ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ – የሶከር ኢትዮጵያ የሁለተኛ ሳምንት ምርጥ 11

የዘንድሮው የውድድር ዓመት ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎችን በመንተራስ የሳምንቱን ምርጥ ቡድን ከተጠባባቂዎች እና ዋና አሰልጣኝ ጋር በዚህ መልኩ መርጠናል።

አሰላለፍ፡ 4-3-3

ግብ ጠባቂ

ሴኮባ ካማራ – አዳማ ከተማ

በሳምንቱ በርከት ያሉ ግብ ጠባቂዎች ጥሩ አቋም አሳይተዋል። ሚኬል ሳማኬ ፣ መሳይ አያኖ ፣ ዳንኤል ተሾመ ፣ ሲልቪያን ግቦሆ እና ታምራት ዳኜ ዓይነት ግብ ጠባቂዎች ከባባድ ኳሶችን ሲያድኑ ተመልክተናል። አዳማ ከተማ በጠባብ ውጤት ጅማ አባ ጅፋርን ሲረታ የነበረው የጊኒያዊው ግብ ጠባቂ የጨዋታ ብቃት ግን ለውጤቱ ትልቅ ድርሻ ነበረው። ካማራ አራት የጅማን ኢላማ የጠበቁ ሙከራዎች ሲያድን የዳዊት ፍቃዱ የቅርብ ረቀት ሙከራ እና የበላይ ዓባይነህ ቅጣት ምት እጅግ ለግብ የቀረቡ ነበሩ።

ተከላካዮች

ወርቅይታደስ አበበ – አርባምንጭ ከተማ

ድንቅ ምሽት ካሳለፈው የሲዳማ ቡናው አማኑኤል እንዳለ እንዲሁም በሸገር ደርቢ ጥሩ አቋም ያሳየው የቅዱስ ጊዮርጊሱ ሄኖክ አዱኛ ጋር ለቦታው ተፎካሪ የነበረው የአርባምንጩ አምበል ቡድኑ አዲስ አበባን ከኋላ ተነስቶ ሲረታ ወሳኝ ሚና ነበረው። ከመከላከል ድርሻው ባለፈ ተጫዋቹ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ወደ ፊት ተጠግቶ ለማድረግ የሞከረው እንቅስቃሴ ፍሬ አፍርቷል። ወሳኙ የአቻነት ግብ በፍቃዱ መኮንን አማካይነት ሲቆጠር መነሻ የነበረው የወርቅይታደስ ኳስ ነበር። ቡድኑ አሸናፊ ያደረገውን የፍፁም ቅጣት ምት ጎል ያስቆጠረው የመስመር ተከላካዩ ሆኗል።

ምኞት ደበበ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ግዙፉ አዲስ ፈራሚ በፈረሰኞቹ ቤት የተደላደለ ይመስላል። በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ከፍሪምፖንግ ሜንሱ ጋር ዳግም የተጣመረው ምኞት በሸገር ደርቢ የተረጋጋ ከነበረው የቡድኑ አጠቃላይ የመከላከል መንገድ ውስጥ ተመራጫችን ሆኗል። ከሁለቱ የመሀል ተከላካዮች የቀኝ ሚና ያለው ተጫዋቹ የቡናን ወደ ግራ ያዘነበለ ጥቃት ከማቋረጥ አንፃር ከሄኖክ አዱኛ ጋር በመሆን ቁልፍ ሥራን መከወን ችሏል።

አሌክስ ተሰማ – መከላከያ

ጦሩ ሰበታ ከተማን በረታበት ጨዋታ እንደቡድን የሰበታን የማጥቃት አማራጮች አቅም ሲያሳጣ የነበረበት የመከላከል አደረጃጀቱ ድንቅ ነበር። በዚህ የቡድን ሥራ ውስጥ በግል የነበሩ አበርክቶዎችን ስመለከት ደግሞ አሌክስ ተሰማን ተመራጭ አድርገነዋል። ለኋላ መስመሩ እና ከፊቱ ላለው ሽፋን ማማር ጥሩ አመራር ሲሰጥ የነበራው የቡድኑ አምበል የፍፁም ገብረማሪያም የግንባር ኳስ ወደ ግብነት እንዳይቀየር የመጨረሻ ሰው ሆኖ ያወጣበት መንገድም ቡድኑን ከመመራት የታደገ ነበር።

