀት ወደ ውጪ ወጥቷል። ወልቂጤዎች ወዲያው በዛው አቅጣጫ በከፈቱት ሌላ ጥቃት አብዱልከሪም ወርቁ ሳጥን ውስጥ መግባት ሲችል በያሬድ ባየህ ጥፋት ተስርቶበት ሰራተኞቹ ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው የነበረ ቢሆንም ሚኬል ሳማኬ የጌታነህን ምት ሊያድንበት ችሏል።


ከዚህ በኋላ ፋሲሎች የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ይዘው ክፍተቶችን መፈለግ ምርጫቸው ሆኖ ሲታይ ወልቂጤዎች የመልሶ ማጥቃት ቅፅበቶችን ጠብቀው በመስመሮች የመግባት ምልክት አስይተዋል። ለዚህም አህመድ ሁሴን እና እስራኤል እሸቱን በቀኝ እና በግራ በኩል ለውጠው በማስገባት በአዲስ ኃይል ለማጥቃት ጥረዋል። ሆኖም ቀጣዩ ከባድ ሙከራ በፋሲል በኩል ሲታይ 78ኛው ደቂቃ ላይ ተቀያሪው ሳሙኤል ዮሐንስ ከሳጥን ውስጥ ሞክሮ ወደ ውጪ የሰደደው ኳስ ቡድኑ የተሻለ ክፍተትን ያገኘበት ነበር።


ፋሲሎች አጥቂያቸውን እንደልብ በቅብብሎች ባያገኙም 82ኛው ደቂቃ ላይ የበዛብህ መለዮ ከሳጥን ውጪ ያደረጉት ሙከራ ከባድ የነበረ ቢሆንም ግቦሆ በአስገራሚ ቅልጥፍና አውጥቶበታል። ወደ ማብቂያው ላይ ወልቂጤዎች ረዘም ያሉ ኳሶችን ወደ ፊት በመላክ የአቻነቱን ግብ ፍለጋ ቢቀጥሉም ጨዋታው በፋሲል ከነማ 1-0 እአሸናፊነት ተደምድሟል። ውጤቱንም ተከትሎ ፋሲሎች ነጥባቸውን ከባህር ዳር ከተማ በማስተካከል ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችለዋል።

ያጋሩ