የሉሲዎቹ አሠልጣኝ እና አምበል ከነገው ጨዋታ በፊት መግለጫ ሰጥተዋል

“በቻልነው አቅምም ጨዋታው ላይ ጎሎችን አግብተን ለማሸነፍ እንጥራለን” ብርሃኑ ግዛው

“እኔ፣ ሴናፍ እና መዲና በአሁኑ ሰዓት የተሻለ ደረጃ ላይ ያለን አጥቂዎች ነን” ሎዛ አበራ

ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ዳግም ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለመመለስ የማጣሪያ ጨዋታዎችን ማድረግ የጀመረው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታውን ከዩጋንዳ አቻው ጋር እንዲከውን መደልደሉ ይታወቃል። ቡድኑም ባሳለፍነው ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታውን ወደ ዩጋንዳ ካምፓላ አምርቶ ያደረገ ሲሆን የሁለት ለዜሮ ሽንፈትም አስተናግዶ ተመልሷል። የመልሱን ጨዋታ ደግሞ በነገው ዕለት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የሚያደርግ ይሆናል። ከወሳኙ ጨዋታ በፊት ደግሞ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው እና አምበሏ ሎዛ አበራ ወሎ ሠፈር በሚገኘው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። በቅድሚያም አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው በመጀመሪያው ጨዋታ ቡድናቸው ያሳየውን ጠንካራ እና ደካማ ጎን በመግለፅ ንግግራቸውን ጀምረዋል።

“በመጀመሪያው ጨዋታ ኳስ ለመጫወት ሙከራ አድርገናል። ተቃራኒ ቡድንንም በልጠን ለመጫወት ጥረናል። እንዳያችሁት ጎሉ የገባብን በጊዜ ነው። በዛ ጎል ሳንረበሽ ቀሪውን ደቂቃ ለመጫወት ጥረናል። ይህ ደግሞ ጥሩ ነገር ነው። ጨዋታውን ለማሸነፍ የነበረን ስሜትም ጥሩ ነበር። የአካል ብቃትም ችግር አልነበረብንም።” ካሉ በኋላ “ቡድኔ ላይ ግን የመናበብ ችግር አይቻለሁ። በሁሉም ቦታዎች ላይ ተናቦ የመጫወት ችግር ነበር። ከዚህ ውጪ በስነ-ልቦና ረገድም ጠንካራ አልነበረም።” የሚል ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

አሠልጣኙ ቀጥለው ዩጋንዳ በኮሳፋ ውድድር ላይ ተሳትፎ የመጣ እና ከውድድር ያልራቀ ቡድን መሆኑን አመላክተው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግን አቋሙን እንዳይገመግም ጠቃሚ ጨዋታዎችን እንዳላደረገ ጠቁመዋል። “ተጋጣሚያ ቡድናችን ከውድድር የመጣ ቡድን ነው። ደቡብ አፍሪካ ላይ በነበረ የሴካፋ ውድድር ሲሳተፍ ነበር። እኛ ደግሞ የሀገር ውስጥ ውድድር ካደረግን 8 ወር ሆኖናል። የወዳጅነት ጨዋታ ካደረግንም 5 ወር ተቆጥሯል። እነሱ ግን በሁለት ዓመት ውስጥ በሜዳ እና ከሜዳ ውጪ 12 የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን አድርገዋል።” ከዚሁ ከአቋም መፈተሻ ጨዋታ ጋር አያይዘውም “የመጀመሪያው ጎል ሲገባብን ትንሽ የመረባበሽ ነገር ተፈጥሮብን ነበር። ከ20 ደቂቃ በኋላ ግን ወደ ጨዋታ መጥተን ነበር። ይህ የሆነው ደግሞ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ባለማግኘታችን ይመስለኛል።” ሲሉ ተደምጠዋል።

አስከትለው ስለ ነገው ጨዋታ ያወሩት አሠልጣኙ ውጤቱን ለመገልበፅ በሜዳቸው የሚችሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። “ከዩጋንዳ ከመጣን በኋላ ተጫዋቾቹ ላይ ያለውን የሥነ-ልቦና ጫና ለማሳደግ ስንጥር ነበር። ልምምድ ከመጀመራችን በፊትም ቋሚ ከነበሩት ተጫዋቾች ጋር በደንብ ቁጭ ብለን የነበረውን ክፍተት አውርተናል። በቀጣይም ምን ማድረግ እንዳለብን ተነጋግረናል። ተጫዋቾቹን ብቻ ሳይሆን እኛ የአሠልጣኝ ቡድን አባላትም የነበሩ ክፍተቶችን ተነጋግረናል። ከነገው ጨዋታ በፊትም የመጀመሪያው የጨዋታ ፊልም አውርደን አይተን ተነጋግረናል። ስለዚህ ውጤቱን ለመገልበፅ ያለንን ሁሉ እናደርጋለን።” በማለት ተናግረዋል።

