የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዋሳ ከተማ 2-1 ሲዳማ ቡና

ከሱፐር ስፖርት ጋር የተደረገው የሀዋሳ እና ሲዳማ አሰልጣኞች አስተያየት ይህንን ይመስላል።

አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – ሀዋሳ ከተማ

ጎሉ በቶሎ መገኘቱ ጨዋታውን ስለመቀየሩ

አዎ ፤ ማለት ይቻላል። አንደኛ ደርቢ ነው ሁለተኛ በዛ ሰዓት ጎል ስታገባ እና ሲገባብህ ልዩነት አለው። ስታገባ በራስ መተማመንህ ይጨምራል ትነሳሳላህ። ያንንም ጠብቀህ ለመጫወት ነው ጥረት የምታደርገው በዛ ሰዓት ማግባታችን ጥሩ ነው። እንደውም እኛ አስበን የነበረው በዛ ሰዓት ጥንቃቄ አድርገን 30 ደቂቃ ጠብቀን ነበር አጨዋወት ለመቀየር ያሰብነው። አጋጣሚ ግን ያንን ነገር መጀመሪያ ራሳችን በማሳካታችን ጥንቃቄውን መርጠን ነው እስከዕረፍት መውጣት የቻልነው። ዞሮ ዞሮ ጥቃቅን ስህተቶች አሉ። ዳኝነትን መናገር አልፈልግም። ያ ስሜታዊ አድርጎን ነበር ከዕረፍት በፊት። ከዕረፍት በኋላ ግን ልጆቼን አረጋግቼ ባለው ለመጫወት ሞክሪያለሁ እና እግዚአብሔር ይመስገን ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ።

አካላዊ ንክኪ ስለመብዛቱ

ደርቢ ስለሆነ እና ልጆቹ መበላለጥ ስለሚፈልጉ ነው እንዲህ ዓይነት ነገሮች የሚፈጠሩት እንጂ ውጪ ሲገናኙ ጓደኛሞች ናቸው። ግን ሜዳ ላይ መበላለጥ ስለሚፈልጉ እነዛ ነገሮች ይኖራሉ። አላስፈላጊ ካርዶችን በምትሰጥበት ጊዜ ግን እንቅስቃሴው ይወርዳል። ልጆቹ ፍርሀት ውስጥ ይገባሉ ። በተለይ የደርቢ ጨዋታ ላይ ካርዶች በጥንቃቄ ቢሰጡ ጥሩ ነው። ምክንያቱም ደጋፊው ኳስ ሊያይ ነው የሚገባው እና እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ቢስተካከሉ ብዬ ነው የማስበው።

ውጤቱ እንደሚገባቸው

በደንብ ይገባናል። እንደውም ግብ ጠባቂያቸው ኳስ ይዞ ጎል ውስጥ የገባ ይመስለኛል። በእርግጠኝነት እንደዛ ነው ያየሁት። ምንአልባት ቪዲዮውን ሳይ የማረጋግጠው ይሆናል ፤ ይገባናል ብዬ ነው የማስበው።

አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ – ሲዳማ ቡና

ስለጨዋታው አጀማመር

እንደፈለግነው አይደለም። የተከላካያችን ጥምረትም ጥሩ አልነበረም። የመናበብ ችግር ይታይ ነበር። ሁለቱም ግቦች የገቡብን በዛ ችግር ምክንያት ነው። ጥሩ የሚባል አልነበረም ፤ እንግዲህ የምችለውን ያህል አድርገናል። በተስተካከልንበት ሰዓት ከዕረፍት በኋላ ተመሳሳይ ስህተት ነው የተፈፀመው ፤ በዛ ምክንያት ነው የገባብን። ነገር ግን አሁን ገና ነው ጊዜው ችግር የለውም ፤ ያው ጨዋታ ነው ተፈጥቷዊ ነው። መሸነፍ ማሸነፍ ያለ ነው ፤ ባልጠበቅነው መልኩ ሄዷል።

የጎሉ በቶሎ መቆጠር ተፅዕኖ

ተፅዕኖ አለው። መጀመሪያ ላይ ተዘናግተው ነበር ፤ ተነሳሽነት አልነበራቸውም። በዛ መሀል ዝምብሎ አጋጣሚ ተቆጥሮብናል። ቅድም እንደገለፅኩት ማለት ነው። ከዛ ወደምንፈልገው ለመምጣት ጊዜ ወስዶብናል። ከዕረፍት በኋላም በተስተካከልንበት ሰዓት እንደዚሁ ተመሳሳይ ስህተት ተፈፅሟል። እንግዲህ ተፈጥሯዊ ነው ምንም ማድረግ አይቻልም።

ስለብርሀኑ አሻሞ ጉዳት እና ሙሉዓለም መስፍን መተካት

ሙሉዓለም በጣም ጥሩ ተጫውቷል ማለት ይቻላል። ከገባበት ጊዜ ጀምሮ በስርዓት በማስኬዱ ላይ በጣም ጥሩ ነበር። ብርሀኑ መጥፎ ሰዓት ላይ ነው የተጎዳው ለሚቀጥለው አገግሞ እንደምናየው ተስፋ አደርጋለሁ።

ጨዋታው ኃይል ስለመቀላቀሉ

በእኛ በኩል ኃይል የቀላቀለ ጨዋታ አልተጫወትንም። በተጋጣሚያችን በኩል ነበር። ያንን መጀመሪያም ተነጋግረናል። እንደዚህ ዓይነት አጨዋወት እንደሚመርጡ እናውቃለን። ነገር ግን ቅድም እንዳልኩት መዘናጋቶች ነበሩ። ያንን ጠብቆ ያለመጫወት ችግሮች ይታዩብን ነበር። ዛሬ ከሌላው ጊዜ ደከም ብለን ታይተናል።