ቅድመ ዳሰሳ | ሰበታ ከተማ ከ መከላከያ

ነገ 9 ሰዓት የሚደረገውን የሰበታ እና መከላከያን ጨዋታ የተመለከተ ዳሰሳ እንደሚከተለው ተሰናድቷል።

በአሠልጣኝ ዘላለም ሽፈራው የሚመራው ሰበታ ከተማ በሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ተጫውቶ አንድ ነጥብ ይዞ መውጣቱ ይታወሳል። ነገ ደግሞ ከአዲስ አዳጊው መከላከያ ጋር በመፋለም የመጀመሪያ ሦስት ነጥቡን ለማግኘት እንደሚታትር ይጠበቃል።

ከፈረሰኞቹ ጋር ሲጫወቱ አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያደርጉ ሙሉ ለሙሉ መከላከል ላይ ያተኮረ አጨዋወት የተከተሉት ሰበታ ከተማዎች ነገ ከዛ የተለየ ባህሪ ተላብሰው ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይታሰባል። በተለይ ደግሞ በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ውድድር ላይ ቡድኑን ሲጠቅም የነበረው አጥቂው ናንጄቤ ከስራ ፍቃድ ጋር የተገናኙ የወረቀት ጉዳዮችን በማገባደዱ ነገ ለቡድኑ ትልቅ ጥቅም እንደሚሰጥ ይታሰባል። ዋነኛ የማጥቃት አጨዋወታቸውም አጥቂው ላይ ያነጣጠረ እንደሚሆን እና ረጃጅም ኳሶችም ያካተተ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል። በተለይ ደግሞ አጥቂው ከዚህ በፊት የነበረበትን የአጨራረስ ችግር ቀርፎ መታየቱ ለቡድኑ ትልቅ ተስፋን የሚሰጥ ነው።

እንደ ቡድን የተጫወቱበት መንገድ፣ ክፍተቶችን ለተጋጣሚ ተጫዋቾች የነፈጉበተ ጥረት እና አይደክሜነታቸው ነገም ከተደገመ ግባቸውን በቀላሉ ላያስደፍሩ ይችላሉ። በቡድኑ በኩል ከላይ እንደገለፅነው ጁኒያንስ ናንጄቤ የሥራ ፍቃድ በማግኘቱ ለጨዋታው ዝግጁ ሲሆን መሐመድ አበራ ግን በጉዳት ምክንያት ከጨዋታው ውጪ ነው። ዘላለም ኢሳይያስ እና አክሊሉ ዋለልኝ የመግባታቸው ጉዳይ ደግሞ አጠራጣሪ ነው። ከዚህ ውጪ በሀይሉ ግርማ ደግሞ ከቅጣት መልስ ቡድኑን ለማገልገል እንደተዘጋጀ ተገልፆልናል። በአንፃሩ አንተነህ ተስፋዬ በቅጣት ጨዋታው ያልፈዋል።

ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዘንድሮ ያደጉት መከላከያዎች የውድድር ዓመቱን በድል እንደጀመሩ ይታወቃል። ነገም በአርባምንጭ ከተማ ላይ የተቀዳጁትን ድል ደግመው በአሸናፊነት መንፈስ ለመዝለቅ ተግተው ወደ ሜዳ እንደሚገቡም ያታሰባል።

ከፍተኛ አካላዊ ፍትጊያዎች፣ የአየር ላይ እና ተሻጋሪ ኳሶች በበዙበት የመጀመሪያው ጨዋታ ሦስት ነጥብ ያሳካው ቡድኑ ነገም ይህ አይነት አጨዋወት እንደሚጠብቀው ይገመታል። በተለይ ተጋጣሚው ሰበታም ተመሳሳይ እንቅስቃሴ ሊከተል ስለሚችል የመጀመሪያው ጨዋታ በሌላ መርሐ-ግብር ሊደገም ይችላል። በዋናነት ግን ቡድኑ ኦኩቱ ኢማኑኤልን ያማከለ ቀጥተኛ እና ተሻጋሪ ኳሶችን በተደጋጋሚ በመሞከር አስፈሪነቱን ሜዳ ላይ ሊያሳይ ይችላል።

በታታሪነት የማይታማው መከላከያ በሁለቱም ሽግግሮች ላይ ስል መሆኑ ለሰበታ የራስ ምታት ነው። በተለይ ቢኒያም በላይ መሐል ለመሐል የሚያደርገው እንዲሁም በግራ መስመር በኩል ሊሰለፍ ከሚችለው ግሩም ሀጎስ እና በቀኝ መስመር ቦታ ሊያገኝ ከሚችለው ሰመረ ሀፍታይ ጋር በመሆን ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን ሊያደርጉ ይችላሉ። ነገርግን ወገቡ አካባቢ መጠነኛ ጉዳት አስተናግዶ የነበረው ግሩም ነገ በሙሉ ጤንነቱ የመጫወቻ ዕድል ማግኘቱ የተረጋገጠ አይደለም። እርግጥ ትናንት እና ዛሬ ተጫዋቹ ከአጋሮቹ ጋር መደበኛ ልምምድ ቢሰራም ነገ ጠዋት በህክምና ሰዎች የመሰለፉ ነገር ውሳኔ እንደሚያገኝ ሰምተናል።

ይህንን ጨዋታ ፌዴራል ዳኛ ሄኖክ አክሊሉ በዋና ዳኝነት ሲመሩት ፋንታሁን አድማሱ እና እሱባለው መብራቱ ደግሞ በረዳት እንዲሁም ዮናስ ካሳሁን በአራተኛ ዳኝነት እንደተመደቡ ታውቋል።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች ከ11 የውድድር በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ በፕሪምየር ሊጉ የሚገናኙ ሲሆን ከዚህ ቀደም ስድስት ጊዜ የግንኙነት ታሪክ አላቸው። መከላከያ 3 ጊዜ ሲያሸንፍ ሰበታ ከተማ አንድ አሸንፎ በቀሪዎቹ ሁለቱ አቻ ተለያይተዋል። ጦሩ 7፤ ሞግሌዎቹ 5 ጎሎችን አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሰበታ ከተማ (4-3-3)

ለዓለም ብርሃኑ

ጌቱ ኃይለማርያም – በረከት ሳሙኤል – ወልደአማኑኤል ጌቱ – ኃይለሚካኤል አደፍርስ

ሳሙኤል ሳሊሶ – ክርዝስቶም ንራምቢ – አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ

ዱሬሳ ሹቢሳ – ጁኒንያንስ ናንጄቤ – ዘካሪያስ ፍቅሬ

መከላከያ (4-2-3-1)

ክሌመንት ቦዬ

ዳዊት ማሞ – አሌክስ ተሰማ – ኢብራሂም ሁሴን – ገናናው ረጋሳ

ላሬይ ኢማኑኤል – ደሳለኝ ደባሽ

ኤርሚያስ ኃይሉ – ቢንያም በላይ – ሰመረ ሀፍታይ

ኦኩቱ ኢማኑኤል

ያጋሩ