ከስምንት ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሚሳተፍበት የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የተጫዋቾች ቁጥርን የተመለከተ አዲስ ህግ መውጣቱ ተገልጿል።
33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከጥቂት ወራት በኋላ በካሜሩን አስተናጋጅነት እንደሚከናወን ይታወቃል። በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ ብሔራዊ ቡድኖችም ቀድመው የተለዩ ሲሆን የምድብ ድልድሉም ወጥቷል። በወጣው ድልድል መሠረት ደግሞ በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከውድድሩ አስተናጋጅ ካሜሩም፣ ኬብ ቨርዴ እና ቡርኪናፋሶ ጋር መመደቡ ይታወሳል። ትልቁ የአህጉራችን ውድድር ከመጀመሩ በፊት ደግሞ ካፍ ከተጫዋቾች ቁጥር ጋር በተገናኘ አዲስ መመሪያ ማውጣቱን ለአባል ሀገራቱ አስታውቋል።
የካፍ የውድድር ዳይሬክተር ሳምሶን አዳሙ የካፍ የሥራ-አስፈፃሚ ኮሚቴ ያስተላለፈውን ውሳኔ በፊርማው አረጋግጦ ለብሔራዊ ፌዴሬሽኖች በላከው ደብዳቤ ላይ ከጥር 1 ጀምሮ እስከ ጥር 29 ድረስ በሚደረገው ውድድር ላይ የሚሳተፉ ብሔራዊ ቡድኖች ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ የተጫዋች እጥረት እንዳይገጥማቸው የሚይዟቸው 23 ተጫዋቾች ላይ የ5 ተጫዋች ጭማሪ እንዲያደርጉ ይፈቅዳል። ብሔራዊ ቡድኖቹ አምስቱን ተጨማሪ ተጫዋቾች የመያዝ ግዴታ ባይኖርባቸውም በፍቃዳቸው መያዝ ከፈለጉ ግን የጉዞ፣ ማረፊያ እንዲሁም ተያያዥ ወጪዎችን እራሳቸው እንዲሸፍኑ እንደሚደረግም በደብዳቤው ተብራርቷል።
ካፍ በቡድኖች ስብስብ ውስጥ የሚገኙ ተጫዋቾችን ቁጥር ወደ 28 ቢያሳድግም በጨዋታ ላይ ግን የሚቀየሩ ተጫዋቾች ሦስት ሆነው ብቻ እንደሚቀጥሉ (30 ደቂቃ ጭማሪ ካለ 1 ተጨማሪ ተጫዋች መቀየር ይቻላል) አመላክቷል።