ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 2ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

የሁለተኛ የጨዋታ ሳምንት ዓበይት በክለቦች ዙርያ ያተኮረ ፅሁፎች የመጀመሪያው ፅሁፋችን አካል ናቸው።

👉 በስጋት የተሞላው የኢትዮጵያ ቡና መፃኢ ጊዜ

በአሰልጣኝ ካሣዬ አራጌ መሪነት ኢትዮጵያ ቡና በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በሊጉ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ እንዲሁም ምንም እንኳን ጉዞው በጊዜ ቢገታም ከአስር ዓመታት በኋላ ዳግም በአፍሪካ ውድድር ላይ ተሳታፊ መሆን የሚያስችል ውጤትን ይዞ ማጠናቀቁ አይዘነጋም። አሰልጣኙ ከያዘው ስብስብ እና ከተያዘው የአራት ዓመት ውጥን አንፃር ከዕቅድ በላይ የሚባል አፈፃፀም አስመዝግቦ ማጠናቀቅ ችሏል። ይህን ተከትሎ ቡድኑ ለክብሮች የሚፋለም (ለአሸናፊነት) ለሚያደርገው ጉዞ የቀሩት ጥቂት የመሰላል እንጨቶችን ወደ ላይ ለመውጣት የሚረዱ አይነተኛ ድጋፎች በክለቡ አመራሮች በኩል እንደሚደረግ ቢጠበቅም በክረምቱ የሆነው ግን ከዚሁ በተቃራኒ ነበር።

ከምክትል አሰልጣኝ ዘላለም ፀጋዬ ቆይታ ዙርያ የነበሩትን እሰጥ አገባዎች እንኳን ትተን ክለቡ በመልካም የምልመላ አካሄድ ወደተሻለ ተጫዋችነት የቀየራቸውን አቤል ከበደ ፣ ሀብታሙ ታደሰ ፣ ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን ፣ ተክለማርያም ሻንቆ ፣ ኢያሱ ታምሩ የመሰሉ ወሳኝ ሚናን ባለፉት ዓመታት ለቡድኑ ይወጡ የነበሩ ተጫዋቾች እንደዋዛ ወደ ሌሎች ክለቦች አምርተዋል። ተጫዋቾቹን ማጣቱ በራሱ ችግር ላይሆን ቢችልም ቡድኑ ተጫዋቾቹን ለመተካት የሄደበት ርቀት ግን እጅግ ደካማ ነበር።

ከጅምሩ በአህጉራዊ ውድድር ለመሳተፍ እየተንደረደረ የሚገኝ ቡድን በተቻለ መጠን ቁልፍ ተጫዋቾቹን አቆይቶ በእነሱ ላይ የተወሰነ የቡድኑን ጥራት ከፍ ማድረግ የሚችሉ ዝውውሮችን በማድረግ ቡድኑን ማሳደግ ሲገባው በተቃራኒው በኢትዮጵያ ቡና የሆነው ግን ቁልፍ ተጫዋቾችን በሌሎች ክለቦች ተነጥቆ በምትካቸው ከለቀቁት ተጫዋቾች አንፃር በጥራት ደረጃቸው ዝቅ ያሉ ተጫዋቾችን ማስፈረም በራሱ የክለቡ ፍላጎት (Ambition) ላይ ጥያቄ እንዲነሳ የሚያስገድድ ነው። ለዋንጫ የመጫወት ዕቅድ ያላቸው ቡድኖች በዚህ መንገድ ተጫዋቾች አቅማቸውን አሳይተው ወደ ሌሎች ክለቦች የሚሸጋገሩበት (Platform Club) ከሆኑ ሀሳባቸው በሀሳብ መቅረቱ የግድ ይሆናል።

