አራት ኢትዮጵያዊያን እንስት ዳኞች የሴካፋ ጨዋታዎች ይመራሉ

አራት ኢትዮጵያዊያን ዳኞች የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ጨዋታን ለመምራት ወደ ካምፓላ ሲያመሩ ሦስት ተጨማሪ ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎችም ወደ ስፍራው ተጉዘዋል፡፡

የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ዋንጫ ነገ በስድስት የቀጠናው ሀገራት መካከል በዩጋንዳ ካምፓላ በሚደረጉ ሁለት መርሀግብሮች ይጀመራሉ፡፡ በዙር በነጥብ ብልጫ አሸናፊው የሚለይበት የዘንድሮው ውድድር ሀገራችን ኢትዮጵያ በነገው ዕለት የመጀመሪያ ጨዋታዋን ከጅቡቲ አቻዋ ጋር ጨዋታዋን የምታደርግ ሲሆን በተጨማሪነትም ኢትዮጵያዊያን ዳኞች፣ ኮሚሽነር እና የውድድሩ ኮሚቴዎች በዚህ ውድድር ላይ በሴካፋ ተመርጠው በዛሬው ዕለት ወደ ስፍራው እንዳቀኑ ሶከር ኢትዮጵያ ለማወቅ ችላለች፡፡

ከሰሞኑ በአፍሪካ የሴቶች ዋንጫ ማጣሪያ በዳኝነት ሲሳተፉ የነበሩት ዋና ዳኛ አስናቀች ገብሬ፣ በረዳትነት ወይንሸት አበራ እና ብርቱካን ማሞ ለሴካፋውም ውድድር የተመረጡ ልምድ ያላቸው ዳኞች ሲሆኑ ሌላኛዋ ዋና ዳኛ ፀሐይነሽ አበበም በዳኝነት ለሴካፋው ተካታ አምርታለች፡፡

ከዳኞች በተጨማሪ በቅርቡ በናይሮቢ ከ20 ዓመት በታች የማጣርያ የኬንያ እና የደቡብ ሱዳንን ጨዋታ በኮሚሽነርነት የመራችው ሲስተር ሣራ ሰዒድ ውድድሩን ኮሚሽነር ሆና እንድትመራ ስትመረጥ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት አቶ አብዱራዛቅ ሀሰን እና በፌዴሬሽኑ የውድድር ባለሙያ የሆነችው ምህረት ጉታ የሴካፋ ኮሚቴ ውስጥ በመመረጣቸው ወደ ስፍራው በጋራ ከሰዓታት በፊት አምርተዋል፡፡