በኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ የሆነው አዳማ ከተማ በወጣለት ፕሮግራም መሠረት ልምምድ መስራት አለመቻሉን በማንሳት ቅሬታ እያሰማ ይገኛል።
የ2014 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ከአስር ቀናት በፊት በሀዋሳ ከተማ መጀመሩ ይታወሳል። በሁለቱ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብር ከወልቂጤ ከተማ እና ጅማ አባጅፋር ጋር የተጫወተው አዳማ ከተማም አራት ነጥቦችን ሰብስቦ 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ከነገ በስትያ 12 ሰዓት ደግሞ ሦስተኛ ጨዋታውን ከወላይታ ድቻ ጋር በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ያደርጋል።
ለዚህ ጨዋታ ዝግጅት ላይ የሚገኘው ክለቡ ዛሬ ረፋድ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ባወጣለት መርሐ-ግብር መሰረት በግብርና ኮሌጅ ሜዳ ልምምዱን ለመስራት ወደ ሥፍራው ቢያመራም ሜዳው ላይ መግባት እንዳልቻለ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ አንበስ መገርሳ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል። “የሊጉ የበላይ አካል ለሁሉም ክለቦች በሰራው ድልድል መሠረት ክለባችን ዛሬ ከ4 ሰዓት እስከ 6 ሰዓት ድረስ በግብርና ኮሌጅ ሜዳ ልምምድ እንዲሰራ መርሐ-ግብር ወጥቷል። እኛም ተጫዋቾቻችንን ይዘን ሜዳው ላይ ልምምዳችንን ለመስራት ስፍራው ብንደርስም በጥበቃ አካላት ወደ ሜዳው እንዳንገባ ተነግሮናል። ይህ በጣም የሚያበሳጭ ነገር ነው።” በማለት ሀሳባቸውን ለድረ-ገፃችን ሰጥተዋል።
አቶ አንበስ አያይዘውም “የሚገርመው በስፍራው የነበሩ የጥበቃ አካላት ፕሮግራም የወጣልን እኛን ከልክለው ሲዳማ ቡናዎች ያለ ፕሮግራማቸው ሜዳ ገብተው እንዲለማመዱ አስገብተዋቸዋል። ይህ በጣም የሚያስነውር ነገር ነው። ይህንን ተከትሎ ዓርብ ወሳኝ ጨዋታ ቢጠብቀንም ልምምድ መስሪያ ሜዳ አጥተን ወደ ማረፊያ ሆቴላችን ለመመለስ ተገደናል።” ብለውናል።
ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የውድድር እና ሥነ-ስርዓት ኮሚቴ ሰብሳቢ ወገኔ ዋልተንጉስን (ዶ/ር) አግኝተን የአዳማዎችን ቅሬታ አቅርበንላቸው ይህንን ብለውናል። “እኛ ፕሮግራም አውጥተናል። ሁሉም ክለብ በፕሮግራም ነው የሚስተናገደው። አሁን የተፈጠረው ክፍተት ከምን እንደመጣ በትክክል ባላውቅም ለማስተካከል ኮሚቴያችን እየሰራ ነው።” ብለውናል። ዶ/ር ወገኔ ጨምረው ምናልባት ግን ከመለማመጃ ሜዳ ኪራይ ክፍያ ጋር ተያይዞ ክፍተቱ ሊፈጠር እንደሚችል ጠቁመው በቶሎ ችግሩ እንደሚቀረፍ አመላክተዋል።