በክለቡ በኩል ለዚህ ጉዳይ በምላሽነት የሚቀርቡ የተለያዩ ጉዳዮች ቢኖሩም ቡድኑ ዐምና በውስን አቅርቦት ተስፋ ሰጪ ነገር እንደማሳየቱ ይበልጥ ተጠናክሮ ለመቅረብ የክለቡ ኃላፊዎች የተሻለ መንቀሳቀስ ይገባቸው ነበር የሚለው ጉዳይ የሚያግባባ ነው። በተለይ መጫወት ለሚፈልገው የጨዋታ መንገድ የቴክኒክ ክህሎታቸው ላቅ ያሉ ተጫዋቾች እንደሚያስፈልጉ የቡድኑ የዐምና ጉዞ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነበር። ነገርግን በዝውውር መስኮቱ ክለቡ ያመጣቸው ተጫዋቾች ከጥቂቶቹ በስተቀር የአሰልጣኙን የጨዋታ መንገድ ማሳደግ የሚችሉ ስለመሆናቸው ያጠራጥራል።

የካሣዬ አራጌ መምጣትን ተከትሎ ቡድኑ በተጫዋቾች ላይ የሚፈልገውን ብቃት (Skill Set) የሚያሟሉ ተጫዋቾችን ከታችኞቹ ሊጎች ሆነ ከዕድሜ ክርከን ቡድኖች እና በፕሪምየር ሊጉ ተሳታፊ ከነበሩ ቡድኖች ከተለመደው ወጣ ባለ የምልመላ ሥርዓት ተጫዋቾችን ሲያመጣ ብንመለከትም ዘንድሮ በዚህ ረገድ በሚገባው ልክ ሰርቷል ማለት አይቻልም። ይህ ሒደት በራሱ ተጫዋቾች የሊጉን ባህሪ ተላምደው አቅማቸውን ለማሳየት የሚወስደው ሒደት በውስንነት የሚነሳ ቢሆንም ፤ በዘንድሮው የክረምቱ የዝውውር መስኮት ክለቡን የተቀላቀሉት ተጫዋቾች ከጥቂቶቹ በስተቀር የአሰልጣኙ ተቀዳሚ ምርጫዎች ነበሩ ብሎ ለመውሰድ የሚያስቸግሩ ዝውውሮችን ተመልክተናል።

የጨዋታ ሀሳብን ሜዳ ላይ ለመተግበር በሚያስችሉ ተጫዋቾች ካልተደገፈ በስተቀር ሀሳቡ በራሱ አሸናፊ አያደርግም። በኢትዮጵያ ቡና ቤት እየሆነ ያለውም ይህ ነው። የጨዋታ ሀሳቡን አንድ እርምጃ ወደፊት ለማራመድ የሚረዱ ጥራታቸው የላቁ ተጫዋቾች ቡድኑ ውስጥ በሌሉበት እና የጨዋታ መንገዳቸው ለስህተቶች የተጋለጠ እንደመሆኑ ስህተቶችን ለመቀነስ የሚረዱ የተሻሉ ተጫዋቾችን ባልያዘበት ውጤታማ እንዲሆን መጠበቅ አዳጋች ነው። ይባስ ብሎ ገና ከወዲሁ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ቡድኑ ስር የሰደደ የስብስብ ጥልቀት እንዳለበት እየታየ እና በአማራጮች ዙርያ ጥያቄዎች እየተነሱበት ይገኛል። ታድያ ይህ ቡድን በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ ሆኖ በምን መልኩ ወደፊት ይጓዛል የሚለው ጉዳይ የሚጠበቅ ነው።

👉 የአዲስ አበባ አስፈሪ አጀማመር እና ድራማዊ ክስተት

የፕሪምየር ሊጋችን ያለፉት ዓመታትን የደረጃ ሰንጠረዡን በአስተውሎት ለተመለከተ ደካማ የሊግ አጀማመር አድርገው ቀስ በቀስ ከዚህ አጀማመር አገግመው በሊጉ የቆዩ አዲስ አዳጊ ቡድኖች ማግኘት የሚታሰብ አይደለም። ይልቁኑ ደካማ አጀማመር ያደረጉ ቡድኖች ከውጤት መጥፋት ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ በፈርጀ ብዙ ችግሮች ተፈትነው በስተመረሻም ወደታችኛው ሊግ ሲወርዱ እንመለከታለን። እርግጥ መሰል አስተያየቶችን ለመስጠት ጊዜው ገና ቢመስልም ዛሬ ላይ ቀላል የሚመስሉ የነጥብ መጣሎች እና የነጥብ ልዮነት በኃላ በሊጉ ለመቆየት በሚደረገው ትግል ልዩነት ፈጣሪ እንደመሆናቸው ሁሉም የሊጉ ምዕራፎች በእኩል ትኩረት መታየት ግን ይኖርባቸዋል።