በቀጣይ ደግሞ በስፍራው የተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት ለአሠልጣኙ እና ለአምበሏ የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተዋል።

ነገ ጨዋታ ስለሚያደርጉበት የአበበ ቢቂላ ሜዳ?

“ሜዳውን መቀበል ግዴታችን ነው። ምንም አማራጭ የለንም። የባህር ዳር ስታዲየም ለእኛ አጨዋወት ይመች ነበር። ይህ የአበበ ቢቂላ ሜዳ ለተጫዋቾቻችን እንደሚያስቸግር እንረዳለን። ይህ ሳይኮሎጂካሊም ይረብሻል። ምክንያቱም በዚህ ሜዳ እጫወታለሁ ብለን ተዘጋጅተህ ባለቀ ሰዓት በመለወጡ። ዞሮ ዞሮ ባለው ነገር ለመጫወት እንሞክራለን። በቻልነው አቅምም ጨዋታው ላይ ጎሎችን አግብተን ለማሸነፍ እንጥራለን። ከተጫዋቾቻችንም ጋር ያለውን ነገር እንዲቀበሉ ተነጋግረናል።”

ቡድኑ ላይ ስለነበረው የመከላከል ችግር?

“በመከላከሉ ላይ ያለው ችግር እንደ ሀገር ይመስለኛል። ከ17ዓመት በታች ጀምሮ ሊሰራበት የሚገባ ነው።”

የወዳጅነት ጨዋታ ስላለማድረጋቸው?

“ከወንዶች ጋር የተጫወትነው ምንም አማራጭ ስለሌለን ነው። የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንንም ጠይቀን ነበር። ፌዴሬሽኑም ከተለያያዩ ሀገራት ጋር እንድንጫወት ጥሮ ነበር። ነገርግን አልተሳካም። አማራጭ ስለሌለን ነው ከወንዶቹ ጋር የተጫወትነው። ጠቃሚ ጨዋታ ባለማድረጋችንም የተወሰነ ተጎድተናል። ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከውድድር መምጣት እንደውም የተወሰነ ጠቅሞናል።”

ነገ ምን ይጠበቅ?

“እግርኳስ ላይ ስህተቶች አይጠፉም። ነገም ስህተቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ግን የስህተቶቹን ደረጃ መቀነስ ይጠበቅብናል። ነገ ምንም አማራጭ የለንም። ማሸነፍ አለብን። ዛሬ የነበረው ልምምድ ላይም ተጫዋቾቹ ጋር የነበረው ስሜት ጥሩ ነበር። በአጠቃላይ በቻልነው አቅም ውጤቱን በሜዳችን ቀልብሰን ለማለፍ እንሞክራለን።”

 

በመጨረሻ የብሔራዊ ቡድኑ አምበል ሎዛ አበራ ተከታዩን ስትል ተደምጣለች።

“እኔ፣ ሴናፍ እና መዲና አሁን ላይ የተሻለ ደረጃ ላይ ያለን አጥቂዎች ነን። አሠልጣኛችን እንዳለውም በመጀመሪያው ጨዋታ ቡድኑ ላይ ትንሽ የመግባባት እና ያለመናበብ ችግር ነበር። ከዚህ ውጪ ያገኘናቸውንም አጋጣሚዎች ሳንጠቀምበት ቀርተናል። እኔንም ጨምሮ የሳትናቸው ኳሶች ነበሩ። አሁን ግን ቪዲዮውን አይተን ስህተቶቻችን ላይ ተነጋግረናል። ስለዚህ በነገው ጨዋታ የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ይኖረናል ብዬ አስባለሁ። ስነ-ልቦናችንንም ላይ የነበረውን ችግር ቀርፈናል። ስለዚህ ነገ የተሻለ ነገር ይኖረናል ብዬ አስባለሁ።”