የብሔራዊ እና የአዲስ አበባ ስታዲየሞች ጉብኝት ተደረገባቸው

በመዲናችን በግንባታ እና በእድሳት ሂደት ላይ የሚገኙት የብሔራዊ እና የአዲስ አበባ ስታዲየሞች በከፍተኛ የመንግስት ሀላፊዎች ጉብኝት ተደርጎባቸዋል።

ሀገራችን ኢትዮጵያ ለበርካታ ጊዜያት አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮችን ስትከውንበት የነበረው የባህር ዳር ስታዲየም ወቅታዊ መመዘኛዎችን አያሟላም በሚል ዕግድ እንደተላለፈበት ይታወቃል። ይህንን ተከትሎ የወንዶች ብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች በሌሎች ሀገራት እንዲከናወኑም ተወስኗል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በሀገራችን ትልቁ እና ዘመናዊ ተደርጎ እየተገነባ ያለው ብሔራዊ ስታዲየም እና ዕድሳት ላይ የሚገኘው የአዲስ አበባ ስታዲየም በዛሬው ዕለት በመንግሥት ኃላፊዎች ምልከታ ተደርጎበታል።

በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ገርጂ አካባቢ የሚገኘው ብሔራዊ ስታዲየም በሁለት ምዕራፎች ተከፋፍሎ እየተገነባ ሲሆን ሲያልቅ 62 ሺ ተመልካቾችን በወንበር የማስተናገድ አቅም ያለው መሆኑ ተነግሯል። ይህንን ስታዲየም ከሦስት ቀናት በፊት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ክቡር ዶክተር ዐብይ አህመድ የተመለከቱት ሲሆን ዛሬ ደግሞ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች የስታዲየሙን የግንባታ ሂደት ጎብኝተዋል። በዛሬው ጉብኝት ላይ የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጀላ መርዳሳ፣ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት እና ወ/ሮ ወርቅነሽ ብሩ እንዲሁም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ እና ሌሎች ሀላፊዎች ተገኝተዋል።

ከጠዋቱ 3:30 ጀምሮ እስከ 7 ሰዓት ድረስ በነበረው ምልከታ ላይ ሚኒስቴሩ ስታዲየሙ ደረጃውን ጠብቆ እንዲገነባ እና የውጪያዊ ክፍሉ እና የፊኒሺንግ ሥራው ጎን ለጎን እንዲሰራ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። በዋናነት ደግሞ በተያዘው ጊዜ ግንባታው እንዲጠናቀቅም ክትትል እንደሚደረግበት በአፅንኦት ተናግረዋል።

ይሁ ልዑክ ከሰዓት ከ7 ሰዓት ጀምሮ ደግሞ በእድሳት ላይ የሚገኘውን አንጋፋውን የአዲስ አበባ ስታዲየም ተመልክቷል። በተመሳሳይ ስታዲየሙም በቶሎ እድሳቱን አገባዶ ለውድድር እንዲቀርብ ከፍተኛ ርብርብ እንዲደረግ ተገልጿል።