በቀጣይ ዓመት በሚደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ የመልስ የማጣሪያ ጨዋታቸውን አዲስ አበባ ላይ ያደረጉት ሉሲዎቹ በመለያ ምት ተሸንፈው ወድቀዋል።
በመጀመሪያው ጨዋታ ሁለት ለምንም ተረተው የተመለሱት ሉሲዎቹ ከተሸነፉበት ጨዋታ ሦስት ለውጦችን አድርገው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በዚህም አሠልጣኝ ብርሃኑ መስከረም ካንኮ፣ እፀገነት ብዙነህ እና ህይወት ደንጊሶን በትዝታ ኃይለሚካኤል፣ ብዙዓየሁ ታደሠ እና ብርቱካን ገብረክርስቶስ ለውጠው ጨዋታውን ቀርበዋል።
በርከት ያሉ የግብ ሙከራዎች በተስተናገዱበት የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች የሀይል ሚዛኑን ወደ ራሳቸው አድርገው ሲጫወቱ ታይቷል። ከዩጋንዳ ቀድመውም እጅግ ለግብ የቀረበ ጥቃት ፈፅመዋል። በዚህም በ6ኛው ደቂቃ ሎዛ አበራ ከወደ ቀኝ መስመር የተሰነጠቀላትን ኳስ በመጠቀም ወደ ግብ የመታችው ኳስ የግቡ ቋሚ መልሶባታል። የተመለሰውን ኳስ ደግሞ ሴናፍ ዋቁማ አግኝታው ሳትጠቀምበት ቀርታለች። ይህንን የተመለሰ ኳስ የሞከረችው ሴናፍ ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ለመዲና አወል ጥሩ ኳስ ያመቻቸች ቢሆንም ግብ ጠባቂዋ የመዲናን ኳስ ይዛባታለች።
ከጅምሩ ጫናዎች ያየለባቸው ዩጋንዳዎች በ14ኛው ደቂቃ ከወደ ግራ የተገኘን የቅጣት ምት በመጠቀም የመጀመሪያ ጥቃታቸውን አድርገዋል። ከዚህ በተጨማሪም በጨዋታው ጥሩ ጥሩ ዕድሎችን ስትፈጥር የነበረችው ናሉኬንጌ ጁሊየት በ21ኛው ደቂቃ በግንባሯ ቡድኗን መሪ ልታደርግ ነበር። ከአንድ ደቂቃ በኋላ ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ መሪነት የተሸጋገረበትን ኳስ በሴናፍ ዋቁማ አማካኝነት አስቆጥሯል።
ረጃጅም ኳሶችን አዘውትረው ሲጠቀሙ የነበሩት ዩጋንዳዎች ወዲያው ወደ ጨዋታው ለመመለስ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ በፋውዚያ ንጂምባ አማካኝነት ሙከራ አድርገው መክኖባቸዋል። በተጨማሪም በ28ኛው ደቂቃ ተቀይራ የገባችው ናሉጊያ ሌላ ጥቃት ፈፅማ የግቡ አግዳሚ መልሶባታል። ሉሲዎቹ በተቃራኒ በ33ኛው ደቂቃ በአምበላቸው ሎዛ አማካኝነት ሁለተኛ ግብ አስቆጥረው አጋማሹን በጥሩ ሁኔታ አገባደዋል።
ምንም እንኳን በመጀመሪያው አጋማሽ በጥሩ ብቃት ሲጫወቱ የታዩት የአሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ተጫዋቾች በሁለተኛው ግማሽ በአንፃሩ ተዳክመው ታይተዋል። በተቃራኒው ዩጋንዳዎች የተወሰደባቸውን ብልጫ ለመመለስ ታትረው በመጫወት ሉሲዎቹን ማስጨነቅ ይዘዋል። በ59ኛው ደቂቃም በኮሙንታሌ አማካኝነት የአጋማሹን የመጀመሪያ ሙከራ ሰንዝረው ተመልሰዋል።
እንደመጀመሪያው አጋማሽ በርከት ያሉ ሙከራዎች ባላስተናገደው በዚህ አጋማሽ ኢትዮጵያዎች እስከ መጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ድረው አስደንጋጭ ሙከራ አላደረጉም። ዩጋንዳዎች ግን ከዛ በፊት በ78ኛው ደቂቃ ናሉኬንጌ ጁሊየት የግል ጥረቷን ተጠቅማ ወደ ግብ በመታችው ኳስ ጨዋታውን ሊገድሉ ነበር። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ አምስት ደቂቃዎች ሲቀሩት ሴናፍ ሁለት ሙከራዎችን አከታትላ አድርጋ መክኖባታል። በጭማሪው ደቂቃ ደግሞ ዩጋንዳዎች በአስፈሪ አካሄድ ሳጥን ተገኝተው እጅግ አስደንጋጭ ጥቃት ሰንዝረዋል።
ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው 2-0 በመጠናቀቁ የድምር ውጤቱ 2-2 መሆኑን ተከትሎ አሸናፊውን ለማወቅ የመለያ የፍፁም ቅጣት ምት ተሰጥቷል። በተሰጠው የመለያ ምትም ሎዛ አበራ፣ አረጋሽ ካልሳ፣ ህይወት ደንጊሶ እና ብርቱካን ገብረክርስቶስ ስተው ዩጋንዳዎች 2-1 ማሸነፍ ችለዋል።