ቅድመ ዳሰሳ | ሀዋሳ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና

የሦስተኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች መጀመራቸውን የሚያበስረውን መርሐ-ግብር እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።

ከሽንፈት የመጣው ሀዋሳ ከተማ እና ተከታታይ ድል ያስመዘገበው ሲዳማ ቡና ነገ 9 ሰዓት የሚያደርጉት ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር እንደሚታይበት ይገመታል። በተለይ ውድድሩ እየተከናወነበት በሚገኘው ሀዋሳ በርካታ ደጋፊዎች ያላቸው ሁለቱ ክለቦች በደማቅ ድባብ መርሐ-ግብራቸውን እንደሚያከናውኑ ይጠበቃል።

በሊጉን የመክፈቻ ጨዋታ ጅማን ካሸነፉ በኋላ በሁለተኛው ሳምንት በወላይታ ድቻ የተረቱት ባለሜዳዎቹ ሀዋሳ ከተማዎች ሊጉ ለቀናት ከመቋረጡ በፊት ዳግም ወደ አሸናፊነት መመለስን እና ደረጃቸውን ማሳደግን እያለሙ ጨዋታውን ይቀርባሉ።

በአሠልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ የሚመራው ክለቡ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ሙሉ የጨዋታ ክፍለጊዜን ወጥ በሆነ እንቅስቃሴ መጫወት ድክመቱ ሆኖ ታይቷል። ቡድኑ በጥሩ ተነሳሽነት ጨዋታውን በመቅረብ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት ሲያስመለክት ብናስተውልም ደቂቃዎች እየገፉ ሲሄዱ ግን መቀዛቀዞች ታይተውበታል። ይህ የጨዋታውን ሙሉ ደቂቃ በተመጣጠነ መንገድ የመጫወት ከፍተኛ ክፍተትን ማረም ካልቻለም ሊጎዳ ይችላል። ከዚህ በተቃራኒ ግን አሠልጣኙ በተለያዩ አማራጮች ለመጫወት የሚያስችላቸው መሳሪያ እጃቸው ላይ አለ። በዋናነት ደግሞ ለድንገተኛ መልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎች የሚመቹ የፊት መስመር አጥቂዎቻቸውን ያማከለ አጨዋወት ከተከተሉም ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይታሰባል።

ምናልባት መነሳት ያለበት እና በወላይታ ድቻው ጨዋታ የታየው ሌላኛው የቡድኑ ድክመት ደግሞ በተከላካይ መስመሩ ላይ ያለው የመናበብ ችግር ነው። ይህ ክፍተትም በጨዋታው ለመልሶ ማጥቃት ተጋላጭ እንዲሆን ሲያደርገው ተስተውሏል። የሲዳማ ጠንካራ ጎን ደግሞ ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ መሆኑ ሲታሰብ ለአሰልጣኝ ዘርዓይ ራስ ምታት መሆኑ አይቀሬ ያረገዋል። በዋናነት ግን ከፍሬው እና ከቴዎድሮስ የሚነሱ የመሐል ለመሐል ጥቃቶችን ቡድኑ በሚገባ መክቶ እንደተገለፀው ፈጣኖቹን ብሩክ፣ ኤፍሬም እና መስፍንን ያማከለ አጨዋወት የሚከተል ከሆነ በጎ ነገር ከሜዳ ይዞ ሊወጣ ይችላል።

በሀዋሳ በኩል የበቃሉ ገነነ መግባት አጠራጣሪ ሲሆን የሥራ ፍቃዱን ሳያገኝ ሁለት ጨዋታዎች ያመለጡት ጋናዊው የግብ ዘብ መሐመድ ሙንታሪ ደግሞ ጉዳዩን በመጨረሱ ለጨዋታው ዝግጁ ሆኗል።

ትክክለኛ የዋንጫ ተፎካካሪ እንደሆነ በግልፅ እያሳየ የሚገኘው የአሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ሲዳማ ቡና ሁለተኛ ተከታታይ ድሉን በማስመዝገብ ወደ ደረጃ ሠንጠረዡ አናት ለመጠጋት ጠንክሮ ወደ ሜዳ ይገባል።

በአዲሱ የውድድር ዓመት እንደ ሲዳማ ቡና የጎል ዕድሎችን በብዛት የሚፈጥር እና የማጥቃት አጋጣሚዎችን ከተለያዩ መንገዶች የሚያገኝ ቡድን የለም ማለት ማጋነነ አይሆንም። በግራ፣ በቀኝ፣ በመሐል የሚነሱ ኳሶች እንዲሁም ተሻጋሪ እና ረጃጅም ኳሶችን ከየአቅጣጫው በመጠቀም ተጋጣሚ ላይ ጫና ለመፍጠር የሚሞክረው ሲዳማ ነገም ይህንኑ ትጋቱን ሜዳ ላይ እንደሚደግም ይገመታል። በተለይ በተለይ ደግሞ በሁለቱ ጨዋታዎች እንደታየው በመስመር በኩል የሚደረጉ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች የቡድኑ ዋነኛ ትኩረት ሊሆን ይችላል።

በሁለተኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ግብ ካላስተናገዱት ሦስት ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ሲዳማ (ከመከላከያ እና ባህር ዳር) ጠንካራ ጎኑ ነገ በደንብ ሊፈተን ይችላል። ከምንም በላይ ደግሞ ፈጣን የመስመር ላይ ሩጫዎችን በማድረግ ሳጥን ውስጥ መግባት የሚያዘወትሩትን የሀዋሳ ተጫዋቾች የሚቆጣጠሩበት መንገድም ይጠበቃል። ከዚህ ውጪ የቡድኑ አጥቂ ይገዙ ቦጋለ ግብ ማስቆጠር መጀመሩ ጥሩ ሆኖ ሳለ የሚነሱበትን ጥያቄዎች ለመቀነስ በወጥ ብቃት የጎል ምንጭ ሆኖ መዝለቅ ይጠበቅበታል። ከዚህ ውጪ ሌሎች ተጫዋቾችም የቡድኑ የግብ ማስቆጠሪ አማራጭ ሊሆኑ ይገባል። በቡድኑ ውስጥ ምንም አይነት ጉዳት እንደሌለም ለማወቅ ተችሏል።

ይህንን ጨዋታ ፌዴራል ዋና ዳኛ ባህሩ ተካ በአልቢትርነት የሚመሩት ይሆናል።

ግምታዊ አሠላለፍ

ሀዋሳ ከተማ (4-2-3-1)

ዳግም ተፈራ

ዳንኤል ደርቤ – ላውረንስ ላርቴ – ፀጋሰው ድማሙ – መድሃኔ ብርሃኔ

አቡዱልባሲጥ ከማል – ዳዊት ታደሠ

ኤፍሬም አሻሞ – ወንድማገኝ ኃይሉ – መስፍን ታፈሰ

ብሩክ በየነ

ሲዳማ ቡና (4-2-3-1)

ተክለማሪያም ሻንቆ

አማኑኤል እንዳለ – ጊት ጋትጉት – ያኩቡ መሀመድ – ሰለሞን ሀብቴ

ብርሀኑ አሻሞ – ቴዎድሮስ ታፈሰ

ብሩክ ሙሉጌታ – ፍሬው ሰለሞን – ፍራኒሲስ ካሀታ

ይገዙ ቦጋለ

ያጋሩ