አዲስ አበባ ከተማ ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊጉ ከመምጣታቸው አስቀድሞ የመጀመሪያን ተሳትፎ ካደረጉበት የ2009 የውድድር ዘመን በቂ ትምህርት ግን የወሰዱ አይመስልም። ይህንን ሀሳብ ለመደገፍ በርካታ መዘርዝሮች ማቅረብ ይቻላል።

ለጊዜው ዝርዝር ጉዳዮቹን ትተን ቡድኑ የዘንድሮው ቀዳሚ እቅዱ ከሆነው በሊጉ የመቆየት ውጥን አንፃር በመጀመሪያዎቹ ሁለት የጨዋታ ሳምንታት ሽንፈቶችን አስተናግዷል።  ይህ ብዙም የሚያስደነግጥ ባይሆንም ከወዲሁ ግን ከሌሎች ክለቦች ጋር የነጥብ ልዩነቶች እየተፈጠሩ መምጣታቸው በኋላ ላይ በተለይ ውድድሩ እየከረረ ሲመጣ እንደቀልድ ያጧቸው ነጥቦች ቆይታቸውን አስቸጋሪ እንዳያደርጉባቸው የሚያሰጋ ነው። በመሆኑም በአፈጣኝ ውጤቶችን ማስመዝገብ ካልጀመረ ከወዲሁ እጅግ ፈታኝ የውድድር ዘመን እንደሚጠብቀው ለመናገር ነብይ መሆን አይጠይቅም።

ሌላው ቡድኑ ከሜዳ ላይ ካሉ ጉዳዮች ውጭ ከሜዳ ውጭ ባሉ ጉዳዮችም እየተፈተነ እንደሚገኝ ማሳያው በአሰልጣኙ እና በቡድን መሪው መካከል የተፈጠረ አለመግባባት ነው። በሁለተኛ የጨዋታ ሳምንት አዲስ አበባ ከተማ አርባምንጭ ከተማን ከገጠመበት ጨዋታ መጀመር አስቀድሞ አዲስ አበባ ከተማዎች ባረፉበት ሆቴል ውስጥ በዋና አሰልጣኛቸው እስማኤል አቡበከር እና ቡድን መሪያቸው ሲሳይ ተረፈ መካከል በተፈጠረ አምባጓሮ አሰልጣኙ ጨዋታውን ሳይመሩ መቅረታቸው ጉዳይ አንዱ የጨዋታ ሳምንቱ መነጋገርያ ነበር።

ከአለመግባባት እስከ ቡጢ መማዘዝ በደረሰው የቅድመ ጨዋታ ሁኔታ መነሻነት ክለቡ በጊዜያዊነት አሰልጣኙን በማገዱ አሰልጣኝ እስማኤል ጨዋታውን ከተመልካች ጋር ሆነው እንዲከታተሉ ተገደዋል በምትኩም የክለቡ ምክትል አሰልጣኝ ደምሰው ፍቃዱ ቡድኑን ሲመሩ ተመልክተናል።

አሰልጣኝ እስማኤል ስለጉዳዩ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት ሀሳብ “ቡድኑን ለመከፋፈል በተደጋጋሚ ሲሰሩ የነበሩ ሥራዎች ስለተበራከቱ እና በአንድ ተጫዋች ወደ አዲስ አበባ መላክ ምክንያት ከቡድን መሪው ጋር ሳንግባባ ስለቀረን ነው ይሄ የተፈጠረው። ከዚህ ውጪ ሌላ የምለው የለም።” ሲሉ በተቃራኒው ቡድን መሪው ደግሞ “ምንም ባላደረኩት አሰልጣኙ በቦክስ መትቶኛል። ጉዳዩን ክለቡ ይዞታል። እናም በዚህም መነሻነት አሰልጣኙ የዛሬውን ጨዋታ እንዳይመሩ ተደርጓል።” ሲሉ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