ሰለሞን ሀብቴ – ሲዳማ ቡና

ሲዳማ ቡና በድሬዳዋ ከተማ ላይ ላሳየው ብልጫ እና ላገኘው ድል የቡድኑ የግራ ወገን የማጥቃት ድርሻው ከፍ ያለ ነበር። በዚህም የተጋጣሚውን የቀኝ መስመር ጥቃት ከማቋረጥ ባለፈ በተደጋጋሚ በማጥቃቱ ላይ ይሳተፍ የነበረው ሰለሞን ሀብቴ አበርክቶት ተጠቃሽ ነው። ተጫዋቹ አንድ በግቡ ቋሚ የተመለሰ ዕድል እንዲፈጠር ምክንያት ሲሆን ለይገዙ ቦጋለ የግንባር ጎል ኳሱን በማመቻቸት ቀጥተኛ ተሳታፊ ሆኗል።

አማካዮች

ሀብታሙ ተከስተ – ፋሲል ከነማ

ከተከላካዮች ፊት ባለው ቦታ ላይ በሳምንቱ እንደ ሲዳማዎቹ ቴዎድሮስ ታፈሰ እና ብርሀኑ አሻሞ ፣ እንደ ሰበታው ክሪዚስቶም ንታንቢ ፣ እንደመከላከያው ኢምኑኤል ላሪያ ዓይነት ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረጉ ተጫዋቾች ነበሩ። ሆኖም ፋሲል ከወልቂጤ ባደረገው ጨዋታ በመከላከሉ ረገድ የተጋጣሚን ጥቃቶች በማቋረጥ እንዲሁም ማጥቃትን በማስጀመር በመልካም ሁኔታ ኃላፊነቱን ሲወጣ የነበረው ሀብታሙ ተከስተ ተመራጫችን ሆኗል። ተጫዋቹ ከዚህ ዋና ኃላፊነቱ በተጨማሪ ተመራጭ እንዲሆን ያደረገው ቡድኑን አሸናፊ ያደረችውን የበዛብህ መለዮን ጎል ማመቻቸቱ ሆኗል።

ሀይደር ሸረፋ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ሀይደር ከተከላካዮች ፊት ባለው ቦታ ላይ ጨዋታውን ቢጀምርም በማጥቃት ላይ ከነበረው ተሳትፎ እና ለውጤቱ ባደረገው አስተዋፅዖ መነሻነት እንዲሁም ወደ ፊት ተጠግቶ የመጫወት ሚናን መወጣት በመቻሉ አማካይ ክፍላችን ላይ ተመራጭ አድርገነዋል። ለአከራካሪዋ የኦሮ አጎሮ ጎል መቆጠር ምክንያት የነበረው ተጫዋቹ ከኋላ ተነስቶ ሳጥን ውስጥ ይደርስበት በነበረው አኳኋን እና የግል ብቃቱን በሚገባ ባሳየበት ሁኔታ ሦተኛዋን ግብ ማስቆጠር ችሏል። ቡድኑ ውጤቱን ከፍ ያደረገበት የመጨረሻው የፍፁም ቅጣት ምት ጎልም የሀይደር ሸረፋ ነበር።

ፍሬው ሰለሞን – ሲዳማ ቡና

ቀልጣፋው አማካይ ከሲዳማ ቡና ጋር ጥሩ አጀማመር በማድረግ ላይ ይገኛል። በመጀመሪያው የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ በማጥቃትም ሆነ በመከላከል ተሳትፎ ጥሩ መንቀሳቀስ ችሎ የነበረው ፍሬው ድሬዳዋ ላይ ይበልጥ ጎልቶ ወጥቷል። በመጀመሪያው አጋማሽ ያደረጋቸው ጠንካራ ሙከራዎች ሁለት ጊዜ በግቡ ቋሚ ቢመለሱበትም በቡድኑ የማጥቃት ሂደት ላይ ዋና ተዋናይ መሆኑን በመቀጠል ሁለተኛውን ጎል ከመረብ ማዋሀድ ችሏል።

