ሪፖርት | ወላይታ ድቻ ተከታታይ ድል አስመዝግቧል

ምሽቱን የተደረገው የአዳማ ከተማ እና የወላይታ ድቻ ጨዋታ በዳቻ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በዛሬው የተጫዋቾች ምርጫ አዳማ ከተማ ከሁለተኛ ሳምንቱ ጨዋታ አብዲሳ ጀማልን አሳርፎ አቡበከር ወንድሙን ሲያሰለፍ ወላይታ ድቻ ግን ያለአሰላለፍ ለውጥ ጨዋታውን መጀመርን መርጧል።

ጨዋታው ፈጠን ብሎ የጀመረ ነበር። የመጀመሪያው አደገኛ አጋጣሚ በአዳማ በኩል ሲፈጠርም 4ኛው ደቂቃ ላይ አሜ መሀመድ በጥሩ ጊዜ አጠባበቅ ሳጥን ውስጥ ተገኝቶ ከኋላ የተነሳ ረጅም ኳስ ቢደርሰውም ሙከራው ወደ ውጪ ወጥቷል። አዳማዎች ኳስ በመያዝ አልፎ አልፎ ረጅም ኳሶችን በመላክ ተጨማሪ አደገኛ የግንባር ኳስ ዕድሎች ሲፈጥሩ የወላይታ ድቻ ቀጥተኛ ኳሶች ወደ ስንታየሁ መንግስቱ እና ምንይሉ ወንድሙ ጥምረት ይደርሱ የነበረበት መንገድም የጨዋታውን ግለት ከፍ ያደረገ ነበር። ሆኖም ይህ እንቅስቃሴ በደቂቃዎች ውስጥ አልፎ ጨዋታው ወደ መቀዛቀዝ አምርቷል።


ወላይታ ድቻዎች ከመጀመሪያው በተለየ ኳስ መያዝ ሲችሉ ቅብብሎቻቸው ግን በራሳቸው ሜዳ ላይ የተገደቡ ሆነዋል። አዳማዎችም የተጋጣሚያቸው ኳስ ምስረታ የሜዳውን አጋማሽ እንዳያልፍ ቢያደርጉም የሚያቋርጧቸውን ኳሶች ወደ ግብ ዕድልነት መቀየር አልቻሉም። ከመሀል ወደ ድቻ ሜዳ ያደላው የጨዋታ ሂደትም በዚህ ሁኔታ በአመዛኙ ከሳጥኖቹ ውጪ ባለው ቦታ ላይ እየዋለለ በመቀዛቀዙ ገፍቶበታል።

ጨዋታው ከውሀ ዕረፍቱ በኋላ መጠነኛ መነቃቃት ያሳየ መስሎ ነበር። ሆኖም ወላይታ ድቻ ከቆሙ ኳሶች አዳማዎች ደግሞ ወደ ሳጥን ረዘም ያሉ ኳሶችን ለመጣል ሲሞክሩ ቢታዩም ከባድ ሙከራ ሳንመለከት እና ጨዋታው ላይ የተለየ ሙቀት ሳይታይ ተጋምሷል።

ከዕረፍት በኋላ ጨዋታው በሙከራዎች መታጀብ ጀምሯል። አዳማ ከተማዎች የተሻለ ተጭነው መጫወት ሲችሉ ድቻዎች ሜዳቸው ላይ ሆነው የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን መጠበቅ የመረጡ መስለዋል። የመጀመሪያው ከባድ ሙከራ ሲደረግም 48ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ሆቴሳ ከረጅም ረቀት አክርሮ የመታው ኳስ ለጥቂት ወጥቷል። ወላይታ ድቻዎችም ከያሬድ ዳዊት የ51ኛ ደቂቃ የርቀት ቅጣት ምት በበረከት ወልደዮሀንስ አማካይነት ያደረጉት የግንባር ሙከራ በሴኩባ ካማራ ተይዟል። አዳማዎች ከተሻጋሪ ኳሶችም ወደ ግብ ለመድረስ ይጥሩ ነበር። 55ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ወንድሙ ከተሻጋሪ ኳስ ድቻዎች ሳያርቁት አግኝቶ ከሳጥኑ መግቢያ ላይ በቮሊ ላደረገው ሙከራ በግቡ ቋሚ ተመልሷል።

ቀጣዮቹ ደቂቃዎች አደጋ ያላቸው ቅጣት ምቶችን ሲያሳይን ወላይታ ድቻዎች ግብ ያገኙበት ሆኗል። 65ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ሆቴሳ ከቅጣት ምት ያደረገው አደገኛ ሙከራ በጽዮን መርዕድ ተመልሷል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ግን የድቻው ያሬድ ዳዊት ከርቀት ወደ ግብ የላከው የቅጣት ምት ኳስ የአዳማን ተከላካዮች እና ካማራን መሀል ለመሀል አልፎ ግብ ሆኗል። በዚህ መሀል ከጨዋታ ውጪ አቋቋም ላይ ሆኖ ኳሱን ባይነካም ግብ ጠባቂውን ያዘናጋው ስንታየሁ መንግሥቱ ግን ከዳኞች እይታ ውጪ ነበር።

ከግቡ በኋላ ድቻዎች ይበልጥ ወደ ግባቸው ተስበዋል። አዳማዎች ሰብሮ ለመግባት ጥረቶችን ሲያደርጉ ቢታዩም የወላይታዎች ስንታየሁ መንግሥቱን ኢላማ ያደረጉ ረጃጅም ኳሶች አስፈሪ ሲሆኑ ይታይ ነበር። ወደ መጨረሻው ላይ የአዳማ ጥቃት በርትቶ ቢታይም የወላይታ ድቻ ጥብቅ መከላከል ጨዋታው ተጨማሪ ግብ እንዳይቆጠርበት አድርጓል።

ወላይታ ድቻ ሁለተኛ ተከታታይ ጨዋታ ማሸነፉን ተከትሎ ነጥቡን ወደ ስድስት ከፍ ያደረገ አምስተኛው ቡድን ሆኗል።

ያጋሩ