የፈረሰኞቹ አሠልጣኝ ወደ ሀገራቸው አምርተዋል

ከወራት በፊት ቅዱስ ጊዮርጊስን የተቀላቀሉት ዝላትኮ ክራምፖቲች ወደ ሰርቢያ ማምራታቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

የ27 ጊዜ የኢትዮጵያ ቻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ የዘንድሮ የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ከመጀመሩ በፊት ሰርቢያዊውን አሠልጣኝ ዝላትኮ ክራምፖቲችን መሾሙ ይታወቃል። የ64 ዓመቱ አሠልጣኝ ቡድኑን ሙሉ የቅድመ ውድድር ዝግጅት ካሰሩት በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ የተሳተፉ ሲሆን በውድድሩም ሦስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል። ከመዲናው ውድድር በኋላ የጀመረው የሀገራችን ትልቁ የሊግ እርከን ውድድር ላይም ከቀናቶች በፊት ከሰበታ ከተማ ጋር የመጀመሪያ ጨዋታቸውን አድርገው ነጥብ ተጋርተው መውጣታቸው አይዘነጋም። በነገው ዕለት ደግሞ ትልቁ ደርቢ እንደሆነ የሚነገረው የሸገር ደርቢ ጨዋታ ይጠብቃቸዋል።

ከሰበታው ጨዋታ በኋላ እስከ ትናንት ድረስ ቡድኑን ልምምድ ሲያሰሩ የነበሩት አሠልጣኙ ዛሬ ከሰዓት በነበረው ልምምድ ላይ እንዳልተገኙ አውቀናል። ምክንያቱን ለማጣራት የሞከረችው ሶከር ኢትዮጵያም አሠልጣኙ “ወላጅ አባቴ አርፏል” በሚል ከቡድኑ ጋር በአሁኑ ሰዓት እንደሌሉ አውቀናል። አሠልጣኙም በገጠማቸው ሀዘን ጠዋት ከሀዋሳ ወደ አዲስ አበባ የመጡ ሲሆን ወደ ሀገራቸው ሰርቢያም እንዳመሩ ተረድተናል።

አሠልጣኙ የስንት ቀን እረፍት እንደተሰጣቸው ባናውቅም በነገው የሸገር ደርቢ ጨዋታ ግን እንደማይኖሩ ተረጋግጧል።