የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ 2ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋች ትኩረት

የሁለተኛ የጨዋታ ሳምንት በተደረጉ ስምንት ጨዋታዎች ላይ የተመለከትናቸው ትኩረት የሳቡ ተጫዋቾች የዚህኛው ፅሁፋችን አካል ነው።

👉 የፅዮን መርዕድ የጊዜ አጠባበቅ

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብቅ ካሉ እና በብዙዎች ዘንድ ከፍ ያለ ቦታ ከሚሰጣቸው የሀገራችን ወጣት ግብ ጠባቂዎች አንዱ የሆነው ፅዮን መርዕድ ባህርዳር ከተማን ለቆ በቋሚነት የመሰለፍ እድልን ፍለጋ ወደ ወላይታ ድቻ አምርቷል። በአዲሱ ክለቡም በመጀመሪያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች በቋሚነት የመጫወትን ዕድል አግኝቷል።

በባህር ዳር ከተማ በነበረው ቆይታ ወጣቱ ግብጠባቂ የቤኒናዊው ሀሪስተን ሄሱ ተጠባባቂ በመሆን የሀሪሰን ሄሱ በተቀጣባቸው እና ስህተትን ፈፅሞ ወደ ተጠባባቂነት በወረደባቸው ጥቂት ተከታታይ ጨዋታዎች ውጭ ራሱን ለማሳደግ በሚረዳው መንገድ በቋሚነት በቂ የመሰለፍ ዕድልን ማግኘት ሳይችል ቆይቷል። በዚህ ሒደት ልክ እንደ አብዛኞቹ የሀገራችን ግብጠባቂዎች ከጨዋታ መራቁን ተከትሎ የራስ መተማመን እና የብቃት መውረዶችም እንዲሁ ይህን ግብጠባቂ ጎብኝተውታል።

ለዓለም ብርሃኑ፣ ታሪክ ጌትነት፣ አቤል ማሞ፣ ጀማል ጣሰው ከብዙዎቹ በጥቂቱ የዚህ አይነት ሒደት ሰለባ የነበሩ ተጫዋቾች እንደነበሩ ማስታወስ ይቻላል። ታድያ ፅዮን ዳግም የመሰለፍ እድልን ባገኘባቸው ጨዋታዎች ላይ ስህተቶችን ሲፈፅም ተመልክተናል። በመጀመሪያው የድሬዳዋ ጨዋታ በተለይ ግቧ ስትቆጠር ፍሬው ከተከላካዮቹ ጋር የነበረው ተግባቦት (Communication) ለግቧ መቆጠር አይነተኛ ምክንያት ነበር። በተመሳሳይ ሀዋሳን 1-0 በረቱበት ጨዋታ እንዲሁ ተደጋጋሚ የሆኑ የቦታ እና የጊዜ አጠቃቀም ስህተቶችን ቢፈፅምም በሀዋሳ ተጫዋቾች የአጨራረስ ድክመት ግብ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል።

ተጫዋቹ እርግጥ ቡድኑ በማሸነፉ ብዙ ክፍተቶቹ ተሸፋፍነው ቢያልፉም ከጨዋታ ጨዋታ የራስ መተማመኑ ሊያድግ እንደሚችል ቢጠበቅም የጊዜ እና ቦታ አጠቃቀም እንዲሁም የእግር ኳስ አጠቃቀሙን ይበልጥ ለማሻሻል መስራት ይኖርበታል።

👉 ግቦችን በእንቅስቀሴው ላይ ለመጨመር እየጣረ የሚገኘው ፍሬው ሰለሞን

በክረምቱ የዝውውር መስኮት ወልቂጤ ከተማን ለቆ ወደ ሲዳማ ቡና ያመራው ፍሬው ሰለሞን ባለፉት ጥቂት ዓመታት የጨዋታ መንገዱ ላይ በተወሰነ መልኩ መሻሻሎችን እያሳየ ይገኛል። በ2010 የውድድር ዘመን በሀዋሳ ቆይታ ያስመዘገበው የጎል ሪከርዱን ለማሻሻል ያለመ የሚመስል እንቅስቃሴም እያሳየ ይገኛል።

