ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 2ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፬) – ሌሎች ጉዳዮች

በሁለተኛው ሳምንት ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ የታዩ ሌሎች ትኩረት ሳቢ ጉዳዮችን በተከታዩ ፅሁፍ ተመልክተናቸዋል።

👉 የኮቪድ 19 ምርመራ ጉዳይ

በሊጉ ተካፋይ የሆኑት አስራ ስድስቱም ክለቦች ለአባላቶቻቸውን የኮቪድ 19 ምርመራን በተፈቀደ የጤና ማዕከላት ላይ እንዲያደርጉ የሊግ ካምፓኒው አስገዳጅ ህግ ያስቀመጠ ቢሆንም በሁለተኛው የጨዋታ ሳምንት ሲዳማ ቡና በሊጉ አስተዳዳሪ አካል ከተዘረዘሩ ተቋማት ውጭ የምርመራ ውጤት አምጥቷል በሚል በድሬዳዋ ከተማዎች ክስ ቀርቦባቸዋል።

በሲዳማ 3-0 ከተሸነፉበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ የድሬዳዋ ከተማው አሰልጣኝ ዘማሪያም ወልደጊዮርጊስ ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተው ነበር። “ከኮቪድ ምርመራ ጋር ተያይዞ ችግሮች ነበሩ። ተጋጣሚ ቡድን ወረቀት ይዞ አልመጣም። ይሄን በክስ የምንሄድበት ነው የሚሆነው። ከዛ ከዛ ጋር ተያይዞ ተጫዋቾቹ ይሄን ስሜት ይዘውታል። አሁን ፕሪንት አድርጉ ብለናል። ፌዴሬሽኑ አንድ ቦታ ተመርመሩ ነው ያለን። በግድ ተመርምረው የመጣ ወረቀት ነው። ያ ተጫዋቾቹ ስሜት ውስጥ ገብቶ በሥነ ልቦና እንደጎዳብኝ ነው የተሰማኝ።”

እርግጥ ጉዳዩ በሊግ ካምፓኒው በጥልቀት የሚመረምረው ጉዳይ ቢሆንም ከዚህ ቀደም በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ከምርመራ ተቋማት እና ውጤቶች ጋር እንዲሁም ተያያዥ ቅሬታዎች ሲቀርቡ ይደመጣል። በመሆኑም ይሄ የጤንነት ጉዳይ እንደመሆኑ ከየትኛዎቹም አጀንዳዎቹ በበለጠ ሁሉም አካላት መሰል የአሰራር ጥሰቶች ካሉም እንዲታረሙ እና የተሻለ ሁኔታ እንዲፈጠር በቁርጠኝነት መስራት ይኖርባቸዋል።

👉 የቀድሞ ተጫዋቾች በተንታኝነት

ዲኤስቲቪ በዘንድሮው የሊጉ የቀጥታ የጨዋታዎች ስርጭት እያስመለከተን የሚገኘው አንዱ አዲሱ ልምምድ የቀድሞ ተጫዋቾች በጨዋታ ተንታኝነት የማካተቱ ጉዳይ ነው።

ባሳለፍነው የመጀመሪያው የጨዋታ ሳምንት በሀዋሳ ከተማ መለያ የሊጉን ዋንጫ ማሸነፍ የቻለው ሚካኤል ወልደሩፉኤል በጨዋታ ተንታኝነት የተመለከትነው ሲሆን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና አምበልና በ2003 ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን በአምበልነት ያነሳው እድሉ ደረጄ በጨዋታ ተንታኝነት ተሰይሞ ተመልከትናል።

እርግጥ የእግርኳስ ትንተና ከመጫወት እና ከማሰልጠን በዘለለ የተለየ ዕይታ እና ሀሳብን የመግለፅ ክህሎት የሚጠይቅ እንደመሆኑ የሀገራችን የእግርኳስ ተጫዋቾች በዚህ ረገድ ውስንነቶች እንዳለባቸው በግልፅ የሚታይ ቢሆንም በሁለቱ የጨዋታ ሳምንታት የተመለከተናቸው ሚካኤል እና ዕድሉ በዚህ ረገድ የተሻሉ ስለመሆናቸው መናገር ይቻላል። በቀጣይም ሌሎች የቀድሞ ተጫዋቾች ይህን ክህሎት በማዳበር ይበልጥ በሚድያ ሥራዎች ላይ ለመመልከት እንናፍቃለን።

👉 የሀዋሳ ከተማ ደጋፊዎች መነቃቃት

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ታሪክ የመጀመሪያው ከመዲናይቱ ክለቦች ውጭ አሸናፊ መሆን የቻለው ሀዋሳ ከተማ ደጋፊዎች ቁጥር በተለይ በሁለት ሺዎቹ መጀመሪያ የሲዳማ ቡናን መምጣት እንዲሁም የቡድኑ መዳከምን ተከትሎ ቀስ በቀስ ከሜዳ እየጠፉ መምጣታቸውን ተመልክተን ነበር።

