“ዋናው ቡድን የተዘጋጀ ተጫዋች እንዲያገኝ የተሻለ ሥራ እንሰራለን” አሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል

የኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ለሴካፋ ውድድር እያደረገ ያለውን ዝግጅት አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

በአሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የሚመራው የኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በዩጋንዳ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የሴካፋ ውድድር ላይ እንደሚሳተፍ ይታወቃል። ከጥቅምት 18-30 ድረስ አዘጋጇ ዩጋንዳን ጨምሮ ኢትዮጵያ፣ ብሩንዲ፣ ኤርትራ፣ ጅቡቲ እና ታንዛኒያን በሚያሳትፈው ውድድሩ ላይ ተጠናክሮ ለመቅረብ አሠልጣኝ ፍሬው ከቀናት በፊት ዝግጅታቸውን አዲስ አበባ ላይ ማድረግ ጀምረዋል። ይህንን የዝግጅት ጊዜ አስመልክቶም ዋና አሠልጣኙ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

አሠልጣኝ ፍሬው ኃይለ ገብርኤል በሰጡት መግለጫ “አሁን የምናደርገው የሴካፋ ውድድር ስድስት ሀገራት ቡድኖች የሚሳተፍበት ነው፡፡ እኛም ለእነዚህ ቡድኖች የሚሆነውን ነገር ይዞ ለመቅረብ በተለያየ አይነት መንገድ ዝግጅቶችን ስናደርግ ነበር።” ብለዋል። አሠልጣኙ ጨምረውም በመጀመሪያ ቦሌ በሚገኘው ጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል ለ5 ቀናት ቆይታ ካደረጉ በኋላ በካፍ የልህቀት ማዕከል ማረፊያቸውን በማድረግ ልምምዳቸውን እዛው ሲሰሩ እንደቆዩና በቆይታቸው በርካታ አዳዲስ ወጣት ተጫዋቾችን እየጠሩ ለመምረጥ ሙከራ ማድረጋቸውን አስረድተዋል።

አሠልጣኙ ስድስት ተጫዋቾች ወደ ዋናው ቡድን ካደጉ በኋላ በምትካቸው ተጫዋቾችን አምጥተን ከሩዋንዳው ጨዋታ በኋላ በ8 ቀናት ልዩነት ለሴካፋው ውድደር አዳዲስ ተጫዋቾችን ጨምረን ልምምዳችንን ስንሰራ ቆይተናል ብለው “አሁን ላይ በፊት ከነበሩት ተጫዋቾች የሚቀነሱም አሉ። እግር ኳስ የአፈፃፀም ብቃት የሚጠይቅ ነው፡፡ በፊት በሩዋንዳው ጨዋታ ላይ የነበሩ ተጫዋቾች የሚወጡበት መንገድ ይኖራል፡፡ እንደገና ደግሞ ወጣት ተጫዋቾችንም የምናይበት ሁኔታ ይኖራል። ቡድኑን የምናዘጋጀው ለሴካፋ እስከሆነ ድረስ በቀጣይ ሀገሪቱን ወክለው የሚጫወቱ ተጫዋቾችን ከመፍጠር አንፃር ሲሆን ሴካፋ ላይ በደንብ አድርገን ተጫዋቾችን ማየት ይጠበቅብናል፡፡ እኔም ትከረት አድርጌ የምሰራው እዛ ላይ ነው፡፡ በሴካፋው ውድድር ተጫዋቾች ኢንተርናሽናል ልምድ ያገኙበታል። ወደ 5 የሚጠጉ ጨዋታዎችን ስለሚያደርጉ በየጨዋታ ላይ አዳዲስ ነገሮችን የምንማርበትም ይሆናል። ጥሩም ነገር የምንሰራበት ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡” የሚል ሀሳባቸውን መስጠታቸውን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በማኅበራዊ ገፁ አስነብቧል።

አሠልጣኙ ቀጥለው “በነበረን የ12 ቀናት ቆይታ ጠንካራ ዝግጅት አድርገናል። በ12 ቀናት አዲስ ቡድን ነው ያደራጀነው፡፡ እንደገና የተጨመሩ ተጫዋቾች አሉ። በእነዚህም ተጫዋቾች ቡድን መስርቶ ለመጓዝ ትንሽ የሚያስቸግሩ ነገሮች አሉ፡፡ ምክንያቱም አሁን ከጨዋታ የታረፈበት ጊዜ ነው። ተጫዋቾቹ በክለባቸው ውስጥ አይሰሩም ፡፡ በግል ሰርቶ የሚመጣ ተጫዋች ደግሞ አሁን ላይ ውጤታማ ላይሆን ይችላል፡፡ ከውድድር ላይ ቢሆን ኖሮ ሥራ ይቀላል። ዞሮ ዞሮ ሴካፋ ብዙ ወጣቶች የምናይበት እና ለሀገር ግብዓት የሚሆኑ ወጣቶችን የምንይዝበት ስለሆነ ዋና መሠረት አድርጌ የምሰራው ቡድኑ ምን ያህል ኢንተርናሽናል ውድድሮችን ያገኛል የሚለው ላይ ነው።

“ስለዚህ ባለን ዝግጅት የሰራነው በአካል ብቃት፣ በቴክኒክ፣ በታክቲክ እና ሥነ ልቦና ላይ መሠረት ያደረገ ሲሆን እንደ አዲስ የጨመርነው ባለሙያ ሥነ-ምግብ ላይ ነው። በዚህም ተጫዋቾቹ ምን ዓይነት ምግቦችን መመገብ እንደሚገባቸው እየተወያየንበት ነበር፡፡ እንዲሁም ሪከቨሪያቸውን በምን ያህል የጊዜ ልዩነት እንደሚሆን ተጨማሪ ውይይቶችን ከመስክ ልምምዱ ውጪ በክፍል ውስጥ ትምህርት ስንሰራ ቆይተናል፡፡ ሜዳ ላይ ብቻ ባለው ተጨዋች ይቀየራል ብዬ ስለማላስብ እና ሳይንሱም ይህንን ስለማይፈቅድ ይህንን ይዘን በመጓዝ መሠረት መያዙ አስፈላጊ ይሆናል። ዋናው ቡድን የተዘጋጀ ተጫዋች እንዲያገኝም የተሻለ ሥራ እንሰራለን።” በማለት ተናግረዋል።