የቀድሞው የሙገር ሲሚንቶ እና መከላከያ አማካይ እንደቀደመው ጊዜያት ለአጥቂዎች የመጨረሻ ኳሶችን ከማቀበል ባለፈ ራሱ ግቦችን ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረቶችን የሚያደርገው ፍሬውን እየተመለከትን እንገኛለን። ለማሳያነትም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ድሬዳዋ ከተማን 3-0 ሲረቱ ፍሬው ሰለሞን አንድ ግብ አስቆጣሯል። ከቀኝ መስመር የደረሰውን ኳስ ድሬዳዋ ሳጥን ውስጥ ሆኖ በቀጥታ እንደመጣች አክርሮ በመምታት ያስቆጠረበት መንገድ አስደናቂ ነበር።

ከግቧ በተጨማሪ ተደጋጋሚ ኳሶችን ወደ ግብ የሞከረው ተጫዋቹ በሁለት አጋጣሚዎች ማለትም ከግራ መስመር የተሻማ ኳስ ተገጫጭቶ ሲመለስ ያገኘውን ኳስ አክርሮ የመታው እና ቋሚ የመለሰበት እንዲሁሜ ወደ ግራ ካደላ ቦታ ላይ ከረጅም ርቀት በቀጥታ አክርሮ የመታው እና በተመሳሳይ የግቡ ቋሚ የመለሰበትን ሁለት ኳሶች መጥቀስ ይቻላል።

👉 አበባው ቡጣቆ ወደ ሜዳ ተመልሷል

ከ1990ዎቹ አጋማሽ አንስቶ በቅዱስ ጊዮርጊስ መለያ ሆነ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቀዳሚ ተመራጭ የግራ መስመር ተከላካይ በመሆን እጅግ ስኬታማ የሆኑ ጊዜያትን ካሳለፈ በኃላ በ2010 የውድድር ዘመን መጨረሻ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከተለያየ በኋላ ለአንድ አመት በደቡብ ፖሊስ ማሳለፍ ቢችልም ከዛ በኋላ ግን ለወራት ከእግርኳስ ርቆ ቆይቷል።

በኢትዮጵያ እግርኳስ በተለይ ባለፉት 20 ዓመታት ከተመለከትናቸው ምርጥ የግራ መስመር ተከላካዮች አንዱ የሆነው አበባው ቡጣቆ በሀዋሳ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ሲያደርግ በነበረው የወልቂጤ ከተማ የተሰጠውን የሙከራ ጊዜ በአመርቂ ሁኔታ አጠናቆ በዘንድሮ የውድድር ዘመን ዳግም ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የሚመልሰውን ዝውውር ማድረጉ ይታወቃል።

ወልቂጤ ከተማ ከአዳማ ከተማ ጋር አንድ አቻ በተለያየበት ጨዋታ ረመዳን የሱፍ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ መውጣቱን እና በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ያለመኖሩን ተከትሎ አበባው ቡጣቆ ዳግም ከወራት ቆይታ በኋላ የመጀመሪያውን ጨዋታ በወልቂጤ መለያ አከናውኗል።

የፋሲል ከነማ 67% ማጥቃት መነሻ በነበረው የፋሲል ቀኝ (የወልቂጤ ግራ) የተሰለፈው አበባው የፋሲሎች በቁጥር ብልጫ በመስመሮች በኩል ለማጥቃት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ለመመከት በአመዛኙ በራሱ ሜዳ ተገድቦ ጥሩ የመከላከል አበርክቶን ማድረግ ችሏል።

በቦታው የወቅቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተመራጭ የግራ መስመር ተከላካይ ረመዳን የሱፍ በአበባው ቦታ እንደመኖሩ በቋሚነት ለመሰለፍ ከፍተኛ ፈተና የሚጠብቀው ቢሆንም ከጨዋታ ርቆ እንደመቆየቱ እና እንደጨዋታው ክብደት ተስፋ ሰጪ እንስቃሴ አድርጓል።

👉 ኦሴ ማውሊ ቡድኑን ታድጓል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከዚህ ቀደም በመቐለ 70 እንደርታ እና ፋሲል ከተማ ቆይታ የነበረው ጋናዊው የመስመር (የፊት) አጥቂ ኦሴ ማውሊ አምና ከግማሽ ዓመት ያለክለብ ከቆየ በኋላ ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሚመልሰውን የሰበታ ከተማ ዝውውር ካደረገበት ጊዜ አንስቶ ፍፁም የተለየ ተጫዋች እየሆነ መምጣቱን እንመለከታለን።