ነገርግን ዐምና በተወሰነ መልኩ ደጋፊዎች እንዲገቡ ከተፈቀደ በኋላ ወደ ስታዲየም መመለስ የጀመሩት የሀዋሳ ደጋፊዎች ዘንድሮ ደግሞ ይበልጥ በተሻለ መነቃቃት ላይ የሚገኙ ይመስላል። በእስካሁኑ በሁለቱ የሊግ ጨዋታዎች የሀዋሳ ከተማ ደጋፊዎች በተሻለ ቁጥር እና በክለባቸው መለያ ቀለማት ደምቀው እየተመለከትን እንገኛለን።

ይህም ከቀደመ ክብሩ ቀስ በቀስ እየተንሸራተተ እዚህ ለደረሰው ክለብ ተቆርቋሪ የሆኑ ደጋፊዎች ቁጥር እየተበራከተ ከመጣ ለክለቡ ኃላፊዎችም ሆነ የቡድን አባላት ያላቸውን ለቡድኑ እንዲሰጡ በማስቻል ረገድ ያገባናል የሚሉ እና ‘ለምን?’ የሚሉ ደጋፊዎች መበራከት ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።

👉 የአዲስአበባ ከተማ መለያ

ከጥቂት ዓመታት ቆይታ በኋላ ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊጉ የተመለሱት አዲስአበባ ከተማዎች ከሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ባለፈ በትጥቅ ረገድ በሊጉ ከሚገኙ ክለቦች ደካማ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ቡድኑ በመጀመሪያዎቹ ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ሌሎች የሊጉ ክለቦች ከዓመታት በፊት ይጠቀሙበት የነበረ እና እጅግ ኃላ ቀር ንድፍ ያለው ቀይ መለያን ሲጠቀሙ እየተመለከትን እንገኛለን።

ይህ በ2010 ጅማ አባጅፋር የሊጉ ዋንጫን ሲያነሳ የተጠቀመበትን ይህን መለያ ዳግም አዲስ አበባ ከተማ ከዓመታት በኃላ በሊጉ ለብሶት መመልከታችን እንዲሁም የክለቡ መለያ አርማው መለያው ላይ የታተመበትን መንገድ መመልከት በእራሱ የክለቡ አመራሮች የክለቡን ጉዳይ ችል እንዳሉት የሚያመለከት ነው።

ይህ ባለፉት አስር ዓመታት ከቻይና መነሻውን አድርጎ የተለያዩ የዓለም አቀፍ ግዙፍ ትጥቅ ኩባንያዎች የንድፍ ሀሳብ በመውሰድ እያሻሻለ የሚያቀርበው አኪሌክስ ኩባንያ ምርት የሆነው ይህን መለያ አዲስ አበባ ከተማዎች ከጊዜያት በኃላ እየተቀሙበት ከመገኘታቸው ባለፈ የሊጉ ቡድኖች ከሞላ ጎደል ለራሳቸው የተለየ ንድፍ (Design) የተሰሩ መለያዎችን መጠቀምን እየተለማመዱ በመጡት በዚህ ወቅት አዲስ አበባ ከተማ ግን በተቃራኒው በሌሎች ክለቦች ከዚህ ቀደም የተለመደና ምንም የተለየ የንድፍ ሀሳብ (Design Concept) የሌለው ደካማ መለያን እያስመለከቱን ይገኛል።

👉 በመለያ ላይ ስፖንሰር ብቅ ያለው ድሬዳዋ ከተማ

የምስራቅ ኢትዮጵያው ብቸኛ የፕሪምየር ሊግ ተካፋይ ድሬዳዋ ከተማ በአዲሱ የውድድር ዘመን በአዲስ መለያ ስፖንሰር ብቅ ብሏል። በቅርቡ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ጋር ለኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን በፕላቲየም ደረጃ ስፖንሰር ለመሆን የተሰማማው ኤልኔት ግሩፕ አሁን ደግሞ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር የመለያ ላይ የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ፈፅሞ የድርጅቱ ምርቶች በመለያው ላይ መተዋወቅ ጀምረዋል።

በባለፈው የጨዋታ ሳምንት በድሬዳዋ ከተማ የመጀመሪያ መለያ ላይ የኤልኔትን ማስታወቂያ ስንመለከት በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ በሌላ መለያ የኤልኔት ኩባንያ በውስጥ ካቀፋቸው ዘጠኝ ድርጅቶች አንዱ የሆነው “ታክሲዬ” በመዲናይቱ ከምንመለከታቸው ታክሲዎች ጋር ተመሳሳይ በሆነ የመለያ ቀለም ላይ ሲስተዋወቅ ተመልክተናል።

