በሁለተኛው ሳምንት ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ የታዘብናቸው አሰልጣኝ ነክ ጉዳዮችን እንደሚከተለው ቃኝተናል።
👉🏾 የአሰልጣኝ አስተያየቶች እና ሜዳ ላይ ያለው ዕውነታ
ፕሪምየር ሊጉ የቴሌቪዥን ስርጭት ሽፋን ማግኘቱ ተከትሎ ለእግርኳሳችን በርካታ ትሩፋቶችን ይዞ መምጣቱ ብዙ የተባለበት ጉዳይ ቢሆንም ሌላኛው እና ብዙ ያልተባለበት አንዱ ጉዳይ አሰልጣኞች ከጨዋታ በፊት ጨዋታውን መቅረብ ስለሚፈልጉበት መንገድ እንዲሁም ከጨዋታው በኋላ ስለ ጨዋታው የሚሰጧቸው አስተያየቶች በምን ያህል መጠን ሜዳ ላይ ያለውን እውነታ ይገልፃሉ የሚለውን ነገር ሰፊው የእግርኳስ ቤተሰብ እንዲታዘብ የማስቻሉ ጉዳይ ነው።
ምን አልባት ስለነገሮች የሚኖረን ምልከታ ከሰው ሰው ሊለያይ እንደሚችል ይታመናል። ነገርግን ሁሉም ሰዎች ሙሉ ለሙሉ እንኳን ባያግባቡ በተወሰነ መልኩ ሊጋሯቸው የሚገቡ ሀሳቦች ሊኖሩ ይገባል። የሀሳቦቹ ትክክልነኝነትን ወደ ጎን ትተን እውነት አሰልጣኞቻችን የሚናገሯቸው ሀሳቦች ምን ያህል ሜዳ ላይ ተመልከተናቸዋል ብለን ስንጠይቅ ግን መልሱ ብዙም የሚያስደስት አይደለም።
ከጨዋታዎች መጀመር አስቀድሞ የአብዛኞቹ ቡድኖች አሰልጣኞች ኳስን መስርተን እንዲሁም ኳስን ተቆጣጥረው ለመጫወት ስለማቀዳቸው ሲናገሩ ብናደምጥም ሜዳ ላይ ግን ቡድኖቻቸው ይህን ሲያደርጉ እምብዛም አናስተውልም። በተመሳሳይ ከጨዋታ በኋላም አብዛኞቹ ቡድናቸው የተሻለ እንደነበርና የተሻለ ስለመንቀሳቀሳቸው ሲናገሩ ማድመጥ የተለመደ ነው።
በእነዚህ አስተያየቶች ውስጥ ሁለት ነጥቦችን ማንሳት ይኖርብናል አንደኛው ጉዳይ አሰልጣኞች ቡድናቸው ኳስ እንዲቆጣጠር ፍላጎት ቢኖራቸውም ሜዳ ላይ ሳይተገበር ቀርቷል ወይንም አሰልጣኞቻችን ኳስ ቁጥጥርን የሚረዱበት መንገድ ትክክለኝነቱ ላይ ጥያቄ ማንሳት ይኖርብናል።
ከተጋጣሚ ከፍ ብሎ ጫና መፍጠር አለመምረጡን ተከትሎ በራስ የሜዳ አጋማሽ ብሎም ከተጋጣሚ የመከላከል አደረጃጀት ፊት በመጀመሪያዎቹ 60 (70ሜትሮች) ላይ ኳሶችን በማንሸራሸር ብቻ የተገደበ እና ጫናዎች ካሉ ደግሞ ከታች ወደ ላይ ለማደግ የተቸገረ እና የግብ እድሎችን ለመፍጠር የሚያፍር ቡድን በኳስ ቁጥጥር የተሻልን ስለመሆኑ መናገር ብዙም የሚያሳምን አይደለም። በዚህ ሂደት ውስጥ አሰልጣኞች ምናልባት በጫና ውስጥ ኳሶችን የማሳደጊያ መንገዶች ላይ ቡድኖቻቸው ላይ አልሰሩም አልያም ከጫና ውጭ ተጋጣሚ ክፍት በሚተዋቸው ሜዳዎች ላይ በመቀባበል ጊዜውን ያባከነ ቡድን ኳስ ተቆጣጥሮ ተጫውቷል የሚል የተሳሳተ እምነት አለ ማለት ነው።
በተመሳሳይ ከጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ የረባ ሙከራ ለማድረግ የተቸገረን ቡድን የተሻለ ስለመሆኑ እና እድሎችን ፈጥሮ እንደነበር ከድህረ ጨዋታ አስተያየቶች ስታደምጥ አስተያየቶች በተጠናቀቀው ጨዋታ ወይንስ ከሌላ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የተሰጠ መሆኑን ለማመን መቸገር የተለመደ ነገር ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ አንዳንድ ሀቀኝነት የተሞላበት እና የሜዳ ላይ የነበሩትን ሁነቶች ተረድተው የሚያቀርቡ አሰልጣኞች እንዳሉ ሆነው ማለት ነው።
ውድድሩ ቀጥታ የቴሌቪዥን ሽፋን እንደማግኘቱ ፍርዱ ለደጋፊዎች የሚተው ቢሆንም የተሻሻሉ እና ጨዋታን የሚገልፁ አስተያየቶች በቀጣይ ከአሰልጣኞቻችን የሚጠበቁ ይሆናል።
👉🏾 አሰልጣኞች እና ሀዘን
በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የወልቂጤ ከተማው ዋና አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው እና የቅዱስ ጊዮርጊሱ ዋና አሰልጣኝ ዝላትኮ ክራምፖቲች በተለያየ ሀዘን ውስጥ ሆነው ነበር ያሳለፉት።