ቡድኑ በሜዳ ላይም ሆነ ከሜዳ ውጪ ያሉበትን ፈርጀ ብዙ ችግሮችን በጊዜ ቀርፎ ወደ ውጤት የማይመለስ ከሆነ የመዲናይቱ ክለብ በመጣበት ዓመት እንደ 2009 የውድድር ዘመን ሁሉ ወደ ከፍተኛ ሊግ ላይመለስበት የሚችልበት ምክንያት የለም።

👉 ሲዳማ ቡና ሌላኛው ጠንካራ ተፎካካሪ?

ሲዳማ ቡና በ2003 ወደ ፕሪምየር ሊግ ካደገበት ጊዜ አንስቶ በሊጉ የጠንካራ ተፎካካሪነት ታሪክ የነበረው ቡድን ቢሆንም አምና ግን ሳይጠበቅ ላመውረድ ሲንገራገጭ ብሎም በሁለተኛው ዙር መሻሻሎችን በማሳየት በሊጉ ቆይታውን ማረጋገጡ አይዘነጋም።

ቡድኑ በአሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ እየተመራ የዓምናውን መንገራገጭ ድንገተኛ የአንድ የውድድር ዘመን ጉዳይ እንጂ ቡድኑ ለተፎካካሪነት የተዘጋጀ መሆኑን የሚያስመሰክሩ ጠንካራ ዝውውሮችን ፈፅሞ አዲሱን የውድድር ዘመን ጀምሯል። በዚህም ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ በአራት ነጥብ ምንም ግብ ሳይቆጠርበት ጠንካራ የውድድር ዘመን አጀማመርን እያደረገ ይገኛል።

በመጀመርያው የሊግ ጨዋታ በርከት ያሉ የጠሩ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ቢችሉም በአጥቂዎቻቸው ደካማ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ወደ ግብነት መቀየር ሳይችሉ ቀሩ እንጂ በጨዋታው እንደነበራቸው የበላይነት ማሸነፍ በተገባቸው ነበር። በተመሳሳይ በሁለተኛው የድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ሲዳማ ቡና ተጋጣሚያቸውን ወደ ራሳቸው ሜዳ እንዲገፉ በማድረግ በሙሉ ዘጠና ደቂቃዎች በእንቅስቃሴ በሙከራ የበላይ ሆነው 3-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል።

በሜዳው የተለያዩ የሜዳ ክፍሎች ሰፊ አማራጮችን ይዘው ወደ ውድድር የገቡት ሲዳማ ቡናዎች ዘጠኝ ቁጥር ቦታ ላይ ግን በዓመት ከአስራ አምስት የተሻገሩ ግቦችን ማስቆጠር የሚችል ራሱን ያስመሰከረ አጥቂ ሳይዙ ውድድሩን እንደመጀመራቸው ብዙ ጥያቄዎች ሲናሳባቸው ነበር። በጫናዎች ውስጥ ሆኖ የውድድር ዘመኑን የጀመረው የፊት አጥቂያቸው ይገዙ ቦጋለ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ሁለት ግቦችን ማስቆጠር መቻሉ ግን ለተጫዋቹም በራስ መተማመኑን ከማሳደግ ባለፈ ለቡድኑ የተሻለ የማጥቃትን አቅምን ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።

እርግጥ የውድድር ዘመኑ ገና ሁለተኛ ጨዋታ ቢሆንም በሁለቱ ጨዋታዎች እንደተመለከትነው ሲዳማ ቡና ከያዘው ስብስብ ጥራት እና የአሰልጣኝ ደረጃ በአሰደናቂ የደጋፊዎቹ ድባብ ታግዞ ከየትኛውም ቡድን ጋር አንገት ለአንገት ለመተናነቅ የሚያስችል መነሳሳት እየፈጠረ የሚገኝ ቡድን ይመስላል።