እንደ አብዛኛዎቹ የውጭ ሃገር ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾች ቀስ በቀስ መውረድ ነገር ተመልክተንበት የነበረው ተጫዋቹ ወደ ሰበታ ከተማ ከመጣበት ጊዜ አንስቶ እጅግ ድንቅ ጊዜያትን ማሳለፉ አይዘነጋም። በተለይም እጅግ ደካማ የመስመር ላይ የማጥቃት አፈፃፀም የነበረው ቡድን ከማውሊ መምጣት በኋላ ግን በእጅጉ ተሻሽሎ ተመልክተናል በዚህ ሂደት ውስጥ ተጫዋቹ ግቦችን ከማስቆጠር ባለፈ አጠቃላይ የቡድኑን ማጥቃት አሻሽሏል ብለን መናገር እንችላለን።

በክረምቱም አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱን ተከትሎ ባህርዳር ከተማ የደረሰው ኦሲ ማውሊ ባህርዳር ከተማን እየታደገ ይገኛል ፤ በመጀመሪያው ጨዋታ አዲስአበባ ከተማን 3-0 ሲረቱ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር የአንበሳውን ድርሻ የተወጣው ተጫዋቹ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ቡድኑ በተቸገረበት ቀን ኦሲ ማውሊ ቡድኑን የታደገች ግብ በጭማሪ ደቂቃ በማስቆጠር ሙሉ ሦስት ነጥብ አስጨብጧል።

በመስመር ሆነ በፊት አጥቂነት መጫወት የሚችለው ኦሲ ማውሊ ለባህር ዳር ከተማ የማጥቃት እንቅስቃሴ የተለያዩ አማራጮችን ከመስጠት ባለፈ ቡድኑ ለዋንጫ በሚያደርገው ፉክክር ውስጥ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት አይነት ተጋጣሚ ሲያጋጥመው በግል ጥረት ግቦችን ከምንም ማግኘት የሚችሉ ተጫዋቾች ማግኘቱ በራሱ ትልቅ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ይጠበቃል።

👉 የአቡበከር ናስር ስሜታዊነት

በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ በትውልዶች መካከል ከሚገኙ ተሰጥኦዎች ከታደሉ ተቻዋቾች መካከል የሚመደበው አቡበከር ናስር ከእግርኳሳዊ ብቃቱ ባለፈ በአንዳንድ አጋጣሚዎች ደግሞ ከልክ ባለፈ መልኩ ስሜታዊ ሲሆን እናስተውላለን።

በአምስት ቢጫ ካርድ የሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ ያለፈው አቡበከር ናስር በሸገር ደርቢ ኢትዮጵያ ቡና በቅዱስ ጊዮርጊስ 4-1 በተሸነፈበት ሁለተኛ የጨዋታ ሳምንት ዳግም ወደ ሜዳ ተመልሶ ተመልከተነዋል። የደርቢ ጨዋታዎች በራሳቸው በተጫዋቾች እና በደጋፊዎች ዘንድ የስሜት ከፍታን የመፍጠራቸው ነገር እንዳለ ሆኖ አንዱ ለሌላኛው እጅ ላለመስጠት ባለ በሌለ አቅም እንዲፍጨረጠሩ የሚያስገድድ አንዳች የስነልቦና መነሳሳት እየፈጠሩ ተጫዋቾች ሜዳ ላይ በስሜት የተሞላ የጨዋታ ዕለት እንዲያሳልፉ ያደርጋሉ።

ምናልባት ከዚህ መነሻነት በደርቢ ጨዋታዎች ተጫዋቾች በጋለ ስሜት ጨዋታን ማድረጋቸው የተለመደ ቢሆንም አቡበከር ናስር በጨዋታው ሲያሳይ የነበረው ነገር ግን በመጠኑም ቢሆን ከልክ ያለፈ ነበር ብሎ መግለፅ ይቻላል።

