ቅድመ ዳሰሳ | አዳማ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ

የነገ ምሽቱን ጨዋታ የተመለከቱ ጉዳዮችን እንዲህ አንስተናል።

ጨዋታው ሁለተኛው ሳምንት በውጤት ሰምሮላቸው ያሳለፉ ሁለት ቡድኖች የሚገናኙበት ነው። ከወልቂጤ ነጥብ ተጋርቶ የነበረው አዳማ ከተማ ጅማ አባ ጅፋርን መርታት ሲችል በድሬዳዋ ሽንፈት ቀምሶ የነበረው ወላይታ ድቻም ሀዋሳ ከተማን አሸንፎ ቀና ማለት ችሏል። የነገው ጨዋታ ውጤትም ማናቸውን ተከታታይ ባለድል አድርጎ ይጠናቀቃል የሚለው ጉዳይ ተጠባቂ ነው።

የነገውን ጨዋታ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በተለያዩ የጨዋታ ምርጫዎች መካከል የሚደረግ ይመስላል። ኳስ ይዞ የመጫወት ዝንባሌ ያላቸው አዳማዎች በሁለተኛው ጨዋታ አማካይ ክፍላቸው ላይ ቅያሪዎች አድርገው ያገኙት ውጤት በተወሰኑ ማስተካከያዎች የሚቀጥል ይመስላል። በጅማው ጨዋታ የታየው ኳስ ይዞ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚያደርገው እንቅስቃሴ እና የጨዋታውን ሚዛን የጠበቀበት አኳኋን ለነገ የሚተርፍ ነው። ያም ቢሆን በርከት ያሉ ሙከራዎችን ማስተናገዱ እና በጅማው ጨዋታ ማብቂያ ላይ የታየበት ጨዋታ የማቀዝቀዝ ክፍተት ተሻሽሎ ሊቀርብ የሚገባው ነበር። በሁለተኛው ጨዋታ ከኋላ በሦስት ተከላካዮች ወደሚጀምር አደራደር የመጣው ወላይታ ድቻ ደግሞ ሁነኛ የመልሶ ማጥቃት ቡድን መሆኑን አስመልክቶናል። ቡድኑ ብዙ ለውጦች ሳያደርግ ወደ ሜዳ እንደሚመለስ ሲጠበቅ በቀጥተኛ ኳሶች ማጥቃት ግብ ካገኘ ደግሞ እንደ ሀዋሳው ጨዋታ ሁሉ ጠንከር ባለ መከላከል ግቡን የመዝጋት አዝማሚያ ሊኖረው ይችላል።

ሁለቱ ተጋጣሚዎች የሚያኩራራ የአጨራረስ ብቃት አልተስተዋለባቸውም። አዳማ ከተማ የዳዋ ሆቴሳ የቆመ ኳስ አጠቃቀምን ፍሬ ቢበላም እስካሁን ከክፍት ጨዋታ ከሦስትዮሽ የማጥቃት ጥምረቱ ግቦችን አላገኘም። ወላይታ ድቻም በተመሳሳይ የሀዋሳውን ጨዋታ ዘግይቶ ወደ ሳጥን በደረሰው አማካዩ ሀብታሙ ንጉሴ ግብ ነበር የተወጣው። በተቃራኒው የአዳማ የኋላ ክፍል ከመጀመሪያው ጨዋታ ሳይለወጥ ያየነው ሲሆን ድቻም የቅርፅ ለውጥ አደረገ እንጂ የመከላከል መስመር ተሳላፊዎቹን ለመለወጥ አልሞከረም። ይህም በሁለቱም ሳጥኖች ውስጥ ጠቃሚ መሆናቸውን ለማሳየት የሚጥሩ አጥቂዎችን የተሻለ መረጋጋት ላይ ካሉ የተከላካይ ክፍሎች የሚያገናኝ መሆኑ ፍልሚያው አየል ሊል እንደሚችል ይነግረናል።

ጨዋታው አዳማ ያለመሸነፍ ሂደቱን ለማስቀጠል የሚወጥንበት ነው። ለዚህም ከኳስ ጋር ጥሩ መግባባት ያላቸው እንደ ኤሊያስ ማሞ ዓይነት አማካዮቹን የመጨረሻ ኳሶች ጠቅጠቅ ሊል በሚችለው የተጋጣሚው የኋላ ክፍል ማሳለፍ ይጠበቅበታል። ከዚህ ውጪ እንደ እንድሪስ ሰዒድ ካሉ አማካዮች ወደ ፊት የሚጣሉ ኳሶች ለእነስንታየሁ መንግሥቱ የጠራ የግብ ዕድል እንዲፈጥር የድቻዎች ፍላጎት ይሆናል። በመስመር በኩልም እንደ ሚሊዮን ሰለሞን እና ደስታ ዮሃንስ ያሉ የአዳማ መስመር ተከላካዮች ከኳስ ጋር የሚደረግ የማጥቃት ተሳትፎ የቁጥር ብልጫን ለማሳካት ለአዳማ እጅግ ወሳኝ ነው። በዚሁ አቅታጫ ዘንዶሮም የቀጠለቅ የያሬድ በዛብህ የወላይታ ድቻ መስመር ተመላላሾች ተሻጋሪ ኳሶች እና ቀጥተኛ ሩጫዎች የቦታውን ፍልሚያ ወሳኝ እንደሚያደርገው ይጠበቃል።

አዳማ ከተማ እርግጠኛ የሆነ የጉዳት ዜና የለበትም። በመጨረሻው ጨዋታ ድንቅ ብቃት ያሳየው እና የሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ኮከብ ግብ ጠባቂ የሆነው ሴኩባ ካማራ መሰለፍ ግን አጥራጣሪ ሆኗል። ከዚህ በተለየ ግን በግል ጉዳይ ከቡድኑ ጋር ያልነበረው ጀማል ጣሳው መመለሱ ተሰምቷል። የወላይታ ድቻ ስብስብ ግን ያለጉዳት እና ቅጣት ጨዋታውን ያደርጋል።

ፌደራል ዳኛ ዮናስ ካሣሁን ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት የመምራት ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ 12 ጊዜ የመገናኘት ታሪክ አላቸው። አንድ ጊዜ ብቻ ነጥብ የተጋሩ ሲሆን ወላይታ ድቻ ስድስት ጊዜ አዳማ ደግሞ አምስት ጊዜ ድል ቀንቷቸዋል። በጨዋታዎቹ 25 ግቦች ሲቆጠሩ ወላይታ ድቻ 14 አዳማ ከተማ ደግሞ 11 ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

አዳማ ከተማ (4-3-3)

ሴኩባ ካማራ

ሚሊዮን ሠለሞን – አሚን ነስሩ – ቶማስ ስምረቱ – ደስታ ዮሐንስ

ኤሊያስ ማሞ – ዮሴፍ ዮሃንስ – አማኑኤል ጎበና

አሜ መሐመድ – ዳዋ ሆቴሳ – አብዲሳ ጀማል

ወላይታ ድቻ (3-5-2)

ጽዮን መርዕድ

በረከት ወልደዮሐንስ – አንተነህ ጉግሳ – ደጉ ደበበ

ያሬድ ዳዊት – ሀብታሙ ንጉሴ – ንጋቱ ገብረስላሴ – እንድሪስ ሰዒድ – አናጋው ባደግ

ምንይሉ ወንድሙ – ስንታየሁ መንግሥቱ