የአሰልጣኞች አስተያየት | ወልቂጤ ከተማ 0-1 ፋሲል ከነማ

የምሽቱ ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ የነበረው የአሰልጣኞች እና የሱፐር ስፖርት ቆይታ ይህንን ይመስል ነበር።

አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ – ፋሲል ከነማ

በጨዋታው ስለመፈተናቸው

ሁሌም ለቻምፒዮንነት ስትጫወት እንዲህ ዓይነት ነገሮች ያጋጥማሉ። ወልቂጤዎች የሚችሉትን ሞክረዋል። በተለይ መሀል ላይ የነበራቸው አደረጃጅት ጥሩ ነው። እኛም አንዳንዴ ብቅ እልም የምንለው ነገር አለ እሱን ማስተካከል ይገባናል። ግን ጠንካራ ቡድን ነው እንዲህ ዓይነት ጨዋታዎችን አሸንፎ ውጤት መያዝ ራሱ ትልቅ ዋጋ አለው። በአጠቃላይ ውጤቱ አስፈላጊ ስለነበር እሱን ማግኘታችን ጥሩ ሆኖ ያሉንን ስህተቶች ግን እያረምን እንደምንሄድ እርግጠኛ ነኝ።

ሳማኬ ስላዳነው ፍፁም ቅጣት ምት

ሰዓቱም እየሄደ ስለነበር ያ ፔናሊቲ ቢገባ ኖሮ የበለጠ የወልቂጤ ተነሳሽነት ይጨምራል። እኛም ጋር ትንሽ የሚፈጥረው ነገር ነበር። ማዳኑ የጨዋታው አካል ነው። ሳማኬ ባለፉት ዓመታት ለክለቡ ትልቅ ሥራ የሰራ ነው። እና ማዳኑ የእኛን ቡድን አንስቶታል። አንዳንዴ ቡድኑ እንኳን እምቢ እያለው በግብ ጠባቂዎች ኃይል ቡድን ሊወጣ ይችላል ፤ በዓለምም የምናየው ነገር ነው። ስለዚህ ያደረገው ነገር መልካም ነገር ነው።

በተከላካይ መስመሩ ላይ መስተካከል ስላለበት ድክመት

ወደፊት አምሳሉም ይመጣል። ዛሬ የተጫወትነው በአራት ተከላካይ ነው። ግን ኩሊባሊ ወደ ፊት አይሄድም ነበር ፤ የቆመ ነበር። እና በዛ በኩል ድክመት ሊኖር ይችላል። ምክንያቱም ሦስት ተከላካይ ሲኖር ግራ እና ቀኙ ጥሩ ፍሰት ሊኖረው ይገባል። እና በዛ በኩል ያጣነው ነገር አለ፤ ወደፊት የሚታይ ነገር ነው።

አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው – ወልቂጤ ከተማ

ስለጨዋታው

የመጀመሪያው 15-20 ደቂቃ የጥንቃቄ ጉድለት ስለነበረብን አጋጣሚ ያ ኳስ ሥርዓቱን ባልጠበቀ መልኩ ተወርውሮ ተቆጥሮብናል። ያም ችግር አልነበረውም መጀመሪያም እንደተናገርኩት 90 ደቂቃ አጥቅተን ነው የተጫወትነው።

ስለፍፁም ቅጣት ምቱ መሳት

ምንም ችግር የለውም እኛ ብዙ ፍፁም ቅጣት ምት እንደምናገኝ ጨዋታችን በግልፅ ይናገራል። ስለዚህ የፍፁም ቅጣት ምቱ መሳት አይደለም በአጠቃላይ በነበረው እንቅስቃሴ ቡድኔ ላይ ትልቅ ተስፋ ሰጪ ነገር ተመልክቻለሁ። እና በጣም ደስተኛ ነኝ።

ስለተደረጉ የተጫዋች ለውጦች

መጀመሪያ የገቡ ልጆችም መጥፎ ነገር አላሳዩም። ኳስ መስርተው ለመጫወት ሞክረውል። በኋላም ደግሞ ጉልበት እንደሚያስፈልግ አውቀን የቀየርናቸውም ልጆች ጥሩ ነገር ነው ያሳዩን። እና ብዙ አልተከፋሁም።