በተለይ በዚህ ጨዋታ ቡድኑ ወደ ጨዋታው የመመለስ ፍንጭን ባሳየባቸው የጨዋታ ቅፅበቶች ሳይጠበቅ ባስተናገዳቸው ሁለት ግቦች 4-1 መመራቱ ካሳደረበት የብስጭት ስሜት ነው እንዳንል ገና በመጀመሪያው አጋማሽ ደቂቃዎች በተወሰነ መልኩ ስሜታዊ ሲሆን የተመለከትንባቸው አጋጣሚዎችም ነበሩ።

ታድያ ጨዋታውን የመሩት ኢንተርናሽናል አልቢትር ኃይለየሱስ ባዘዘው ጨዋታውን አረጋግተው ለማስቀጠል ያደረጉት የሚደነቅ ጥረት ሆነ እንጂ አቡበከር የቀይ ካርድ ሰለባ የሚሆንበት ዕድል የሰፋ ነበር።

👉 የሀይደር ሸረፋ ወደ መደበኛ ጎል አስቆጣሪነት እየተሸጋገረ መምጣት

በኢትዮጵያ እግርኳስ ባለፉት ዓመታት እየደመቁ ከሚገኙ የአማካይ መስመር ተሰላፊዎች ውስጥ አንዱ የሆነ ሀይደር ሸረፋ ዘንድሮ ደግሞ በቅዱስ ጊዮርጊስ መለያ ከአዲስ ኋላፊነት ጋር ብቅ ብሏል።

ቡድኑን በአምበልነት እየመራ የሚገኘው ሀይደር ዘንድሮ በጥልቀት እየተነሳ የማጥቃት እንቅስቃሴውን ከማሳለጥ ባለፈ ወደ ሳጥን በመድረስም ግቦችንም ማስቆጠር ጀምሯል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን የመጨረሻ ጥቂት ሳምንታት የግብ አስቆጣሪነት አቅሙን ማሳየት የጀመረው ሀይደር ዘንድሮ ይህን አቅሙን አስድጎ እንደመጣ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ምልክቶችን ማሳየት ጀምሮ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ደግሞ በፕሪምየር ሊጉ ይህን በተግባር በማሳየት ላይ ይገኛል።

የዘጠኝ ቁጥር የአጥቂ ቦታ ላይ ወሳኝ ተጫዋቾችን ያጡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች እንደ ሀይደር ያሉ ተጫዋቾች ወደ ግብ አግቢነት መምጣት መቻላቸው በራሱ የአጥቂ አመኖር የሚያጎድልባቸውን የግብ መጠን እንደ ቡድን ጫናውን ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት አይነተኛ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።

👉 ስፖርታዊ ጨዋነትን የተፃረረው ድርጊት

በዓለምአቀፍ የእግርኳስ ህግጋት ውስጥ ስፖርታዊ ጨዋነት (Fair Play) እንዲከበር የሚበረታታ ምግባር እንጂ አስገዳጅነት የተቀመጠ የህግ አግባብ ባይኖረም በጋራ መግባባት (common Sense) ቢተገበሩ የሚበረታቱ ናቸው።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ ቡናን በረታበት ጨዋታ የተፈጠረ አጋጣሚ ግን ይህን መርህ የተጣረሰ ተግባር ነበር። በ21ኛው ደቂቃ የኢትዮጵያ ቡናው የመሀል ተከላካይ ጡንቻው ላይ መጠነኛ የህመም ስሜት ያጋጥመዋል። ይህን ተከትሎ ተጫዋቹ በእንቅስቃሴ ላይ የነበረችውን ኳስ ራሱ ጨዋታ ውጭ እድትወጣ በማድረግ የህክምና እርዳታ ለማግኘት ሜዳ ላይ ይወድቃል። የህክምና እርዳታ ተደርጎለት ጨዋታው በስፖርታዊ ጨዋነት ለማስቀጠል አቤል ያለው የወረወረውን የመልስ ውርወራ ኳስ ሀይደር ሸረፋ ለኢትዮጵያ ቡናው ግብጠባቂ አቤል ማሞ ቀለል አድርጎ ሲያቀብል የቅዱስ ጊዮርጊሱ አጥቂ ኢስማኤል ኦሮ-አጎሮ አሳማኝ ባልሆነ መንገድ ግብ ማስቆጠር ችሏል።

