ምሽት ላይ በተደረገው የሸገር ደርቢ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ ቡናን 4-1 በመርታት የመጀመሪያ ሦስት ነጥቡን ጨብጧል።
ሁለቱም ቡድኖች ከመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታቸው ሦስት ለውጦችን አድርገዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ባህሩ ነጋሽን በቻርለስ ሉኩዋጎ ከነዓን ማርክነህ እና ቡልቻ ሹራን በዓላዛር ሽመልስ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል ቀይሮ አስገብቷል። ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ወንድሜነህ ደረጄ ፣ ሥዩም ተስፋዬ እና ዊሊያም ሰለሞንን በቴዎድሮስ በቀለ ሮቤል ተክለሚካኤል እና አቡበከር ናስር ተክቶ ጨዋታውን ጀምሯል።
ጨዋታው የደርቢ ስሜት ያለው ፈጠን ያለ አጀማመርን አሳይቷል። እንቅስቃሴውም በአመዛኙ በቡና ሜዳ ላይ የቆየ ነበር። ቡናዎች ኳስ ይዘው በቅብብል ከሜዳ ለመውጣት የሚያደርጉት ጥረት በጊዮርጊሶች ንቁ ጫና አጋማሹን በተፈለገው መንገድ እንዳያልፍ ተደርጓል። አምስት ያህል ተሳላፊዎቻቸውን ወደ ቡና ሳጥን አስጠግተው እንቅስቃሴውን እዛው በማስቀረት የተሳካላቸው ጊዮርጊሶች በቶሎ ወደ ሳጥን ለመድረስ የሚያደርጉት ጥረት ቢታይም ወደ ከባድ ሙከራ መቀየር አልቻሉም። 10ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ናስር ከርቀት ካደረገው የቅጣት ምት ሙከራ ውጪ በጨዋታው አደጋ ያለው ኳስ ሳይታይ ቀጥሏል።
በዚህ ሁኔታ እየሄደ የነበረው ጨዋታ 20ኛው ደቂቃ ላይ ያልተጠበቀ ጎል ተቆጥሮበታል። የቡናው ተከላካይ አበበ ጥላሁን ጉዳት ሲገጥመው ኳሱን ወደ ውጪ አውጥቶ የህክምና እርዳት ሊያገኝ ከሜዳ ወጥቷል። ጨዋታው ሲቀጥልም የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች የእጅ ውርወራው በስፖርታዊ ጨዋነት እንደሚመለስላቸው እየጠበቁ ሳለ ሀይደር ሸረፋ ከእጅ ውርወራ የተቀበለውን ኳስ በታሰበው መንገድ ወደ ቡና ሳጥን ሲልከው ቶጓዊው አጥቂ ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ ማንም ሳይጠብቀው ተነጥሎ በመውጣት ኳሱ አቤል ማሞ ጋር ሳይደርስ አግኝቶ ጎል አድርጎታል። ሁኔታው በኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ከፍተኛ ተቃውሞ ቢገጥመውም ጎል ሆኖ መፅደቁ ግን አልቀረም።
ጨዋታው ከውሀ ዕረፍት ከተመለሰ በኋላ የቡና ቅብብሎች ቀስ በቀስ ወደ ጊዮርጊስ ሳጥን መጠጋት ጀምረዋል። ቡድኑ አቡበከር ባለበት የግራ መስመር አድልቶ ለመፍጠር የሞከራቸው ጫናዎች በሙከራ የታጀቡት ግን ወደ መጨረሻው ላይ ነበር። 43ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ከግማሽ ጨረቃው አቅራቢያ ከቅጣት ምት የመታው ኳስ አግዳሚ ገጭቶ ወጥቷል። ጭማሪ ደቂቃ ላይ ደግሞ ታፈሰ ሰለሞን ከግራ መስመር ያሻገረውን ጥሩ ኳስ አቡበከር እና ሮቤል በሚያስቆጭ መልኩ ሳይደርሱበት ቀርተው ወደ ውጪ ወጥቷል።
ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለተኛ ግብ አስቆጥሯል። ቡናዎች ከኋላ ኳስ ሲጀምሩ በተፈጠረ ስህተት አበበ ኳስ ለማራቅ ሲሞክር አማኑኤል ዮሐንስ ላይ የተደረበውን ኳስ ያገኘው ቡልቻ ሹራ ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ ቢመለስም መልሶ በግንባሩ ማስቆጠር ችሏል። 48ኛው ደቂቃ ላይም ከነዓን ማርክነህ ነፃ አቋቋም ላይ ሆኖ ከአቤል ያለው የደረሰውን የማዕዘን ምት በቀጥታ ወሰ ግብ ልኮት ለጥቂት ስቷል።
57ኛው ደቂቃ ላይ ደርቢው ሌላ ውዝግብ አስተናግዷል። በጊዮርጊስ ሜዳ ላይ አቤል ያለው በታፈሰ ሰለሞን ላይ በሰራው ጥፋት መነሻነት በተጫዋቾች መሀል ግርግር ተነስቶ አቤል እና እንዳለ ደባልቄ የቢጫ ካርድ ሰለባ ሆነዋል። ጨዋታው በቅጣት ምት ሲቀጥልም ወደ ጊዮርጊስ ሳጥን የተላከውን የታፈሰ ቅጣት ምት ዘሎ ለመያዝ የሞከረው ባህሩ ነጋሽ ኳስ ከእጁ ሲያመልጠው አግኝቶ እንዳለ አስቆጥሯል። ግብ ጠባቂው ሲዘል ጥፋት ተሰርቶበታል የሚለው የጊዮርጊሶች ቅሬታ ተቀባይነት ሳይኖረው ቀርቶም ጎሉ ፀድቋል።
ጨዋታው ሞቅ ብሎ ሲቀጥል ቡናዎች ከኳስ ጋር በርከት ብለው በጊዮርጊስ ሳጥን አቅራቢያ የሚታዩባቸው ቅፅበቶች ። አማኑኤል ገብረሚካኤል እና የአብስራ ተስፋዬን ቀይረው ያስገቡት ቅዱስ ጊዮርጊሶችም ቀጥተኛ ኳሶችን ወደ ፊት በመጣል አደጋ ለመፍጠር ጥረታቸውን ቀጥለዋል። በጥሩ ፉክክር የቀጠለው ጨዋታ አደገኛ ቅፅበቶችን እያሳየን ያለከባድ ሙከራ ቢቀጥልም 79ኛው ደቂቃ ላይ የቅዱስ ጊዮርጊስ መልሶ ማጥቃት ግብ አስገኝቷል።
ጊዮርጊስ በግራ መስመር በቡልቻ ሹራ አማካይነት የከፈተውን መልሶ ማጥቃት ቡናዎች በአግባቡ ሳያርቁት ቀርተው ሀይደር ሸረፋ አማኑኤል ያስቀረለትን ኳስ ይዞ ወደ ሳጥኑ በመድረስ ተከላካዮችን አታሎ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል። ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ተቀይሮ የገባው ደስታ ደሙ በኃይሌ ገብረትንሳይ ጥፋት ተሰርቶበት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ሀይደር በድጋሚ በማስቆጠር ልዩነቱን ሦስት አድርሶታል።
ተቀዛቅዞ ወደ ፍፃሜው ባመራው ጨዋታ ጭማሪ ደቂቃ ላይ አቡበከር ናስር ተቀይሮ ከገባው ሚኪያስ መኮንን ከደረሰው ኳስ ያደረገው ሙከራ ወደ ላይ ሲነሳ ከቅጣት ምት ያደረገው ሌላ ሙከራም በባህሩ ጥላሁን በቀላሉ ተይዞ ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ 4-1 አሸናፊነት ተቋጭቷል።