እርግጥ በድሬዳዋ ከተማ እና በኤልኔት ግሩፕ መካከል ስለተፈፀመው የውል ስምምነት ይፋዊ እና ዘርዘር ያሉ መረጃዎች ባይታወቁም መሰል ስምምነቶች ክለቦቻችን ከመንግሥት ድጎማ ለመላቀቅ በሚያደርጉት በጎ ጥረት ውስጥ የራሳቸውን ጠጠር እንደመጣላቸው ይበል የሚያሰኙ ናቸው። ሌሎችም ክለቦች በዚህ ረገድ መሰል ሥራዎችን መሥራት የግድ ይላቸዋል።

👉 ሰበታ ከተማ የድሬዳዋ እና ወልቂጤን መንገድ ተከትሏል

የእግርኳስን ከሜዳ ላይ ፉክክር ባለፈ ያለውን ተፅዕኖ ለመጠቀም ክለቦቻችን በተለየ በዘንድሮ የውድድር ዘመን ለመጠቀም ተግባራዊ እንቅስቃሴን ስለመጀመራቸው የወልቂጤ ከተማን እና የድሬዳዋ ከተማን ተሞክሮ ተመልክተን ነበር።

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ሰበታ ከተማን የእነዚሁን ክለቦች ተሞክሮ በመከተል በነጩ መለያቸው የግራ የእጅ ክፍሉ ላይ “Sebeta Center of Industry” የሚልን ፅሁፍ በኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ የቀለም መደብ ላይ አሳትመው ተመልክተናል።

ይህም ከተማው የኢንዱስትሪዎች ማዕከል መሆኗን እና ሌሎች በተለያዩ አጋጣሚዎች ይህን መልዕክት የሚመለከቱ እና ገንዘባቸውን ፈሰስ ማድረግ የሚፈልጉ አካላት ሰበታ ከተማን ተቀዳሚ መዳረሻቸው እንዲያደርጉ ያለመ መልዕክትን አስመልክተውናል። ይህም በእጅጉ የሚበረታታ ተግባር ሲሆን አሁንም ቢሆን ሌሎች ቡድኖች ይህን በጎ ጅምር በተጠናከረ መንገድ ለማስቀጠል ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል።

👉 የደጋፊዎች ቁጥር

በአዲሱ የውድድር ዘመን ስታዲየሞች ማስተናገድ ከሚችሉት የደጋፊዎች ቁጥር 25% የሚሆኑ ደጋፊዎች ወደ ሜዳ እንዲገቡ ፈቃድ ቢያገኝም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት አንዳንድ ጨዋታዎች የተመለከትነው የደጋፊዎች ቁጥር ግን ከተቀመጠው ኮታ አንፃር የደጋፊዎች ቁጥር በእጅጉ ልቆ የተመለከትንባቸው ነበሩ።

ሲዳማ ቡና ድሬዳዋ ከተማን ሲረታ በተለምዶ ካታንጋ በሚባለው የሜዳ ክፍል ሙሉ በሙሉ በሚያስብል መልኩ በሲዳማ ደጋፊዎች ተሞልቶ የተመለከትን ሲሆን በተመሳሳይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ቡና ባደረጉት ጨዋታ ከባለሜዳው ቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች በቁጥር የሚልቁ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች እንዲሁም በጥቅሉ ስታዲየሙ ከተፈቀደለት ቁጥር የሚልቁ ተመልካቾችን በስታዲየም ታድመው ተመልክተናል።

የደጋፊዎች በብዛት ወደ ሜዳ መምጣት ለእግርኳሱ የሚሰጠው የተለየ ድባብ ቢኖርም አስቀድሞ የጤና ሚንስቴር እና ሌሎች አካላት በጋራ መክረው ያስቀመጡት ቁጥር ግን ይህን አደገኛ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል የተቀመጠ አስገዳጅ ደንብ እንደመሆኑ የትኛውም አካል ለዚህ አስገዳጅ ደንብ ተገዢ መሆን ይኖርበታል። በተመሳሳይ ለቁጥጥር እንዲያግዝ ደግሞ የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ሙሉ ለሙሉ የመቀመጫ ወንበር የተገጠመለት እንደመሆኑ ወደ ሜዳ የሚገቡ ደጋፊዎችን የትኬት ቁጥር በወንበር ብዛት ጋር መወሰን በመቻሉ በዚህ ረገድ በትኩረት መሠራት ይኖርበታል።

ያጋሩ