የግቧን መቆጠር ተከትሎ ከፍተኛ ውዝግቦች በሜዳ ላይ የተመለከትን ሲሆን መናገር የሚቻለው ነገር ግን አጥቂው አስቦበት ካደረገው ከስፖርታዊ መንፈስ ባፈነገጠ መልኩ የፈፀመው ተግባር ሆኖ ስለሚቆጠር የማይበረታታ ድርጊት መሆኑ ነው። ሆን ተብሎ የተደረገ  ከሆነም ተጫዋቹ ይህን የስፖርታዊ ጨዋነትን የጣሰ ድርጊት በመፈፀሙ መነሻነት ቢያንስ መላውን የእግርኳስ ቤተሰብ በይፋ ይቅርታ መጠየቅ ይኖርበታል።

በቅርብ ጊዜ እንኳን በ2019 በእንግሊዝ ሻምፒየን ሺፕ አስቶን ቪላ ከሊድስ ዩናይትድ ባደረጉት ጨዋታ በተመሳሳይ በስፖርታዊ ጨዋነት ጥሰት ሊድስ ዩናይትዶች ግብ ቢያስቆጥሩም ሊድሶች በአሰልጣኛቸው ማርሴሌ ቤዬልሳ ትዕዛዝ የአስቶንቪላ ተጫዋቾች የአቻነት ግብ እንዲያስቆጥሩ የፈቀዱበቶ መንገድ በፊፋ ዘንድ የዓመቱ ምስጉን የስፖርታዊ ጨዋነት ተሸላሚ እንዲሆኑ ያስቻላቸው አጋጣሚ ይታወሳል ፤ የእስማኤልን ድርጊት ደግሞ ይበልጥ አነጋጋሪ የሚያደርገው ግቡን አስቆጠር ደስታውን መግለፁ ይበልጥ የተቃራኒ ተጫዋቾችን ስሜት ያጋለ ድርጊት ነበር።

👉 ቴዎድሮስ በቀለ እና አስከፊው የጨዋታ ዕለት

በክረምቱ የዝውውር መስኮት ኢትዮጵያ ቡናን የተቀላቀለው ቴዎድሮስ በቀለ በኢትዮጵያ ቡና መለያ ባደረገው የመጀመሪያው ይፋዊ ጨዋታው እጅግ አስከፊ የነበረ እና ሊያስተዋሰው የማይፈልገው ዓይነት ቀን አሳልፏል።

በመከላከያ አስደናቂ ጊዜያትን ካሳለፈ በኋላ ባለፉት ዓመታት በአዳማ ከተማ እና በሀዲያ ሆሳዕና ያንን የቀደመ አስደናቂ ብቃቱን በቂ የመሰለፍ ዕድሎችን ማግኘት ባለመቻሉ እና በሌሎች ምክንያቶች ለማግኘት መቸገሩ በቀደሙት ቡድኖቹ ያደረጋቸው የጨዋታ ብዛቶች በራሱ ገላጭ ናቸው።

በሸገር ደርቢ የመጀመሪያውን ጨዋታውን ለኢትዮጵያ ቡና ያደረገው ተጫዋቹ ለጨዋታው በአዕምሮ ደረጃ ፍፁም ዝግጁ የነበረ አይመስልም። ይህም አጠቃላይ ጨዋታው ላይ የታዘብነው እውነታ ነበር። ተጫዋቹ በጨዋታው በመለስተኛ ጫና ውሰጥ ሆኖ ተደጋጋሚ የማቀበል ስህተቶችን እንዲሁም በጣም በበርካታ አጋጣሚዎች ተደጋጋሚ የውሳኔ ስህተቶችን ሲፈፅም መመልከት ችለናል።

በጨዋታው ኢትዮጵያ ቡና ቴዎድሮስ በቀለን ሜዳ ላይ በመጠቀሙ ካገኘው ጥቅም ይልቅ ያለማጋነነ በጨዋታው ያጣው ነገር ብዙ ነበር። በመሆኑም ተጫዋቹ ከዚህ አስከፊ አጀማመር ማግስት በብዙ መንገዶች ራሱን ማሻሻል የማይችል ከሆነ በቡና የሚኖረው ቆይታ ስኬታማነቱ አጠራጣሪ ይመስላል።

ያጋሩ