👉 ባህርዳር ከተማ ተፈትኖም ቢሆን አሸንፏል

በመጀመርያው ጨዋታ ከተሻለ የሜዳ እንቅስቃሴ ጋር አዲስአበባ ከተማን ማሸነፍ የቻሉት ባህርዳር ከተማዎች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ እጅግ በተፈተኑበት የሀዲያ ሆሳዕናው ጨዋታ በመጨረሻ ደቂቃ ባስቆጠሩት ግን አሁንም አሸንፈው መውጣት ችለዋል።

ጠንካራ እና ተወዳዳሪ የሆኑ ቡድኖች የውድድር ዓመቱን ሙሉ በአስደናቂ ብቃት ሁሉን ጨዋታዎች ያሸንፋሉ ተብሎ ባይገመትም። አሸናፊ ቡድኖች ከሌሎች መደበኛ ቡድኖች የሚለዩት ጥሩ የጨዋታ ቀን ባላሳለፉባቸው ጨዋታዎች እንኳን በአንዳች መንገድ ከጨዋታው ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዘው የሚወጡበትን መንገድ ማግኘት መቻላቸው እንደሆነ ይነገራል።

በሀዲያ ሆሳዕና የተፈተኑት ባህርዳር ከተማዎች መደበኛው ደቂቃ ተጠናቆ በተሰጡ ጭማሪ ደቂቃዎች ላይ ኦሲ ማውሊ ባስቆጠራት አስደናቂ ግብ እንደምንም ከጨዋታው ሙሉ ነጥብ ይዘው መውጣት ችለዋል።

ከተለመደው የተጫዋቾች አደራደር በተለየ ከኋላ ሦስት የመሐል ተከላካዮች ተጠቅመው ጨዋታውን የጀመሩት የጣና ሞገዶቹ መሰረታዊውን ነገር ሳይለቁ የቅርፅ ሆነ የአጨዋወት ለውጦችን ማድረግ እንደሚችሉ ባሳዩበት ጨዋታ አሸናፊ መሆናቸው ለአሰልጣኙ ለቀጣይ ጨዋታዎች ተስፋ የሚሰጥ ውጤት ሆኗል።

👉 የሚከላከል አምስት፤ የሚያጠቃ አምስት – መከላከያ

ከከፍተኛ ሊጉ ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊጉ የተመለሱት መከላከያዎች ሰበታ ከተማን በገጠሙበት እና አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ከአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ጀምሮ ቡድኑ ላይ ስንመለከት የነበረውን አንድ ዝንባሌን አስተውለናል።

የአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌው መከላከያ በጥንቃቄ የሚከላከል እንዲሁም ቀጥተኛነትን በቀላቀለ የመልሶ ማጥቃት ተጋጣሚን ለመጉዳት የሚንቀሳቀስ ቡድን እንደሆነ ከሁለቱ ጨዋታዎች እንዲሁም ከአሰልጣኙ የቀደሙ ቡድኖች እንቅስቃሴ መረዳት ይቻላል። በዚህ ሒደት ቡድኑ ተጋጣሚዎቹ ኳሱን እንዲይዙ የሚፈቅድ እና ኳሱን ይዘው ወደ መከላከያ ሜዳ እንዲመጡ የሚጋብዝ ዓይነት ነው። በአንዳንድ አጋጣሚዎችም በመካከለኛ ጫና (Medium Press) ትንሽ ከፍ ብሎ ጫና ለመፍጠርም ሲሞክሩ እናስተውላለን።

ታድያ በዚህ ሂደት ውስጥ በፊት አጥቂው ኡኩቱ ኢማኑኤልን የሚመራው እና የተቀሩ አራት ተጫዋቾች የሚሳተፉበት ጫና የመፍጠር ሂደትን እንመለከታለን። ይህ ሲሆን ግን ባልተለመደ መልኩ የተቀሩት የቡድኑ አባላት ከፍ ብሎ ለአጥቂዎቹ ጫና እገዛ ከመስጠት ይልቅ የኋላ አራት ተከላካዮች እና የአማካይ ተከላካዩ ኢማኑኤል ላርያ ወደ ግባቸው ተጠግተው ሲከላከሉ እናስተውላለን።

