ቅድመ ዳሰሳ | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ኢትዮጵያ ቡና

እጅግ በከፍተኛ ጉጉት የሚጠበቀው የሸገር ደርቢን ጨዋታ እንደሚከተለው ቃኝተነዋል።

በሀገራችን ከሚደረጉ የደርቢ ጨዋታዎች መካከል ግንባር ቀደሙ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ነው። ሁለቱ ቡድኖችም ነገ ለ43ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሚያደርጉት ጨዋታ ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም የሚደረግ ይሆናል።

በሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታ ከሰበታ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርተው የወጡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ነገ ከሦስት ነጥብ ጋር ለመገናኘት ጥረት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። በተለይ የከተማ ተቀናቃኛቸው ላይ የዓመቱ የመጀመሪያ ድላቸውን ማስመዝገብን አልመው ወደ ሜዳ እንደሚገቡም ይታመናል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሰበታ ከተማ ጋር በመጀመሪያ ሳምንት ባደረገው ጨዋታ ከተጋጣሚው የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት ይኑረው እንጂ ወደ ሳጥኑ የደረሰባቸው አጋጣሙዎች አጥጋቢ አልነበሩም። ወደቀጥተኛ አጨዋወቱ የተመለሰ የሚመስለው ጊዮርጊስ በተለይም የመስመር አጥቂዎቹን መዳረሻ ባደረጉ ኳሶች በቶሎ ወደ ግብ ለመድረስ ሲሞክር ታይቷል። እርግጥ ነው የነገው ተጋጣሚው ኳስ መስርቶ መውጣት ላይ የሚያተኩር በመሆኑ ከሰበታው ጨዋታ የተሻለ ክፍተት ሊያገኝ ይችላል።

ነገ በቡና ሜዳ ላይ ተበራክቶ እንቅስቃሴውን ለማፈን መሞከርም ከፈረሰኞቹ የሚጠበቅ ትልቅ ጉዳይ ነው። ነገር ግን ይህን በማድረግ ሂደት ውስጥ ጫና ከሚያሳድረው የቡድኑ ክፍል ኋላ ያለውን ቦታ በጥንቃቄ መሸፈን የግድ ይለዋል። በሰበታው ጨዋታ የከፋ ጥቃት ያላገኘው የጊዮርጊስ የመከላከል አደረጃጀት ነገ ጠንከር ባለ ጨዋታ ከመፈተኑ አንፃር አቡበከር ናስርን የያዘው ተጋጣሚው ክፍተት እንዳያገኝ ጥንቃቄ አዘል የኋላ መስመር አወቃቀር እንደሚኖረው ይገመታል።

ድረ-ገፃችን ከደቂቃዎች በፊት በሰራችው ዘገባ የቡድኑ አሠልጣኝ ዝላትኮ ክራምፖቲች ወላጅ አባታቸው በማረፋቸው ምክንያት ወደ ሀገራቸው ሰርቢያ ማምራታቸውን ጠቁማለች። ይህንን ተከትሎ የ64 ዓመቱ አሠልጣኝ ከመዲናችን ውጪ ለሁለተኛ ጊዜ የሚደረገው የሸገር ደርቢ ጨዋታ ላይ ቡድናቸውን አይመሩም። ከዚህ ውጪ ናትናኤል ዘለቀ እና ሳላዲን በርጌቾ በጉዳት ምክንያት ነገ የማይሰለፉ ተጫዋቾች መሆናቸውን ተረድተናል።

እንደ ተጋጣሚያቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጀመሪያው ጨዋታ ያለ ጎል አቻ የተለያዩት ኢትዮጵያ ቡናዎች የመጀመሪያ ሦስት ነጥብ አግኝተው ደረጃቸውን ለማሻሻል ትግል እንደሚያደርጉ እሙን ነው። በተለይ በሲዳማው ጨዋታ እምብዛም በማጣቃቱ ላይ ያልተሳተፈው ቡድኑ ነገ ታሪካዊውን ጨዋታ በመርታት ወደ አሸናፊነት መንገድ እንደሚገባ ይጠበቃል።

