ሲዳማ ቡና እና ኢትዮጵያ ቡና የገንዘብ ቅጣት ተላለፈባቸው፡፡
የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛው ሳምንት መርሀግብሮች ከትላንት በስቲያ ተደርገው መጠናቀቃቸው ይታወሳል፡፡ በዚህ የጨዋታ ሳምንት ሁለት ክለቦች በሁለት የተለያዩ ክለቦች የገንዘብ ቅጣት ተላልፎባቸዋል፡፡
ዕለተ ዕሁድ ጥቅምት 14 ሲዳማ ቡና ድሬዳዋ ከተማን ሦስት ለምንም ከረታበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የድሬዳዋ ከተማ ክለብ ”ሲዳማ ቡናዎች ከተፈቀደላቸው የህክምና ማዕከል ውጪ ተጫዋቾቻቸውን የኮቪድ 19 ምርመራን አስመርምረው መጥተዋል፤ ይሄ ደግሞ አግባብ አይደለም። ” በማለት ክለቡ ለሊግ ካምፓኒው የዲሲፕሊን ኮሚቴ በደብዳቤ አስገብቶ የነበረ ሲሆን ኮሚቴውም ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ ሲዳማ ቡናን ጥፋተኛ በማለት የሀያ አምስት ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ቀጥቷል፡፡
በሌላ ቅጣት ማክሰኞ ጥቅምት 16 በሸገር ደርቢ ኢትዮጵያ ቡና በቅዱስ ጊዮርጊስ 4ለ1 በተረታበት ጨዋታ ላይ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በዕለቱ ዳኛን አፀያፊ ስድብ መሳደባቸውን ኮሚቴው በመግለፅ ኢትዮጵያ ቡናን የ50 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት አስተላልፎበታል፡፡
በተያያዘ ሌላ ዜና የፕሪምየር ሊጉ አስራ ስድስቱ ክለቦች በዛሬው ዕለት ከሊግ ካምፓኒው አመራሮች ጋር ከልምምድ ሜዳ ጋር በተያያዘ በሚነሱ እና ተያያዥነት ባላቸው ቅሬታዎች ላይ ስብሰባን ማድረጋቸውን ሊግ ካምፓኒው አስታውቋል።