ከኅዳር 23 እስከ ታህሳስ 8 ድረስ ሊከናወን የነበረውን የሴካፋ የሴቶች ውድድር ልታስተናግድ የነበረችው ጂቡቲ ራሷን ከአዘጋጅነት አንስታለች።
የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ የሴቶች ዋንጫ ውድድር ከአንድ ወር በኋላ በጂቡቲ አስተናጋጅነት እንዲከናወን ቀጠሮ ተይዞለት ነበር። ይህ ቢሆንም ግን የውድድሩ አስተናጋጅ ሀገር የነበረችው ጂቡቲ ለሴካፋ በላከችው ደብዳቤ ውድድሩን እንደማታስተናግድ አስታውቃለች።
የጂቡቲ እግርኳስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ሀላፊ ዮሱፍ አህመድ መሐሙድ በትናንትናው ዕለት ለሴካፋ በላኩት ደብዳቤም የቦርድ አባላት ከሦስት ቀናት በፊት ባደረጉት ስብሰባ ላይ ውድድሩ እንዲከናወንበት ታስቦ የነበረው ኤል ሀጂ ሀሰን ጉሌድ ስታዲየም እንዲያገግም በማሰብ ከአዘጋጅነት ራሳቸውን ማግለላቸውን ጠቁመዋል። ይህንን ተከትሎ ሌሎች አባል ሀገራት ውድድሩን ለማስተናገድ ፍላጎት ካላቸውም ውድድሩ እንደሚዘጋጅ ተመላክቷል።