በሲዳማ ቡናው ጨዋታ ያለ ወሳኝ ተጫዋቹ አቡበከር ናስር ወደ ሜዳ የገባው ኢትዮጵያ ቡና ነገ የአምበሉን ግልጋሎት ማግኘቱ ትልቅ ነገር ነው። አቡበከር ሜዳ ላይ መኖሩ ደግሞ የተጋጣሚን የመከላከል ትኩረት ስለሚስብ እሱ እና አጋሮቹ የተሻለ ክፍተት ሊያገኙ ይችላሉ። ከምንም በላይ ተጫዋቹ ቅልጥፍናውን እና ፍጥነቱን ተጠቅሞ ከሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች በተጨማሪ ጀርባውን ለጎል ሰጥቶ አጋሮቹን በእንቅስቃሴ በማሳተፍ ወደ ሳጥን እንዲገቡ የሚያረግበት መንገድ ለፈረሰኞቹ ተከላካዮች የራስ ምታት ነው።

ቡና ከሜዳው ኳስ መስርቶ ሲወጣ የሚደርስበት ጫና አሁንም መቀጠሉ እና ለስህተት ሲዳርጉት መታየቱ ነገ የአሠልጣኝ ካሳዬ ሀሳብ እንደሚሆን ይታሰባል። በተለይ የአማካይ ክፍሉ ጥንካሬ ከአምናው ቀንሶ መታየቱ ደግሞ ለዚህ ትልቁን ድርሻ የሚወስድ ይመስላል። ነገ ይህ የመሐል ክፍል ተጠናክሮ ካልቀረበም ቡድኑ አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል።

በቡናማዎቹ በኩል ሚኪያስ መኮንን ልምምድ ቢጀምርም ለነገው ጨዋታ እንደማይደርስ ሲታወቅ በቅጣት ከመጀመርያው ሳምንት ጨዋታ ያልነበረው አቡበከር ናስር ግን ወደ ሜዳ የሚመለስ ይሆናል።

በጉጉት የሚጠበቀውን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው በመሐል ዳኝነት ሲመሩት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ይበቃል ደሳለኝ እና ዳንኤል ጥበቡ የመስመር ዳኞች ናቸው። ዳንኤል ግርማይ ደግሞ የመርሐ-ግብሩ አራተኛ ዳኛ ነው።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– በዚህ ታላቁ ደርቢ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና 42 ጊዜ ተገናኝተዋል። በእነዚህ ግንኙነቶች ጊዮርጊስ 19 ጊዜ ድል ሲቀናው ቡና ደግሞ 7 ጊዜ አሸንፏል። ቀሪውን ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

– በ42ቱ የሁለቱ ቡድኖች ግንኙነት 79 ጎሎች መረብ ላይ አርፈዋል። 52ቱን ግብ በማስቆጠር ፈረሰኞቹ ቀዳሚ ሲሆኑ ቡናማዎቹ ደግሞ 27 ኳሶችን ከመረብ አዋህደዋል።

ግምታዊ አሠላለፍ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-3-3)

ቻርለስ ሉክዋጎ

ሄኖክ አዱኛ – ምኞት ደበበ – ኤድዊን ፍሪምፖንግ – ቸርነት ጉግሳ

ሀይደር ሸረፋ – በረከት ወልዴ – ከነዓን ማርክነህ

አማኑኤል ገብረሚካኤል – ኦጎሮ ኢስማኤል – አቤል ያለው

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

አቤል ማሞ

ኃይሌ ገብረትንሳኤ – ወንድሜነህ ደረጄ – አበበ ጥላሁን – አሥራት ቱንጆ

ታፈሠ ሰለሞን – አማኑኤል ዮሐንስ – ዊልያም ሰለሞን

አቡበከር ናስር – እንዳለ ደባልቄ – አቤል እንዳለ