ተጠባቂ የነበረው የሀዋሳ ከተማ እና የሲዳማ ቡና ሮድዋ ደርቢ በሀዋሳ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ሀዋሳ ከተማ ከመጨረሻ ጨዋታው አራት ለውጦችን አድርጓል። የግብ ጠባቂው መሀመድ ሙንታሪን ግልጋሎት ከዛሬ ጀምሮ የሚያገኘው ቡድኑ ዳግም ተፈራን ሲያሳርፍ መሀል ላይ በቃሉ ገነነ የዳዊት ታደሰን ቦታ ወስዷል። በመስመር ተከላካይ በኩል ዳንኤል ደርቤ እና ዮሐንስ ሱጌቦ ወደ ሜዳ ሲመለሱ አዲስአለም ደበበ እና መድሀኔ ብርሀኔ አርፈዋል። በሲዳማ በኩል በተደረገው ብቸኛ ለውጥ ደግሞ የመሀል ተከላካዩ ተስፋዬ በቀለ ጉዳት ላይ በሚገኘው ጊት ጋትጉት ቦታ ተተክቶ ወደ ሜዳ ገብቷል።
ከጅምሩ ፈጠን ያለ እንቅስቃሴን ያሳየን የመጀመሪያ አጋማሽ ብርቱ ፉክክር የተደረገበት ነበር። መልሶ ማጥቃትን ምርጫቸው ያደረጉት ሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ በቶሎ ግብ አግኝተዋል። 4ኛው ደቂቃ ላይ ሀዋሳ ከተማ መሀል ለመሀል በሰነዘረው ጥቃት ብሩክ በየነ የሲዳማን ተከላካዮች ወደ መሀል በመሳብ ከወንድምአገኝ ኃይሉ ጋር አንድ ሁለት በመቀባበል ከሳጥን ውስጥ ያደረገው ሙከራ በተክለማሪያም ሻንቆ ሲመለስ አግኝቶ ኤፍሬም አሻሞ ወደ ግብነት ለውጦታል።
ከግቡ በኋላም የሲዳማዎች ከኋላ አለመናበብ ሀዋሳን ተጨማሪ አጋጣሚ ሊያስገኝ ሲቃረብ ሲታይ ቀስ በቀስ ኳስ በሲዳማዎች ስር መዋል ጀምራለች። ያም ቢሆን የመስመር አጥቂዎቻቸውን በመሳብ በቶሎ የመከላከል ቅርፃቸውን ይይዙ የነበሩት ሀዋሳዎች ኃይልም በመቀላቀል በቀላሉ ክፍተት የሚሰጡ አልሆኑም። በዚህ ምክንያት የሲዳማ ሙከራዎች በአብዛኛው ከቆሙ ኳሶች መነሻቸውን አድርገዋል። ከዚህም መካከል 14ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬው ሰለሞን ከሰለሞን ሀብቴ ቅጣት ምት ተጨረርፎ ከቅርብ ርቀት ያገኘውን ዕድል ወደላይ ልኮታል።
ጉሽሚያዎች በተለይም በሀዋሳ በኩል በርከት ብለው በቅጣት ምቶች እና ቢጫ ካርዶች ተጋግሎ የቀጠለው ጨዋታ ሲዳማዎች መሀል ለመሀል ሀዋሳዎች ደግሞ በሁለቱ ክንፎች ከሲዳማዎች ስህተት ጥቃቶችን ለመሰንዘር ሲሞክሩ ቆይተዋል። ሲዳማዎችም ከሌላ የቆመ ኳስ የግብ ዕድል አግኝተዋል። 33ኛው ደቂቃ ላይ ከሰለሞን ማዕዘን የተሻገረን ኳስ አብዱልባስጥ ከማል በእጁ በመንካቱ የፍፁም ቅጣት ምት ለሲዳማ ቡና ተሰጥቶ ይገዙ ቦጋለ ወደ ግብነት ቀይሮታል።
ከግቡ በኋላ አቻ ለመሆን የተንቀሳቀሱት ሀዋሳዎች የማዕዘን ምቶች አግኝተዋል። በተለይም አወዛጋቢ በሆነ ሁኔታ በቀጥታ ከማዕዘን የመጣውን ኳስ ተክለማሪያም የያዘበት መንገድ መስመሩን አልፏል የሚል ጥያቄ ከሀዋሳዎች ተነስቶ የነበረ ቢሆንም ፌደራል ዳኛ ባህሩ ተካ ጨዋታውን አስቀጥለዋል። ሲዳማዎች በሁለተኛው የሜዳ አጋማሽ ገብተው ከመስመር በመነሳት ለማጥቃ ያደርጉ በነበሩት ጥረቶች 39ኛው ደቂቃ ላይ የሰለሞን ሀብቴ ተሻጋሪ ኳስ አደገኛ ቦታ ላይ ነጥሮ በፍሬው ሰለሞን ተነክቶ የመቆጠር ዕድል ቢኖረውም መሀመድ ሙንታሪ አውጥቶታል። ጉሽሚያዎች በበረከቱበት ጨዋታ ብርሀኑ አሻሞ አጋማሹ ከመጠናቀቁ በፊት ተጎድቶ በሙሉዓለም መስፍን ተተክቷል።
ሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያው ፍትጊያ ቀነስ ብሎ የጀመረበት ነበር። ሀብታሙ ገዛኸኝ በፍራንሲስ ካሀታ ለውጠው ያስገቡት ሲዳማዎች ጫን ብለው የመጀመር ምልክት ቢያሳዩም ሀዋሳዎች እንደቀድሞው ሁሉ ክፍተት አልሰጡም። የሀዋሳዎችም ጥቃት ደጋግሞ ወደ ሳጥን ሳይደርስ እንቅስቃሴው በአመዛኙ በሁለቱ ሳጥኖች መካከል የሚቆራረጥ ሆኗል። የመጀመሪያው ሙከራም 62ኛው ደቂቃ ላይ ዳንኤል ደርቤ ከግብ ክልል በግንባር ያራቀውን ኳስ ይገዙ ከሳጥን ውጪ በቀጥታ የመታው ሲሆን ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል።
በሂደት ሁለቱም ቡድኖች በመስመር ያላቸውን አደገኝነት የሚያሳዩባቸው ቅፅበቶች ይታዩ ነበር። ሀዋሳ በግራ በመስፍን ታፈሰ ሲዳማም በግራ በፍሬው እና ሀብታሙ ጥረት ሰብረው ለመግባት ሞክረዋል። 69ኛው ደቂቃ ላይ በሲዳማ በኩል በዚሁ በግራ በኩል የተገኘውን የቴዎድሮስን ቅጣት ምት ሀብታሙ በግንባሩ ጨርፎ የአጋማሹን አደገኛ ሙከራ ሲያደርግ ሙንታሪ እንደምንም አድኖታል። ከዚህ እንቅስቃሴ የቀጠለው የማዕዘን ምትም በሀብታሙ ተገጭቶ ለጥቂት የወጣ ነበር።
በመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች የሀዋሳዎች ጥቃት ሳጥን ውስጥ መዝለቅ ሲጀምር 76ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ በየነ ከወንድምአገኝ እና ዳንኤል ጋር ቅብብሎችን ከውኖ ሳጥን ውስጥ በመግባት ለመድኃኔ ብርሀኔ የጠራ የግብ ዕድል ቢፈጥርም ኤፍሬም አሻሞን ቀይሮ የገባው መድኃኔ ወደ ላይ ሰዶታል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ግን የሁለቱ ተጨዋቾች ጥምረት ለሀዋሳ ውጤት አስገኝቷል። ከሙንታሪ በረጅሙ የተላከውን ኳስ መስፍን ሲጨርፍለት መድኃኔ ከተከላካዮች ጋር ታግሎ ያመቻቸውን ብሩክ በየነ በሲዳማ መረብ ላይ አሳርፎታል።
ሀዋሳዎች 2-1 መምራት ከጀመሩ በኋላ የመልሶ ማጥቃት ምልክቶች ቢታዩባቸውም ጥንቃቄ ጨመር አድርገዋል። ሲዳማዎች ወደ ፊት ገፍተው አቻነት ግቡን ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ 86ኛው ደቂቃ ላይ የይገዙ ቦጋለ የማዕዘን ምት የግንባር ሙከራ ወደ ውጪ ወጥቷል። ሀብታሙ ገዛኸኝም ከቴዎድሮስ ታፈሰ የተሰነጠቀን ኳስ 89ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውስጥ ሞክሮ ሙንታሪ አድኖበታል። ሲዳማዎች ከቀጥተኛ እና የማዕዘን ምት ኳሶች ግብ ለማግኘት ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ጨዋታው በሀዋስ 2-1 አሸናፊነት ተቋጭቷል።
ውጤቱን ተከትሎም ሀዋስ ከተማ ከላይ ስድስት ነጥብ ያላቸውን ሦስት ቡድኖች መቀላቀል ችሏል።