የ2014 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የሁለቱም ዲቪዚዮን የዕጣ ማውጣት ስርዓት የሚከናወንበት ዕለት ይፋ ተደርጓል፡፡
የ2014 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ እና ሁለተኛ ዲቪዮን ውድድሮች በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስር እንደሚካሄዱ ይታወቃል፡፡ ከቀናቶች በፊት ክለቦች የቅድመ ውድድር ዝግጅት ለመጀመር ሊጎቹ የሚጀመርበትን ቀን ለማወቅ እንዳልቻሉ የገለፁ ቢሆንም የሴቶች ልማት ውድድር ኮሚቴ ባደረገው ስብሰባ ሁለቱም ዲቪዚዮኖች ታኅሣሥ 17 እንዲጀመር መወሰኑን ገልፀን የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ ፌድሬሽኑ የሊጎቹ የዕጣ ማውጣት ስነ ስርአት የሚደረግበት ዕለት ይፋ አድርጓል፡፡
በዚህም መሠረት 13 ክለቦችን ተካፋይ የሚያደርገው የአንደኛ ዱቪዚዮን የዕጣ ማውጣት ስነ ስርአት ኅዳር 7 እንዲሁም 16 ክለቦች ያሳትፋል ተብሎ በሚጠበቀው የሁለተኛ ዲቪዚዮን የማውጣት ቀን ኅዳር 8 መሆኑን ፌዴሬሽኑ ለክለቦች በላከው ደብዳቤ ጠቁሟል፡፡
ፌዴሬሽኑ አያይዞ ክለቦች እስከ አሁን በተቀመጠው ቀነ ገደብ መሠረት በአግባቡ ምዝገባን እየፈፀሙ ባለመሆኑ እስከ ጥቅምት 30 ድረስ ብቻ ተመዝግበው እንዲያጠናቅቁ ማሳሰቢያ አስተላልፏል፡፡