ይህ ሂደት በአዲስአበባ ከተማ ዋንጫ ላይም ጭምር በስፋት የተመለከትን ሲሆን ይህም ቡድኑ ለሁለት ተከፍሎ በአምስት ተጫዋቾች ጫና ሲፈጥር የተቀሩት አምስት የሜዳ ላይ ተጫዋቾች ደግሞ ተጠንቅቀው ለመከላከል ሲሞክሩ እናስተውላለን። በተመሳሳይ መከላከያዎች በማጥቃት አደረጃጀት ውስጥ በሚሆኑበት ወቅት በተመሳሳይ ሁለቱ የመስመር ተከላካዮች ሆነ የተከላካይ አማካዩ ለማጥቃት እንቅስቃሴ ተጠግተው ከመጫወት ይልቅ ኳሶች ቢቋረጡ (Turnover) ቢኖር ሊሰነዘሩባቸው የሚችለውን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ለማቋረጥ ሳይሆን ለመከላከል በሚያስችል የቦታ አያያዝ ኳሶችን ሲጠብቁ ተመልክተናል።

እርግጥ ነው በመልሶ ማጥቃት መጫወትን የሚመርጠው መከላከያ በሁለቱም አጋማሾች በረጃጅም ወደ ፊት ከሚላኩ ኳሶች ውጪ ከመስመር ተከላካዮቻቸው በማጥቃቱ ረገድ ይህ ነው የሚባል ተሳትፎን ሲያደርጉ አልተመለከትንም። ምናልባት መከላከያ በእስካሁኖቹ ጨዋታዎች በጨዋታው ሁለተኛ ግምት አግኝቶ ወደ ጨዋታዎቹ እንደመግባታቸው ቅድሚያ ላለመሸነፍ ሰጥተው በዚህ አጨዋወት መጫወታቸው ውጤታማ አድርጓቸዋል። ነገር ግን በንፅፅር መከላከያ ይበልጥ ለማጥቃት በሚገደድባቸው የጨዋታ አጋጣሚዎች በምን መልኩ ራሳቸውን አስማምተው(Adapt) አድርገው ይቀርባሉ የሚለው ነገር ይጠበቃል።

👉 በደርቢው የደመቁት ፈረሰኞቹ

ለሁለተኛ ጊዜ ከአዲስ አበባ ውጪ በተደረገው ተጠባቂው የሸገር ደርቢ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ ቡናን 4-1 በማሸነፍ ደጋፊዎቹን አስፈንድቋል።

ያለ ዋና አሰልጣኙ ዝላትኮ ክራምፖቲች ኢትዮጵያ ቡናን የገጠሙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በመጨረሻዎቹ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በነበራጓቸው ግንኙነቶች እንዳደረጉት የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾችን ስህተት መሰረት ባደረገ እንቅስቃሴ ውጤታማ መሆን ችለዋል። በእርግጥ ቡድኑ በኢስማኤል ኦሮ-አጎሮ አማካይነት ያስቆጠራት ግብ ስፖርታዊ ጨዋነትን የተጋፋች በመሆኗ በገለልተኛ ደጋፊዎች ጭምር መብጠልጠል ቢደርስባቸውም የጨዋታው ትልቅነት ነገሩን የሚያስታውሳቸው አይመስልም። ጨዋታው በደጋፊዎች ዘንድ ያለው ትርጉም ላቅ ያለ እንደመሆኑ የከተማ ተቀናቃኛቸውን ማሸነፍ ያውም በዚህ ልዩነት ለደጋፊዎቹ ከሚሰጠው ስሜት ባለፈ የተጫዋቾችን ሥነልቦና በመገንባት ረገድ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ከውድድር ዘመኖች መጀመር በፊት ሁሌም ቢሆንም ዋንጫውን የማሸነፍ ቅድመ ግምትን አግኝተው የሚጀምሩት ፈረሰኞቹ ባለፉት አራት የውድድር ዘመናት ግን ከተስፋ በዘለለ ኮስታራ የዋንጫ ተፎካካሪ ለመሆን ተቸግረዋል።ዘንድሮም እንደተለመደው በአዲስ አሰልጣኝ እና በአዲስ ሀሳብ በአዳዲስ ተጫዋቾች የተዋቀረውን ቡድን ምን ድረስ ሊጓዝ ይችላል የሚለው ጉዳይ በደጋፊዎች ዘንድ ይጠበቃል።