አጥቂዎች

ፍቃዱ መኮንን – አርባምንጭ ከተማ

በጨዋታ ሳምንቱ የሙሉ ደቂቃ የፊት መስመር ተሰላፊዎች በመሆን ለቡድናቸው ስኬት በማስቆጠርም ሆነ በማመቻቸትም ጥሩ ሚና የተወጡ ተጫዋቾች ነበሩ። በጥቂት ደቂቃዎች ተሳትፎ ተመሳሳይ ውጤት በማስገኘት ግን ፍቃዱን የሚስተካከል አልነበረም። 47ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ሜዳ የገባው ፍቃዱ ለተጋጣሚ ተከላካዮች ራስ ምታት መሆን ችሏል። የቡድኑ ማጥቃት ዋና ተዋናይ በመሆንም የአቻነቱ ጎል ከሳጥን ውጪ በመምታት ሲያስቆጥር ቡድኑን አሸናፊ ያደረገው የፍፁም ቅጣት ምት እንዲገኝ ያስቻለውን ተሻጋሪ ኳስ ወደ ሳጥኑ በማድረስ ወሳኝ ሚና ተወጥቷል።

ኦሴ ማዉሊ – ባህር ዳር ከተማ

በመጀመሪያው ሳምንት ሁለት ግቦችን በማቆጠር በምርጫችን ውስጥ ተካቶ የነበረው ማዉሊ በድጋሚ ተመራጭ ሆኗል። ከባድ በነበረው የሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታ አንድ ያለቀለት ዕድል በመፍጠር እንዲሁም በመሳይ አያኖ ጥረት ግብ ከመሆኑ የዳኑ ሁለት ኳሶችን በመሞለር ከወትሮው ተቀዛቅዞ በነበረው የባህር ዳር የማጥቃት ሂደት ውስጥ በንቃት ሲሳተፍ ቆይቷል። ጨዋታው ያለግብ ሊጠናቀቅ ሲቃረብ ግን ከሳጥኑ መግቢያ ላይ በመቀስ ምት ወደ ግብ የላካት ኳስ ባህር ዳርን የሙሉ ነጥብ ባለቤት ማድረግ ችላለች።

ይገዙ ቦጋለ – ሲዳማ ቡና

በሁለተኛው ሳምንት ከፍ ባለ ጫና ወደ ሜዳ ገብቶ ደምቆ የወጣ ተጫዋች ከፈለግን ከይገዙ ቦጋላ የሚቀድም የለም። የሲዳማ ቡና የፊት መስመር የአጨራረስ ብቃት ሲወረፍ የነበረ ቢሆንም በድጋሚ የፊት መስመሩን እየመራ የገባው ይገዙ ልዩነት መፍጠር ችሏል። ተደጋጋሚ ጉዳቶች ከሜዳ እያራቁት የነበረው ይገዙ ዘንድሮ ሌላ መልክ እንደሚኖረው በጠቆመበት ጨዋታ ከቡድኑ ሦስት ግቦች ሁለቱን በድሬዳዋ ከተማ መረብ ላይ ማሳረፍ ችሏል። በአከራካሪ የዳኝነት ውሳኔ ተሻረበት እንጂ ተጫዋቹ ሐት-ትሪክ ለመስራትም ተቃርቦ ነበር።


አሰልጣኝ – ዘሪሁን ሸንገታ

በሸገር ደርቢ ቅዱስ ጊዮርጊስን በመምራት ለድል ያበቁት ምክትል አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታን ከአሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ እና ከአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ጋር በማፎካከር የሳምንቱ ምርጥ አሰልጣኝ አድርገናቸዋል። አሰልጣኝ ዘሪሁን የዋና አሰልጣኙ ዝላትኮ ክራምፖቲች በሀዘን ምክንያት አለመኖርን ተከትሎ በድንገት የተረከቡትን ኃላፊነት በድል መወጣታቸው አስመርጧቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ ስኬታማ የጨዋታ ሳምንት ካሳለፉት ሁለቱ አሰልጣኞች ጋር ሲተያይ የሸገር ደርቢ ጨዋታ ክብደት ምክትል አሰልጣኙን የተሻለ ነጥብ አሰጥቷቸዋል።

ተጠባባቂዎች

ሚኬል ሳማኬ – ፋሲል ከነማ
በረከት ወልደዮሐንስ – ወላይታ ድቻ
አማኑኤል እንዳለ – ሲዳማ ቡና
ኢማኑኤል ላሪያ – መከላከያ
ሙሉቀን አዲሱ – አዲስ አበባ ከተማ
ሀብታሙ ንጉሤ – ወላይታ ድቻ
ቡልቻ ሹራ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ዳዋ ሆቴሳ – አዳማ ከተማ