ተመሳሳይ የቤተሰብ ሀዘን ያጋጠማቸው አሰልጣኞቹ ጳውሎስ ጌታቸው በሀዘን ውስጥ ሆነው ቡድናቸውን ሲመሩ የተመለከትን ሲሆን በተቃራኒው ሰርቢያዊው ዝላትኮ ክራምፖቲች ደግሞ የወላጅ አባታቸውን ቀብር ለመካፈል በሚል ወደ ሰርቢያ ማቅናታቸውን ተከትሎ በሸገር ደርቢ ቡድናቸው ሳይመሩ ቀርተዋል።
👉🏾 ውጤት ያስገኙ የተጫዋች ቅያሬዎች
ውጤታማ አሰልጣኞች ከሌሎች የሚለዩበት አንዱ እና ዋነኛው በጨዋታ ወቅት የጨዋታውን ሂደት እና የተጋጣሚን ሁኔታዎችን በመረዳት ለውጦች ማድረግ (In Game Management) ጉዳይ ተጠቃሽ ነው። ከነዚህም መካከል የተጫዋቾች ቅያሬዎች አንዱ ነው።
በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት አርባምንጭ ከተማ ከመመራት ተነስቶ አዲስአበባ ከተማን በረታበት ጨዋታ የአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ የሁለተኛ አጋማሽ ቅያሬዎች አይነተኛ ሚና ነበራቸው። በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይረው ወደ ሜዳ ከገቡት ሦስት ተጫዋቾች መካከል ፍቃዱ መኮንን የአቻነቷን ግብ ሲያስገኝ አማካዩ አሸናፊ ተገኝ ደግሞ ወርቅይታደስ አበበ ላስቆጠራት የፍፁም ቅጣት መገኘት ምክንያት ነበር።
በተመሳሳይ መከላከያ ሰበታን ባሸነፈበት ጨዋታም የመከላከያ የማሸነፍያ ግብ የተገኘችው በሁለተኛ አጋማሽ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ቀይረው ካስገቡት አቤል ነጋሽ የተገኘች ነበረች።
👉🏾 የምክትል አሰልጣኞች ጨዋታ መምራት
በዚህ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለት ምክትል አሰልጣኞች የቡድኖቻቸውን ጨዋታ መርተዋል። በዕለተ ዕሁድ አዲስ አበባ ከተማ ከአርባምንች ከተማ ያደረገውን ጨዋታ የአዲስ አበባው አሰልጣኝ እስማኤል አቡበከር እንደሚመሩት ቢጠበቅም ከጨዋታው በፊት በተከሰቱ ውዝግቦች በተመልካች መቀመጫ ላይ ሆነው እንዲያሳልፉ ተገደዋል። አሰልጣኙ ከቡድን መሪው አቶ ሲሳይ ተረፈ ጋር በፈጠሩት ውዝግብ እንዲታገዱ መደረጉን ተከትሎ ምክትል አሰልጣኙ ደምሰው ፍቃዱ በአርባምንጭ 2-1 የተሸነፉበትን ጨዋታ እንዲመሩ ሆኗል። በአሰልጣኝ እስማኤል የተጀመረው ቅድመ ጨዋታ አስተያየትም በምክትሉ ደምሰው ድህረ ጨዋታ አስተያየት ተደምድሟል።
ሌላው በዚህ ሳምንት በምክትል አሰልጣኝ እየተመራ ወደ ሜዳ የገባው ቡድን ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው። በሸገር ደርቢ ቡናን ከገጠሙበት ዕለት አስቀድሞ ዋና አሰልጣኙ ዝላትኮ ክራምፖቲች በሀዘን ምክንያት ወደ ሀገራቸው ማምራታቸውን ተከትሎ ምክትል አሰልጣኙ ዘሪሁን ሸንገታ በፈረሰኞቹ 4-1 አሸናፊነት የተጠናቀቀው ጨዋታን እንዲመሩ ተደርጓል።
👉🏾 ስክን ያሉት ካሣዬ አራጌ
ስሜታዊነት እና መጣደፎች የተለመዱ በሆኑበት ሁኔታ ውስጥ እንደ ካሳዬ አራጌ በየትኛውም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ስሜታቸው የማይለዋወረጥ ስብዕና ያላቸው ግለሰቦችን እግርኳሳችን አብዝቶ ይፈልጋቸዋል።
በደጋፊዎች ዘንድ ትልቅ ትኩረት በሚሰጠው የሸገር ደርቢ 4-1 ሽንፈት ቡድኑ ቢያስተናግድም አሰልጣኙ ግን በድህረ ጨዋታ ቃለመጠይቃቸው ወቅት እንደተለመደው በተረጋጋ መንፈስ ውስጥ ሆነው ነበር ቆይታ ያደረጉት። ጉዳዩን ይበልጥ አስገራሚ የሚያደርገው ነገር ደግሞ አንደኛው ግብ የተቆጠረበት መንገድ ለተመለከት ሌሎች አሰልጣኞች ቢሆኑ በድህረ ጨዋታ ቆይታቸው ዘለግ ያለውን ጊዜ የሚወስዱት በዚሁ ጉዳይ ላይ በሆነ ነበር። ነገርግን ካሳዬ ይህን ሲያደርጉ አልተመለከትንም።
ይልቁኑ በዚህ ጉዳይ እና በሌሎች ነገሮች ላይ ተንተርሶ ሀሳቦችን ከመስጠት ይልቅ የቡድኑ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ላይ ያተኮሩ ሀሳቦችን መስጠት ምርጫቸው ሆኗል። ይህም ሌሎች በሊጉ የሚገኙ አሰልጣኞች ከካሳዬ ሊማሩት የሚገባ ጉዳይ ነው።