የአዲስ አበባ ከተማ ዋና አሠልጣኝ ወደ መዲናችን እየተመለሱ ነው

ከአራት ቀናት በፊት በአዲስ አበባ ከተማው አሠልጣኝ እስማኤል እና ቡድን መሪው ሲሳይ መካከል የተፈጠረው ፀብ የሚታወስ ሲሆን አሠልጣኙም ከሀዋሳ ወደ አዲስ አበባ ጉዞ መጀመራቸውን አውቀናል።

ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ ዘንድሮ ያደገው አዲስ አበባ ከተማ ከአስፈሪው የሊጉ አጀማመር ጎን ለጎን በሁለተኛ ሳምንት ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ከመጫወቱ በፊት በአሠልጣኙ እስማኤል አቡበከር እና ቡድን መሪው ሲሳይ ተረፈ መካከል የተፈጠረው ፀብ ትኩረትን ስቦ ነበር። ከጨዋታው መጀመር በፊት በማረፊያ ሆቴል በተፈጠረው ፀብ ምክንያትም ‘አሠልጣኙ ቡድን መሪውን በቡጢ በመማታታቸው’ ቡድኑን እንዳይመሩ መታገዳቸውን ቡድን መሪው መግለፃቸው ይታወሳል።

የተፈጠረውን ፀብ ለማጣራት ወደ ሀዋሳ ከቀናት በፊት አምርተው የነበሩት የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ነፃነት ታከለም ሁለቱን አካላት በተናጥል ካናገሩ በኋላ አስፈላጊውን የማጣራት ሥራ ሰርተው ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል። ከተመለሱም በኋላ ደግሞ የተከናወነውን ማጣራት ለክለቡ የዲሲፕሊን ኮሚቴ የሚያቀርቡ ሲሆን ኮሚቴውም አሠልጣኙን እና ቡድን መሪውን በመጥራት ለቦርዱ ግምገማ ለማቅረብ ቀጠሮ ይዟል። ይህንን ተከትሎም የቡድን መሪው አቶ ሲሳይ ቀድመው ወደ አዲስ አበባ የመጡ ሲሆን አሠልጣኝ እስማኤል ደግሞ በዛሬው ዕለት ክለቡ በፃፈው ደብዳቤ መሠረት ከሀዋሳ ወደ አዲስ አበባ ጉዞ እንዳደረገ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

እንደተገለፀው የዲሲፕሊን ኮሚቴውም ለቦርዱ በሚያቀርበው ግምገማ መሠረት በቅርቡ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉም ተመላክቷል። የፊታችን እሁድ ከመከላከያ ጋር የሚጫወተው ክለቡም ዋና አሠልጣኙን በሜዳ ላይ ያገኛል ወይስ አያገኝም የሚለው ጥያቄም አጓጊ ሆኖ ቀጥሏል።

በተያያዘ ዜና የአሠልጣኙ እና የቡድን መሪው ጉዳይ ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት እንዳመራም አውቀናል። ይህንን ተከትሎም ፖሊስ አስፈላጊውን ማጣራት እያደረገ እንደሆነ ተገልጿል።