👉 የክለቦቻችን ደካማ አደረጃጀት

የኢትዮጵያ እግርኳስ በፈርጀ ብዙ የሜዳ ላይ እንዲሁም ከሜዳ ውጭ ኋላ ቀር እሳቤዎች የተተበተበ ስለመሆኑ ይነገራል። ይህን አሰራር ለመሻር እንቅስቃሴዎችን እያደረጉ ያሉ መሆኑ እንዳለ ሆኖ አሁን በቀደመው አስተሳሰብ ውስጥ የሚዳክሩትም ደግሞ ቁጥራቸው ያይላል።

ለዛሬው አንድ ጉዳይ እንመልከት። ዐምና በዚሁ ዓበይት ጉዳዮች ፅሁፋችን በወላይታ ድቻ ቤት አንድ ግለሰብ የቴክኒክ ዳይሬክተር፣ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ እና ቡድን መሪ ሆኖ እየሰራ እንደሚገኝ ማንሳታችን አይዘነጋም። ታድያ ዘንድሮም ወላይታ ድቻ ይህን አካሄድ በተወሰነ መልኩ ለወጥ በማድረግ አዲሱ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ ቡድኑን በቡድን መሪነት እንዲያገለግሉ መመደቡን እየተመለከትን እንገኛለን።

ይህን ጉዳይ አስገራሚ የሚያደርገው ክለቦቹ ወጪ ለመቀነስ አስበው ነው እንዳንል በረባ ባረባ ያለከልካይ ገንዘብ የሚረጩት ክለቦች ለቡድን መሪ ቅጥር ሲሆን የገንዘብ ምንጫቸው ደረቀ ብሎ መገመት አዳጋች ነው። በተመሳሳይ ይህን ሥራ መስራት የሚችሉ ባለሙያዎች ባሉበት የክለቦች ይህን አካሄድ መምረጥ ለቡድኖች ውጤታማነት እያንዳንዱ በክለቡ ዙርያ ያሉ አካላት ያላቸውን ሚና ካለመረዳት የሚመነጭ ይመስላል።

ውጤታማ ቡድንን ለመገንባት ትንሽ ከሚመስሉት የምግብ አቅራቢዎች እስከ ዋናው አሰልጣኝ ድረስ ያሉ ሁሉም አካላት የሚያደርጉት የጋራ ድምር ውጤት ቡድኑን ውጤታማ ሲያደርግ እናስተውላለን። ከላይ የጠቅስናቸው ማሳያ ክለቦች ተመሳሳይ ግለሰቦችን በተደራራቢ ሚናዎች ላይ መመደብ ሥራዎቹን ከመበደል ባለፈ ግለሰቦቹ በተለያዩ ሚና በተበታተነ ትኩረት ክለቡን ከመጥቀም ይልቅ እንደነገሩ ሥራዎቹ እንዲሸፈኑ ከማድረግ የዘለለ ፋይዳ አይኖራቸውም።

እንግዲህ ይህ ሁሉ ነገር እያወራን የምንገኘው በሀገሪቱ የክለቦች ከፍተኛው የሊግ እርከን መሆኑ ወደ ታች እየወረድን ስንሄድ ክለቦች በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ለመገመት አይከብድም። በመሆኑም ቢያንስ በፕሪምየር ሊግ የሚገኙ ክለቦች ከዚህ ደካማ አስተሳሰብ ወጥተው ጠንካራ የክለብ ቁመና ለመላበስ መስራት ይኖርባቸዋል።