ከፍተኛ ሊግ | ሀላባ ከተማ አራት ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የነባሮችን ውል አድሷል

የቀድሞው አሰልጣኙ አላምረው መስቀሌን በድጋሚ ዋና አሰልጣኝ አድርጎ የሾመው ሀላባ ከተማ ነባር እና አዳዲስ ተጫዋቾችን እያስፈረመ ይገኛል።

ነጋሽ ታደሰ ከፈራሚዎቹ መካከል ነው። የአጥቂ አማካዩ ከዚት ቀደም በሀዋሳ ከተማ እና ወላይታ ድቻ የተጫወተ ሲሆን ባለፈው ውድድር ዓመት አጋማሽ ወደ ሀምበሪቾ አምርቶ ከተጫወተ በኋላ ወደ በርበሬዎቹ ያመራ ተጫዋች ሆኗል።

ዳግም በቀለ ሌላው ፈራሚ ሆኗል። የቀድሞው የነገሌ ቦረና፣ ወላይታ ድቻ እና ሀዲያ ሆሳዕና የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች ያለፈውን የውድድር ዓመት በሀምበሪቾ ያሳለፈ ሲሆን ለዚህ የውድድር ዓመት አዲሱ የበርበሬዎቹ ፈራሚ ሆኗል።

ፍራኦል መንግሥቱ ሦስተኛው አዲስ ፈራሚ ነው። የቀድመው የወላይታ ድቻ፣ ጅማ አባ ጅፋር፣ ሀዲያ ሆሳዕና እና ኤሌክትሪክ የስመር ተከላካይ የአሰልጣኝ አላምረው መስቀሌ ምርጫ በመሆን ቡድኑን ተቀላቅሏል።

ዐምና በጋሞ ጨንቻ ያሳለፈው የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ደሳለኝ አሎ ለክለቡ ፊርማውን ያኖረ ሌላው አዲስ ተጫዋች ነው።

ቡድኑ ከአዳዲሶች በተጨማሪ የነባር ተጫዋቾችን ውል አራዝሟል። ግብ ጠባቂው ንጉሥ ሙሉጌታ፣ የቀኝ መስመር ተከላካዩ ቴዎድሮስ ወልዴ እና አማክዩን ሠዒድ ግርማ ለ1 ዓመት ውል ማደሳቸውን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል።

ያጋሩ